Wednesday, April 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በጎማና በብረት ዋጋ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ታየ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ብቸኛው የጎማ ፋብሪካና አገር በቀል የብረት ፋብሪካዎች ሥራ የማቆም አደጋ አንዣቦባቸዋል

በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት የኢንዱስትሪ ምርቶች በሆኑት ጎማና ብረት ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እየታየ ነው፡፡ አገር በቀል የብረት ፋብሪካዎች ከአቅማቸው በታች እያመረቱ በመሆኑ በማምረቻ ዋጋቸው ላይ ከፍተኛ ግሽበት እንዳጋጠማቸው እየተናገሩ ነው፡፡

ከውጭ በሚገቡ የተለያዩ የጎማ ምርቶች ላይ ከስድስት መቶ እስከ አንድ ሺሕ ብር፣ በብረት ላይ ደግሞ በኪሎና በቤርጋ ከእጥፍ በላይ የዋጋ ጭማሪ ተከስቷል፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ ብቸኛው የጎማ ፋብሪካ ሆራይዘን አዲስ ጎማ አክሲዮን ማኅበር፣ በቂ የውጭ ምንዛሪ እያገኘ ባለመሆኑ ከአንድ ወር በኋላ ምርት እንደሚያቆም  አስታውቋል፡፡

በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት አገር ውስጥ የተመረቱ የብረት ዓይነቶች ከገበያ እየጠፉ ሲሆን፣ በተለይ ከውጭ እየገቡ በሚገኙ የተለያዩ የብረት ዓይነቶች የኪሎና የቤርጋ ዋጋ መናር ሥጋት ፈጥሯል፡፡

የ45 ዓመቱ የዕድሜ ባለፀጋ ሆራይዘን አዲስ ጎማ በዓመት ከ750 ሺሕ እስከ 800 ሺሕ ጎማዎችን የማምረት አቅም እንዳለው ይነገራል፡፡ እነዚህን ጎማዎች ለማምረት የሚጠቀማቸው 112 ዓይነት ጥሬ ዕቃዎችን ከውጭ በማስገባት ሲያመርት ቆይቷል፡፡

ነገር ግን ፋብሪካውን በሙሉ አቅሙ ለማንቀሳቀስ በዓመት 18 ሚሊዮን ዶላር ቢያስፈልገውም፣ ይህንን የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ባለመቻሉ የመዘጋት አደጋ እንዳንዣበበበት ታውቋል፡፡

የሆራይዘን አዲስ ጎማ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አካለወልድ አድማሱ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የፋብሪካው ምርቶች የውጭ ምንዛሪ በማዳን በኩል ጉልህ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ ነገር ግን ኩባንያው ጎማዎቹን ለማምረት የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ እያገኘ ባለመሆኑ ከአንድ ወር ተኩል በኋላ ሊዘጋ ይችላል ብለዋል፡፡

ሆራይዘን አዲስ ጎማ 62 ዓይነት ጎማዎችን ያመርታል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 37 የሚሆኑት የጎማ ዓይነቶች መመረት የጀመሩት ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ነው፡፡

ሆራይዘን የቀድሞውን አዲስ ጎማ ፋብሪካ ከመንግሥት ከገዛ በኋላ 600 ሚሊዮን ብር ኢንቨስት እንዳደረገ፣ የሚጠቀመው ቴክኖሎጂም በአሁኑ ወቅት ዓለም የሚጠቀምበት ነው ተብሏል፡፡

ሆራይዘን አዲስ ጎማ በአሁኑ ወቅት ከአቅም በታች በማምረት ላይ እንደሆነ፣ ለምርት የሚያስፈልገውን ጥሬ ዕቃ ከጨረሰ ከሥራ ውጪ እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡

አምራቾችም ሆነ ጎማ አስመጪ ነጋዴዎች የውጭ ምንዛሪ ባለማግኘታቸው ፍላጎትና አቅርቦት ባለመጣጣሙ፣ የብር የመግዛት አቅምም እንዲሁ በ15 በመቶ በመዳከሙ፣ የጎማ ዋጋ በነበረው ላይ ከ600 እስከ 1,000 ብር፣ እንዲሁም ቶሎ በማያልቁ የኮንስትራክሽንና የእርሻ ማሽን ጎማዎች ደግሞ 400 ብር ጭማሪ መታየቱን ለመረዳት ተችሏል፡፡

የብረት ገበያውም እንዲሁ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እየታየበት ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት ስምንት ቁጥር ብረት በኪሎ 260 ብር፣ ባለ አሥር በቤርጋ 400 ብር፣ ባለ 12 በቤርጋ 540 ብር፣ ባለ 16 በቤርጋ 890 ብር ተሸጧል፡፡ ይህ ዋጋ ከእጥፍ በላይ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት አገር ውስጥ የተመረተ ብረት ከገበያ እየጠፋ ሲሆን፣ በተለይም በገበያ ውስጥ የሚገኘው ከውጭ ወደ አገር የገባ ብረት መሆኑ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለግሉ ዘርፍ ሰሞኑን ካቀረበው 300 ሚሊዮን ዶላር 70 ሚሊዮን ዶላር ያህል ለትልልቅ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪዎች የቀረበ ቢሆንም፣ ይህ የውጭ ምንዛሪ ፋብሪካዎቹን ብዙ ርቀት እንደማያስኬዳቸው ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ መሠረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ሙሉጌታ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከውጭ በሚገቡ የተለያዩ የብረት ዓይነቶች ላይ ከእጥፍ በላይ የዋጋ ጭማሪ ተከስቷል፡፡

‹‹አገር በቀል ብረት አምራቾች በቂ የውጭ ምንዛሪ እየቀረበላቸው ባለመሆኑ ለገበያ የሚሆን ምርት እያቀረቡ አይደሉም፤›› በማለት አቶ ሰለሞን ገልጸው፣ ‹‹የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለብረት አምራቾች ያቀረበውም የውጭ ምንዛሪ ከአሥር ቀናት በላይ የሚያስኬድ ባለመሆኑ ፋብሪካዎቹ ከፍተኛ የመዘጋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል፤›› ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ከውጭ ብረት የሚያስገቡ ነጋዴዎች በዓመት 143.8 ሚሊዮን ዶላር ከተለያዩ ባንኮች ማግኘታቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በኢንቨስተሮችና በነጋዴዎች መካከል ያለው የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ያልተመጣጠነ በመሆኑ፣ አገር በቀል ኢንቨስተሮች ከገበያ የመውጣት አደጋ ሲጋረጥባቸው፣ ነጋዴዎች ደግሞ የበለጠ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ዕድል መፈጠሩ ለኢኮኖሚውም ጭምር ጉዳት እንዳለው አቶ ሰለሞን አስረድተዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች