በተጠረጠሩበት የማታለልና ሐሰተኛ ሰነድ መጠቀም ወንጀሎች የ50 ሺሕ ብርና የ40 ሺሕ ብር ዋስትና የተፈቀደላቸው [መምህር] ግርማ ወንድሙን፣ ፖሊስ በነፍስ ግድያ እንደሚጠረጥራቸው በማመልከቱ አለመፈታታቸው ታወቀ፡፡
ፖሊስ [መምህር] ግርማ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፈቃድ ሳያገኙ ፈቃድ እንደተሰጣቸው በማስመሰል ሐሰተኛ ሰነድ እንደተጠቀሙ በመግለጽ፣ ሰነዱን እያስመረመረ መሆኑን ገልጾ፣ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ኅዳር 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ፍርድ ቤቱን ጠይቆ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን ውድቅ አድርጎ ተጠርጣሪው በ40 ሺሕ ብር ዋስ እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ፖሊስ እሳቸውን በነፍስ ግድያ እንደሚጠረጥራቸው በመግለጽ ለፍርድ ቤቱ ማመልከቻ በማቅረቡ፣ ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ ሰነዶችን እንዲያቀርብ ለኅዳር 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ተጠርጣሪው ወሰን ግሮሰሪ አካባቢ የሚኖሩ ግለሰብን ቤት በማሸጥና ገንዘቡንም ‹‹ይፀለይበት›› በማለት መውሰዳቸውን በሚመለከት ፖሊስ ካቀረበባቸው ክስ፣ በ50 ሺሕ ብር ዋስ እንዲለቀቁ ትዕዛዝ መስጠቱ ይታወሳል፡፡
ነገር ግን በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ቅር የተሰኘው ፖሊስ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ያለ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ኅዳር 17 ቀን 2008 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የፖሊስን ማመልከቻ ውድቅ በማድረግ የሥር ፍርድ ቤትን ትዕዛዝ አፅድቆ በ50 ሺሕ ብር ዋስ እንዲለቀቁ አዟል፡፡ ነገር ግን ተጠርጣሪው በነፍስ ግድያ በመጠርጠራቸው ከእስር አልተፈቱም፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ በሪፖርተር ቅጽ 21 ቁጥር 1622 ዕትም፣ ‹‹በ50 ሺሕ ብር ዋስ ይፈቱ የተባሉት [መምህር] ግርማ ይግባኝ ተጠየቀባቸው›› በሚለው ዜና ውስጥ ‹‹ከቤተ ክህነት እንደተሰጣቸው የገለጹት ሰነድ በፎረንሲክ ተመርምሮ ሐሰተኛ መሆኑን እንዳረጋገጠ ፖሊስ ለፍርድ ቤት አስረድቷል፤›› የሚለው አገላለጽ በስህተት ስለሆነ፣ ‹‹ሰነዱን ለምርመራ ለፎረንሲክ ሰጥቶ እየተጠባበቀ መሆኑን አስረድቷል፤›› ተብሎ ተስተካክሎ እንዲነበብ አንባቢያንን ከይቅርታ ጋር እንጠይቃለን፡፡