Thursday, April 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በፋይናንስ አቅርቦት ችግር የ15 ባለ ኮከብ ሆቴሎች ግንባታ እየተጓተተ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአዲስ አበባ ከተማ 15 ባለ ኮከብ ሆቴል ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ ቢሆንም፣ ብድርም ሆነ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ባለመቻላቸው ለከፍተኛ ችግር እየተዳረጉ መሆኑ ታወቀ፡፡

ከኢትዮጵያ ሚሊኒየም ወዲህ በርካታ ሆቴሎች በአዲስ አበባ የተገነቡ ሲሆን፣ አሁንም በርካታ የሆቴል ፕሮጀክቶች በማያቋርጥ የግንባታ ሒደት ላይ ይገኛሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት እንኳን ከዓለም አቀፍ የሆቴል ማኔጅመንት ኩባንያዎች ጋር ኮንትራት የተፈራረሙና በራሳቸው ማኔጅመንት ለመተዳደር የተዘጋጁ፣ 15 ሆቴሎች በግንባታ ላይ ናቸው፡፡

ነገር ግን እነዚህ ሆቴሎች በዕቅዳቸው መሠረት ተገንብተው ሥራ ለመጀመር አለመቻላቸው እየተገለጸ ነው፡፡

በተለይ በኢትዮጵያ ግዙፍ መንግሥታዊ ባንክ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብድር መስጠት ማቆሙንና ለግንባታ ማጠቃለያ የሚሆን የውጭ ምንዛሪ እየቀረበ እንዳልሆነ ፕሮጀክቶቹን እያካሄዱ የሚገኙ ኢንቨስተሮች ይናገራሉ፡፡

ለአብነት የሰንሻይን ግሩፕ ባለቤት አቶ ሳሙኤል ታፈሰ፣ የዮቤክ ኤሌክትሪካል ኢንተርፕራይዝ ባለቤት አቶ ብርሃኔ ግደይ፣ የኔክሰስ ሆቴል ባለቤት አቶ ዳዊት ገብረ ፃዲቅ ችግሩ ከፍተኛ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ወደ ሆቴል ቢዝነስ በጥልቀት የገባው ሰንሻይን ግሩፕ በአዲስ አበባ ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ ማርዮት የሚያስተዳድረው፣ በሐዋሳ ከተማ ደግሞ ሒልተን የሚያስተዳድረው ሆቴል በመገንባት ላይ ነው፡፡

አቶ ሳሙኤል ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የሆቴል ፕሮጀክት በቢሊዮን የሚቆጠር ብር የሚፈልግ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሆቴል ግንባታ ብድር መስጠት አቁሟል፡፡ ሌሎቹ ንግድ ባንኮች ይኼንን ከፍተኛ ገንዘብ ማቅረብ ስለማይችሉ ዘርፉ እየተጎዳ ነው ብለዋል፡፡

‹‹እኛ ገና በግንባታ ሒደት ላይ የምንገኝ በመሆኑ ከውጭ ምንዛሪ ይልቅ እየተጎዳን ያለነው የብድር አቅርቦት አለመኖር ነው፡፡ መንግሥት ለዚህ ዘርፍ ትኩረት ሊያደርግ ይገባል፤›› ሲሉ አቶ ሳሙኤል አስረድተዋል፡፡

ሌላው የአቶ ብርሃኔ ግደይ ኢምፔሪያል አካባቢ ከስፖርት አካዳሚ ጎን እየተገነባ ያለው ሆቴል ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት እስካሁን 700 ሚሊዮን ብር የወጣበት ሲሆን፣ የስዊዘርላንዱ ግዙፍ ኩባንያ ሞቨንፒክ ሆቴልና ሪዞርት ሆቴሉን ለማስተዳደር ውል ተዋውሏል፡፡

አቶ ብርሃኔ እንደሚሉት ይህ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል የሲቪል ምሕንድስና ግንባታው ከተጠናቀቀ የቆየ ቢሆንም፣ የማጠቃለያ ግንባታ ለማካሄድ የሚያስፈልገውን 16 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ባለመቻላቸው ሥራ ተስተጓጉሏል፡፡

የሆቴል ግንባታው በባንክ ብድር የሚካሄድ በመሆኑ ብድሩ እየተከማቸ መሆኑን በመግለጽ፣ መንግሥት የውጭ ምንዛሪ እንዲያቀርብ አቶ ብርሃኔ ጠይቀዋል፡፡

ሌላው የሆቴል ፕሮጀክት ከቀለበት መንገድ ወደ የረር በሚወስደው መንገድ ገባ ብሎ የሚገኘው የኔክሰስ ሆቴል ፕሮጀክት ነው፡፡

ኔክሰስ ሆቴል ነባር ቢሆንም የሆቴል የማስፋፊያ ፕሮጀክት አካሂዶ የውጭ ምንዛሪ መፈለግ ከጀመረ ሁለት ዓመታት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

አቶ ዳዊት ገብረ ፃዲቅ፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ባለመቻላቸው፣ ከሌሎች የግል ንግድ ባንኮች ለማሟላት ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም አሁንም እንዳልተሟላላቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹ከሁለት ዓመት በፊት ሥራ መጀመር የነበረበት ኔክሰስ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል አሁንም ግንባታው አላለቀም፤›› ሲሉ ችግሩ የከፋ መሆኑን አቶ ዳዊት አስረድተዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ሆነ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስተያየት እንዲሰጡበት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡       

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች