Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናቀዳማዊ ቤተሰብ

ቀዳማዊ ቤተሰብ

ቀን:

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በፓርላማ ሲሰየሙ ባደረጉት ንግግር፣ በሕዝብ ዘንድ ትኩረትን ከሳቡት ጉዳዮች መካከል የቤተሰብ ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ የሰባት ዓመት ልጅ እያሉ ሩቅ፣ ጥልቅና ረቂቅ ራዕይ በውስጣቸው የተከሉትን፣ ያሳደጓቸውንና ለፍሬ ያበቋቸውን ወላጅ እናት ለማመሥገን እንዲፈቀድላቸው ሲጠይቁ ብዙዎች ልባቸው ተነክቷል፡፡ እናታቸው ከሌሎቹ ቅን፣ የዋህና ጎበዝ ኢትዮጵያውያን እናቶች እንደ አንደኛቸው የሚቆጠሩ፣ ቁሳዊ ሀብትና ዓላማዊ ዕውቀት እንደሌላቸው፣ በእናታቸው ውስጥ ሁሉንም የኢትዮጵያ እናቶች ዋጋና ምሥጋና እንደ መስጠት በመቁጠር፣ ‹‹ዛሬ በሕይወት ከአጠገቤ ባትኖርም ውዷ እናቴ ምሥጋናዬ ከአፀደ ነፍስ ይደርሳት ዘንድ በክብር ላመሠግናት እወዳለሁ፤›› ብለዋል፡፡ ሌሎች ኢትዮጵያውያን እናቶች በልጆቻቸው የነገ ራዕይ ላይ ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው በመገንዘብ ለሚከፍሉት መስዋዕትነት በምንም የማይተካ አድናቆት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ አይተኬ ሚናቸውንም እንዲወጡ አደራ ብለዋል፡፡ ‹‹. . . የሚስቶች ስኬት ሁለት-ሦስት ነው፡፡ ሁለት ሲሆን አንዱ የራሳቸው ሌላው የባላቸው፡፡ ሦስት ሲሆን ደግሞ የልጆቻቸውም ይጨመርበታል፡፡ አንዳንዴ የድል ስኬታቸው ከዚህም ይሻገራል፡፡ የእናቴን ራዕይ ተረክባ በብዙ የደገፈችኝና የእናቴ ምትክ የሆነችልኝ ውዷ ባለቤቴ ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው ከእነዚህ ሚስቶች ተርታ ትመደባለችና እጅግ አድርጌ ላመሠግናት እፈልጋለሁ፤›› በማለት ሰብዓዊ ስሜታቸውን ገልጸዋል፡፡ በምሥሉ ላይ የሚታዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይና ባለቤታቸው ከሦስት ልጆቻቸው ጋር ነው፡፡ 

‹‹ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ ነን››

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ባለፈው ሩብ ምዕተ ዓመት የኢትዮጵያ ጉዞ ውስጥ መጋቢት 24 ቀን የኢትዮጵያ ሕዝቦችን በጋራ ስለአንድነታቸው እንዲነሱ፣ ተስፋ እንዲያደርጉ የራሱን ታሪክ እያኖረ ይመስላል፡፡ መጋቢት 24 ቀን ከሰባት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያውያን ልዩነታቸውን ትተው የዘመናት ቁጭት የነበረ የተፈጥሮ ሀብታቸውን ብርሃን ሊፈነጥቁበት የመሠረት ድንጋይ የጣሉበት ቀን ነው፡፡ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በዓባይ ወንዝ ላይ ለመገንባት፡፡

ከሰባት ዓመታት በኋላ ሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ግጭት፣ መጠቃቃትና በሥልጣን መሻኮት ከፈጠረው የመበተን ሥጋት ውስጥ የተወለደውን አዲስ መሪ ኢትዮጵያውያን በሕግ አውጪው ፓርላማ ፊት በጠቅላይ ሚኒስትርነት በመሰየም፣ ስለኢትዮጵያ አንድነት በስሜት ያለቀሱበት ቀን ነው፡፡ ለሦስት ዓመታት በቆየው አስጨናቂ የፖለቲካ ቀውስና የሥልጣን ሽኩቻ ውስጥ አሸናፊ ሆነው የወጡትና በፓርላማ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሰየሙት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት ናቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማው ከተሾሙ በኋላ ባደረጉት ንግግር፣ መላ ኢትዮጵያውያንን በአገር ውስጥም ከአገር ውጭም የሚገኙትን በሚያክል ደረጃ አስደምመዋል፤ የአንድነትን ተስፋ በውስጣቸው ዘርተዋል፡፡

‹‹…አማራው በካራማራ ለአገሩ ሉዓላዊነት ተሰውቶ የካራማራ አፈር ሆኖ ቀርቷል፡፡ ትግራዋዩ በመተማ ከአገሬ በፊት አንገቴን ውሰዱ ብሎ የመተማ አፈር ሆኗል፡፡ ኦሮሞው በዓድዋ ተራሮች ላይ ስለአገሩ ደረቱን ሰጥቶ የአሩን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ከዓድዋ አፈር ተቀላቅሏል፡፡ ሱማሌው፣ ሲዳማው፣ ቤንሻንጉሉ፣ ወላይታው፣ ጋምቤላው፣ ጉራጌው፣ አፋሩ፣ ሥልጤው፣ ከምባታው፣ ሐዲያውና ሌሎቹም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሁሉ በባድመ ከአገሬ በፊት እኔን ብለው እንደወደቁ ከባድመ አፈር ጋር ተዋህደዋል፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ አባት እንዳሉት እኛ ስንኖር ሰዎች ስናልፍ አገር እንሆናለን፡፡ የየትኛውንም ኢትዮጵያዊ ክቡር ሥጋና ደም በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ አፈር ሆኖ ታገኙታላችሁ፡፡ ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናለን፤›› በማለት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለአገሩ ራሱን የሚሰዋና ሲሰዋም እንደኖረ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

በአንድ አገር ውስጥ ልዩነቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ነገር ግን መደማመጥ ካለ በሐሳብ ፍጭት ውስጥ መፍትሔ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ በሊቀመንበርነት መምራት ለጀመሩት ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግም፣ ‹‹ከስህተታችን ተምረን አገራችንን የምንክስበት ወቅት ነው፤›› ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

‹‹ከስህተቶቻችን ተምረን ወደፊት በመራመድ ማተኮር ያለብን ጉዳይ የተሻለች አገር ለሁላችንም በመገንባቱ ላይ ነው፡፡ ዋናው ቁምነገር አገራችንን ከፍ ወዳለ ምዕራፍ ማሸጋገሩና አንድነቷን ጠብቃ የምትቆይበትን ሁኔታ በቀጣይነት እያረጋገጡ መሄድ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ያስተማረን እውነታ በጊዜያዊ ችግሮች ተሸፍኖ መውደቅን ሳይሆን፣ ፈተናዎችን ወደ ዕድልና መልካም አጋጣሚ ቀይሮ ድል መቀዳጀትን ነው፤›› ሲሉ ጥሪ ያዘለ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የፓርላማው አባላት በስሜት ውስጥ ሆነው በከፍተኛ ጥሞና ሲከታተሏቸው የተሰማቸውንም ደስታ በዕንባ ሲገልጹ ተስተውለዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል የፓርላማው የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ ይገኙበታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ወደ ከፍተኛ አመራርነት ከመሸጋገራቸው ከአራት ዓመታት በፊት፣ በፓርላማው የሕዝብ ውክልና ተግባራቸውን በንቃት በሚፈጽሙበት ወቅት የአቶ ተስፋዬ ዳባ የቅርብ ጓደኛ ነበሩ፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተሰየሙ በኋላ ያደረጉት ንግግር የፈጠረባቸውን ስሜት በተመለከተ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ የፓርላማ አባል ከሆኑበት ቀን አንስቶ እንደዚህ ቀን ተደስተው እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡

‹‹ብሔር ብሔረሰቦች ለኢትዮጵያ አንድነት የከፈሉትን ዋጋ ዶ/ር ዓብይ የገለጹበት መንገድ ልብን የሚካ ነው፤›› ያሉት አቶ ተስፋዬ፣ ‹‹በዚህ አስጨናቂ ወቅት ለኢትዮጵያ የተሰጣት አንድ ክስተት ነው፣ አንድ ቆራጥ መሪ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ሁኔታ ወጥታ ወደ ሰላም እንድትመጣ የሚያደርግ፣ ኃይልን በሁሉም ኢትዮጵያ ውስጥ የዘራ ንግግር እንደነበር ተናግረዋል፡፡

አስተያየታቸውን የሰጡት ሌላው ከፍተኛ አመራር ደግሞ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ እሳቸውም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በውስጣቸው ያለውን የኢትዮጵያዊነት ስሜት እንዳወጣው ይናገራሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውጭ ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን፣ ‹‹አንዳንድ ጊዜ ከኢትዮጵያ ያነሰ የተፈጥሮም ሆነ የታሪክ ሀብት ባላቸው፣ ነገር ግን እጅግ በበለፀጉ አገሮች ውስጥ ራሳችሁን ብታገኙት ስለአገራችሁ ቁጭት ሳይሰማችሁ አይቀርም፡፡ ሁላችንም ውስጥ ያ ቁጭት አለ፡፡ እንደ አገር ያለንን ሀብት አሟጠን ለመጠቀም የምናደርገው ጥረት በቂ ሳይሆን ሲቀር መቆጨታችሁ አይቀርም፡፡ መቆጨትም አለባችሁ፡፡ ይህንንም ሁኔታ ለመለወጥ ለሁላችሁም የምትበቃ በዚያው ልክ ግን የሁላችንንም ተሳትፎ የምትፈልግ አገር አለችን፡፡ ዕውቀታችሁንና ልምዳችሁን ይዛችሁ ወደ አገራችሁ መመለስና አገራችሁን አልምታችሁ መልማት ለምትሹ ሁሉ እጃችንን ዘርግተን እንቀበላችኋለን፤›› ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ይህንንም ሆነ ጥቅሉን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በተለያዩ ምክንያቶች ከአገር ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንደተቀበሉትና ተስፋ እንደታያቸው በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሰው ሰው የሚሸት›› ሲሉም ንግግሩ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያካተተ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዴሞክራሲ፣ በፍትሕ፣ በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ መንግሥታቸው ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ በንግግራቸው ሲገልጹ፣ ‹‹መጪው ጊዜ በኢትዮጵያችን የፍቅርና የይቅርታ ጊዜ ነው፤›› ሲሉም አውጀዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት እንደ መንግሥትም እንደ ዜጎችም ከዴሞክራሲ ባህል አለመዳበር ጋር ተያይዞ በታዩ እጥረቶች፣ በዜጎች ሕይወትና በግልም በጋራም ንብረቶች ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት መድረሱ ተገቢ እንዳልነበርና ማስቀረት ይቻል እንደነበር ተናግረዋል፡፡

‹‹በተለያየ ጊዜ መስዋዕትነት ለከፈሉ የመብት ተከራካሪዎችና ፖለቲከኞች፣ በቅጡ ሳይቦርቁ ሕይወታቸው ለተቀጠፈ ለውጥ ፈላጊ ወጣቶች፣ ለሥነ ልቦናዊና አካላዊ ቀውስ ለተዳረጉ ቤተሰቦችና ግለሰቦች ከልብ የመነጨ ይቅርታ እጠይቃለሁ፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ‹‹ለተፈጠሩ ችግሮች እልባት በማበጀት ሕዝባችንን እንደምንክስም ጭምር በዚሁ አጋጣሚ ቃል እገባለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ያለወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት አገር የትም ልትደርስ እንደማትችል የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ለወጣቶች ተስፋ የምትሰጥ እንጂ ተስፋ የምታስቆርጥ አገር እንዳትሆን የምንችለውን ሁሉ እንደምናደርግ ቃል እገባለሁ፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ለመሥራት፣ የመናገር የመሰብሰብና የመደራጀት ነፃነት ተግባራዊ እንደሚሆን ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለዓመታት የቆየ ግጭት በሰላም እንዲፈታና በደም የተሳሰሩ ሁለት ሕዝቦች ወንድማማችነት እንዲቀጥል እንደሚተጉ በመናገር፣ በኤርትራ መንግሥት በኩልም ዝግጁነት እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ፍላጎታቸውና ዕቅዳቸውን ለመተግበር የሚችል መሆኑን የተጠራጠሩ የመኖራቸውን ያህል፣ ዕገዛ ካገኙ መፈጸም የሚችሉ መሆናቸውንም በእርግጠኝነት የሚናገሩ አሉ፡፡

የቀድሞ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ ‹‹በዛሬው ቀን በድርጊቱ ብቻ ሳይሆን በመልዕክቱም ጭምር ሐሴት ያልወረረውና አንዳች በጎ ስሜት ያልነዘረው ይኖር ይሆን? እርግጥ ይህ በጎ ምልክት አዎንታዊ ጅምር ብቻ ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ በዚሁ መንፈስ ተዛዝለን ሳይሆን ተጋግዘን መዝለቅ ነው፤›› ሲሉ በማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ትብብር ጠይቀዋል፡፡

አቶ ተስፋዬ ዳባ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግሮችን የመተንተንና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የመፍታት አቅም እንዳላቸው እንደሚያውቁ፣ ሁሉም በየፊናው ካገዛቸው ታሪክ የመቀየር ዕድል እንደሚፈጠር እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...