Saturday, November 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እንዲጀመር ከማደናቀፍ መደጋገፍ ይቅደም!

  ኢትዮጵያ ከአንድ የታሪክ ምዕራፍ ወደ ሌላው እየተሸጋገረች ዘመናትን ያስቆጠረች ባለታሪክ አገር ናት፡፡ ሌላው ቀርቶ ከዘመነ መሳፍንት ወደ ማዕከላዊ መንግሥት ምሥረታ፣ ከአሀዳዊ ወደ ፌዴራላዊ ሥርዓት የተሸጋገረችባቸው ታሪካዊ ሒደቶች በበርካታ ውጣ ውረዶች ታጅበው እዚህ ዘመን ላይ ተደርሷል፡፡ የታሪክ ሒደት በየትውልዱ የሚቀጥል ስለሆነ፣ አሁን ደግሞ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እየተከፈተ ነው፡፡ ይህ ምዕራፍ የመንግሥት ሥልጣን ያለ ደም መፋሰስ ወይም ግርግር እየተቀባበሉ የሚሄዱበት መሆኑ ደግሞ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ እዚህኛው ምዕራፍ ላይ ለመድረስ አገሪቱ ላለፉት ሦስት ዓመታት ያጋጠማት ቀውስ ይታወቃል፡፡ ይህ ቀውስ ያደረሰው ሰቆቃም እንዲሁ፡፡ አሁን ከዚህ የቀውስ አዙሪት ውስጥ በአስቸኳይ በመውጣት ሰላም የሰፈነባት ዴሞክራሲያዊት አገር እንድትገባ፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ዜጎች አስተዋጽኦ ይጠበቃል፡፡ አዲስ ምዕራፍ ሲጀመር ቆሞ መተቸት፣ ከግልና ከቡድን ጥቅም አኳያ የአገር ጉዳይን ማስላትና እንቅፋት መሆን ለአገርም ለሕዝብም አይጠቅምም፡፡ ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር ሥራቸውን ሲጀምሩ ከመደጋገፍ ይልቅ፣ የተለመደው ማደናቀፍ ከተጀመረ እንኳን ለውጥ በነበረበት መቀጠልም አይቻልም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት አዲሱ አስተዳደር በሳል አመራር እንዲሰጥ፣ ብሔራዊ መግባባት እንዲጀመር፣ በአገሪቱ ሁለንተናዊ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገርና ለመደራደር በቅን ልቦና መዘጋጀት ይገባል፡፡ ከማደናቀፍ መደጋገፍ ይበጃል፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥራ ሲጀምሩ ከተለያዩ አቅጣጫዎች በተለያዩ ምልከታዎች እንዲያከናውኗቸው ተብለው ምክረ ሐሳቦች መቅረባቸው የሚደገፍ ቢሆንም፣ ከምክረ ሐሳቦቹ ባልተናነሰ ከትምህርትና ከልምድ የተገኙ ድጋፎች ያስፈልጋሉ፡፡ ሁሉንም ነገር አንድ ሰው ላይ ጭኖ ለውጥ መጠበቅ ስለማይቻል፣ ከሚቀርቡት ሐሳቦች ባልተናነሰ ድጋፍ ማድረግ ይጠቅማል፡፡ ‹‹ጨለማ ላይ ከማፍጠጥ ቁራጭ ሻማ መለኮስ›› እንዲሉ፣ ሰጥቶ ለመቀበል የሚያስችሉ የሐሳብ ልውውጦች በተግባራዊ ድጋፍ ሊታጀቡ ይገባል፡፡ እዚህች ታሪካዊት አገር ውስጥ ዕውቀትም ጥንካሬም ሊኖር ቢችልም፣ ለተግባራዊ ለውጥ ካልማሰኑ ግን ውጤቱ ኃይል ማባከን ይሆናል፡፡ አሁን ቀዳሚው ጉዳይ ባጋጠሙ ተቃውሞዎች ምክንያት የተፈጠሩትን ግጭቶች በማርገብ ሰላም ማስፈን፣ ሕዝብን ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚያቀራርቡ፣ ለአገሩ ልማትና ዴሞክራሲ ተዋናይ እንዲሆን የሚያስችሉ ተግባራትን ማመቻቸትና አገሪቱን ከገባችበት ማጥ ውስጥ ማውጣት መቅደም አለበት፡፡ ይህ ዕውን ይሆን ዘንድ ደግሞ ከማደናቀፍ ይልቅ መደጋገፍ ላይ ይተኮር፡፡

  ኢትዮጵያዊነት የሚለመልመውና የሚያብበው ቅራኔ ውስጥ ተዘፍቆ በመኖር አይደለም፡፡ በመግባባት እንጂ፡፡ በአገር የጋራ ጉዳይ ላይ ለመግባባት የሚቻለው ግን ሐሳብን በነፃነት መግለጽ፣ መደራጀት፣ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ መሳተፍና በሕግ የበላይነት ሥር በነፃነት መኖር ሲቻል ነው፡፡ ብሔር፣ ቋንቋ፣ እምነት፣ ባህል፣ የፖለቲካ አቋምና የመሳሰሉ ልዩነቶችን በማጦዝ መቃረን የፈየደው የለም፡፡ ነገር ግን ልዩነቶችን ይዞ በአገር የጋራ ጉዳይ ላይ በአንድነት መቆም ይቻላል፡፡ በብሔሬ፣ በሃይማኖቴ፣ በቋንቋዬ፣ ወዘተ. በደል ደርሶብኛል እያሉ ከማላዘን በመውጣት በኅብረ ብሔራዊ አንድነት ጥላ ሥር የዘመናት ቅሬታዎችን ማስወገድ ይቀላል፡፡ የአሁኗ ኢትዮጵያ ከብሔር ብሔረሰቦች ብዝኃነት በተጨማሪ፣ የአስተሳሰብ ብዝኃነት የሚነግሥባት እንድትሆን ከአፍራሽ ድርጊቶች መታቀብ ይገባል፡፡ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቷ የተጠናከረ ዴሞክራሲያዊት አገር ዕውን የምትሆነው በተከፋፈለና ዓይንህን ለአፈር በሚባባል የጽንፈኝነት አራጋቢ ሳይሆን፣ አገራቸውን ከልብ በሚወዱ አርቆ አሳቢ ዜጎች ነው፡፡ የፖለቲካውንም ሆነ ሌላውን ልዩነት ወደ ጎን በማድረግ በሰከነ መንፈስ ለመነጋገር ሁሉም ወገን ልቡን በቅንነት ይክፈት፡፡ ተረት ከሚመስሉ አደናጋሪ ትርክቶች በመላቀቅ ለአገር ግንባታ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን ይዘን እንቅረብ፡፡ ሐሳቦች ተፋጭተው የበለጠው ነጥሮ ይውጣ፡፡ የሐሳብ ልዩነትም ይከበር፡፡ በሐሳብ መለያየት ሞት አይደለምና፡፡

  ኢትዮጵያ የሁሉም ልጆቿ እናት እንድትሆን የሚያግዙ ፍሬ ነገሮች ላይ ማተኮር ጠቃሚ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ተሞክረው ፍሬ ያላፈሩት ጽንፈኝነት፣ ጥላቻ፣ ሐሜት፣ አሉባልታና ፍሬ ከርሲ ነገሮች ይወገዱ፡፡ እንዲህ ዓይነት አላስፈላጊ ነገሮች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች መካከል ሳይቀር ብሔር ተኮር ግጭት በመቀስቀስ፣ ወገኖቻችንን የእሳት እራት ነው ያደረጉት፡፡ ኢትዮጵያ ቧልተኞች፣ ግድ የለሾችና ራስ ወዳዶች የሚፈነጩባት ሳትሆን፣ ለአገራቸው ግድ የሚሰጣቸው ልጆቿ አንገታቸውን ቀና አድርገው ኃላፊነታቸውን የሚወጡባት ልትሆን ይገባል፡፡ በቡድን እየተደራጁ አገርን መዝረፍ፣ ሕዝብን ማስለቀስ፣ ወጣቱን ተስፋ ማሳጣትና ቀውስ መፍጠር ሊያከትም ይገባል፡፡ የዘመኑ ትውልድ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት የሰፈነባት አገር እንድትኖረው ይፈልጋል፡፡ ይህ ምኞቱ ደግሞ ዕውን የሚሆነው ለአገር የጋራ ጉዳይ በአንድነት መሠለፍ ሲቻል ነው፡፡ አዲሱ አመራር ሥራውን ሲጀምር ከወጣት ጀምሮ እስከ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድረስ ትልቅ ዕገዛ ያስፈልገዋል፡፡ ከዕገዛው በተጨማሪ ትዕግሥትም ይሻል፡፡

  ይህንን ታሪካዊ ወቅት የአዲስ ታሪክ ምዕራፍ መጀመርያ ማድረግና መሠረታዊ ለውጥ ሊገኝ የሚችለው፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ እንደሆነ ሲታመን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያለፉት 27 ዓመታት ብቻ ሳይሆን ለዘመናት የተጠራቀሙ ችግሮች ያሉባት አገር ናት፡፡ እነዚህ ችግሮች በተቻለ መጠን እንዲፈቱ ለብሔራዊ መግባባት ቅድሚያ መስጠት ተገቢ ነው፡፡ ኢሕአዴግ አመራሩን ለውጦ ተተኪውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሰይም፣ በውስጡ ከፍተኛ ትግል ማድረጉ መቼም ቢሆን ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ይህ ትግል በሰላማዊ ምርጫ ተጠናቆ እዚህ ደረጃ ላይ ሲደረስ፣ በተቃውሞው ጎራ ያሉ ኃይሎችም ከዚህ ትምህርት ቢቀስሙ ይበጃቸዋል፡፡ አንድ የፖለቲካ ድርጅት እግርና እጁን ተይዞ መንቀሳቀስ ሲያቅተው ለውጥ እንደሚያስፈልገው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ‹‹በሽታውን የደበቀ መድኃኒት አይገኝለትም›› እንደሚባለው፣ ችግርን እያድበሰበሱ በነበረው መቀጠል የራስን ፍፃሜ ማፋጠን ነው፡፡ የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች ለውጥን ከኢሕአዴግ ብቻ ከጠበቁ፣ ከሁለት ዓመት በኋላ በሚደረገው ምርጫ እንዴት ሆነው ሕዝብ ፊት ይቀርባሉ? እንደ በፊቱ ሕዝብን ማምታታት እንደማይቻል ይህ ዘመን እያሳየን ነው፡፡ አሁን ዋናውና መሠረታዊው ጉዳይ የለውጥ ኃይል ሆኖ መውጣት ብቻ ነው፡፡ ለዘመናት አልሠራ ያሉ ተሞክሮዎችን በመደጋገም በነበሩበት መቀጠል አይቻልም፡፡ ከሰላማዊው የፖለቲካ ትግል አፈንግጦ ነውጥ መፍጠርም ለሕዝብ ትርጉም የለውም፡፡ በዚህ ወሳኝ ጊዜ ከኢሕአዴግ መማር ብቻ ሳይሆን፣ የውስጥ ገመናን አብጠርጥሮ ፈትሾ ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ትግል መዘጋጀት ለሚታሰበው ለውጥ ትልቅ ድጋፍ ነው፡፡

  በርካታ ጥያቄዎችና ፍላጎቶች ባሉባት የአሁኗ ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ አስተዳደራቸው እንደሚፈተኑ ግልጽ ነው፡፡ ፈተናው ቢከብድም ማለፍ ግን የሚቻለው ድጋፍ ሲኖር ነው፡፡ ይህ ድጋፍ ከኢሕአዴግ ይጀምራል፡፡ የኢሕአዴግ አመራሮችና አባላት በሙሉ ልብ የግንባራቸውን ሊቀመንበር መደገፍ አለባቸው፡፡ የገዛ ድርጅታቸው ድጋፍ ያላደረገላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ምንም ቢማስኑ ውጤት አይኖራቸውም፡፡ ኢሕአዴግ በዚህ ግንዛቤ ድጋፉን ይስጥ፡፡ የተከፋፈለ መንግሥት ፀንቶ ሊቆም አይችልምና፡፡ የተቃዋሚ ፖለቲካ አመራሮችም ጥያቄዎችን ከመደርደር ጎን ለጎን ድጋፍ ያበርክቱ፡፡ የፖለቲካው ምኅዳር ተከፍቶ በነፃነት የሚወዳደሩበት ምርጫ የሚመቻቸው በዚህ መሠረት አርቀው ሲያስቡ ነው፡፡ ልሂቃኑም ከዝምታ ወይም ከአጉል ትችት ታቅበው ለተሻለች ኢትዮጵያ መገኘት ሲሉ ድጋፍ ይስጡ፡፡ ወጣቶች በእርጋታና በትዕግሥት ውስጥ ሆነው ዕገዛ ያድርጉ፡፡ አስተዋዩና ጨዋው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደተለመደው ተምሳሌታዊነቱን እያሳየ ድጋፉን ይቸር፡፡ በአገር ጉዳይ ላይ በነፃነት የሚነጋገሩበትና የሚደራደሩበት ብሩህ ጊዜ እንዲፈጠር ይህ ወቅት ወሳኝ ነው፡፡ ይህንን መልካም አጋጣሚ አበላሽቶ ሌላ ቀውስ ውስጥ መግባት በታሪክ ስለሚያስጠይቅ መጠንቀቅ ይሻላል፡፡ አሁን ጊዜውን የአዲስ ታሪክ ምዕራፍ መጀመርያ ማድረግ ይገባል፡፡ ታሪክ ይሠራል እንጂ አይፈጠርም፡፡ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እንዲጀመር ከማደናቀፍ መደጋገፍ ይቅደም!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ሰርጌ ላቭሮቭ ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ በአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ ምዕራባውያንን አጣጣሉ 

  የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ለአፍሪካ አገሮች ላደረጉት...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...

  የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከታክስ በፊት 27.5 ቢሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ

  የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2014 ሂሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 27.5...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን 55 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ወሰነ

  የአዋሽ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ ዛሬ ህዳር 17 ቀን 2015...

  ከብሔራዊ ባንክ እውቅና ያገኘው ፔይሊንክ አክሲዮን ማህበር ምሥረታውን አካሄደ

  ከገንዘብ ንክኪ ነፃ የሆነ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ለመተግበር ያቀደው...

  የተወሳሰበው ሰላም የማስፈን ሒደት

  የደቡብ አፍሪካ የሰላም ስምምነት ተፈርሞ ብዙም ሳይዘገይ የኬንያው ቀጣይ...

  በግብርና ዘርፍ ለመሰማራት ያቀደው ድርዜማ

  ከፋይናንስ ተቋማት ውጪ ባሉ የተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች በአክሲዮን ኩባንያ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ይደረግ!

  የሰላም ስምምነቱ ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ሊሆን የሚችልባቸው ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ሚሊዮኖችን ለዕልቂት፣ ለመፈናቀል፣ ለከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና መሰል ሰቆቃዎች የዳረገው አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት...

  ዘረፋ የሚቆመው በተቋማዊ አሠራር እንጂ በዘመቻ አይደለም!

  ኢትዮጵያ ውስጥ ሌብነት ከመንግሥት አቅም በላይ ሆኖ ለያዥ ለገናዥ ሲያስቸግር ከማየት በላይ አሰቃቂ ነገር የለም፡፡ በፌዴራል፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች መረን የተለቀቀው ሌብነት አስነዋሪ መሆኑ...

  ሰላም ዘላቂ የሚሆነው ቃል ሲከበር ብቻ ነው!

  እንደ አለመታደል ሆኖ የሰሜን ኢትዮጵያ አውዳሚ ጦርነት ውስጥ ለሁለት ዓመታት ከተከረመ በኋላ የሰላም መንገድ ተጀምሯል፡፡ በአገር በቀል ሽምግልና ማለቅ የነበረበት ከአገር ውጪ አስጉዞ፣ በባዕዳን...