Tuesday, December 6, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  መሪ ከመተካት በላይ የተመሪው ሕዝብ ጉዳይ ያሳስባል!

  ኢሕአዴግ ሊቀመንበሩን ለመምረጥ አንድ ሳምንት ስብሰባ ላይ ከርሟል፡፡ ተመራጩ ሊቀመንበር በፓርላማ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ይሰየማል፡፡ ይህ የኢሕአዴግ አሠራር ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከኃላፊነት የመልቀቂያ ጥያቄ ካቀረቡበት ጊዜ ጀምሮ፣ ከአንድ ወር በላይ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አንዱ አነጋጋሪ ጉዳይ ተተኪውን መሰየም ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት የተተኪው ማንነት በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ቢያነጋግር አይገርምም፡፡ ነገር ግን አሁንም በፍፁም መዘንጋት የሌለበት ከምንም ነገር በላይ አሳሳቢው የሕዝብ ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአገሩ በላይ ምንም የለውም፡፡ አገሩን የሚወድ መሪ ከሁሉም ነገር በላይ የሚገነዘበው የሕዝቡንና የአገሩን ቁርኝት ነው፡፡ ይህ ቁርኝት ከትውልድ ወደ ትውልድ በመስዋዕትነት ጭምር የተገነባ ስለሆነ፣ መሪን ከመተካት በላይ የተመሪው ሕዝብ ጉዳይ ተደጋግሞ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሰየም ይህን መሠረታዊ ጉዳይ ለአፍታም መዘንጋት አይኖርበትም፡፡

  እንደሚታወቀው አገር መስቀለኛ መንገድ ላይ ሆና ሕዝቡ ከዛሬ ነገ ምን ይመጣ ይሆን እያለ በሚጨነቅበት ጊዜ፣ የአገር ህልውና ምን ያህል አሳሳቢ መሆኑን መረዳት አያዳግትም፡፡ ይህ አስተዋይ ሕዝብ የሚጨነቀው ለአገሩ ነው ሲባል፣ የአገሩ ህልውና አደጋ ውስጥ ከወደቀ በታሪኩ ዓይቶት የማያውቅ ቀውስ ውስጥ ይዘፈቃል ማለት ነው፡፡ ሕዝባችን ዘመናትን የተሻገረው ኅብረ ብሔራዊ አንድነቱን አስጠብቆ እንደመሆኑ መጠን፣ ይህ አንድነት ከተናጋበት የእኔ የሚላት አገሩ አትኖርም፡፡ ኢሕአዴግ መሪውን ሲመርጥም ሆነ ሲሰይም ጉዳዩ የአገር እንጂ የድርጅት ብቻ ተብሎ አይተውም፡፡ ለመተው ከታሰበም ስሜት አይሰጥም፡፡ አገርን ቀውስ ውስጥ የከተቱት የሦስት ዓመታት ተቃውሞዎችና ሁከቶች ዋነኛ መንስዔአቸው ከኢሕአዴግ ጋር የሚያያዝ በመሆኑ፣ ተተኪው መሪ ሲመጣ የመጀመርያው ትኩረቱ የሕዝብ ፍላጎት መሆን አለበት፡፡ ሥልጣነ መንበሩን የተቆናጠጠው ተተኪ ማንነቱ ሳይሆን፣ ለአገርና ለሕዝብ ሰንቆ የመጣው ራዕይ ትኩረት መሳብ አለበት፡፡ የድርጅትን ዓላማ ከማስፈጸም በላይ የሕዝብ ጉዳይ ከምንም ነገር በላይ ይቀድማል፡፡ አገሪቱን የገጠማት ቀውስ መነሻም የሕዝብ አለመደመጥ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡

  ኢሕአዴግ ተተኪ በመምረጥና በመሰየም ብቻ ተልዕኮውን እንዳበቃ ቆጥሮ ወደ ተለመደው ሥራ ልግባ ካለም ችግር ነው፡፡ ተተኪው የሥልጣኑን እርካብ በሚገባ ጨብጦ ሕዝቡን በእኩልነት ማስተዳደር የሚቻለውና የተሻለች ኢትዮጵያ እንድትፈጠር ጥርጊያውን የሚያመቻቸው፣ ኢሕአዴግ በዚህች ታላቅ አገር መሠረታዊ ለውጥ እንዲመጣ ሙሉ ፈቃድ ሲያሳይ ነው፡፡ ሕዝብም በተደጋጋሚ ሲጠይቅ የነበረው ፍትሕ ማግኘት፣ በእኩልነት ያለ አድልኦ መተዳደር፣ ሐሳቡን በነፃነት መግለጽ፣ በሚፈልገው የፖለቲካ ድርጅት መሳተፍ፣ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩና በገዛ አገሩ በነፃነት መኖር ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ ተቀባይነት ባለማግኘቱ የተፈጠረው ብሶት ነው፡፡ ይህ ብሶት ተጠራቅሞ ሲገነፍል ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ተቃውሞ ነው ያጋጠመው፡፡ ሰላማዊ ተቃውሞን የሚያስተናግድ ሥርዓት ባለመለመዱም በገሃድ የታየው ሞትና ውድመት ነው፡፡ ይህ አሳዛኝ ሁኔታ በተከታታይ በመቀጠሉም የአገር ህልውና ለአደጋ ተዳርጓል፡፡ የሕዝቡ ሰላም ተናግቷል፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ እጃቸውን አስረዝመው ያስገቡ ኃይሎች ለሳላማዊ የፖለቲካ ትግል የቀረችውን እንጥፍጣፊ በመደፋፋት፣ ነውጡ ገጽታውን እየቀያየረ በአውዳሚነቱ እንዲቀጥል አሉታዊ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በዚህ መሀል ግን ሕዝብ ተሳቋል፡፡

  ሌላው አሁንም አሳሳቢ እየሆነ የቀጠለው የመንግሥትና የፓርቲ መደበላለቅ ነው፡፡ ምንም እንኳ ገዥው ፓርቲና መንግሥት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚገናኙባቸው በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም፣ የሁለቱ ሚና እየተደበላለቀ አገርን ችግር ውስጥ መክተቱ የታወቀ ነው፡፡ ይህ መታረም ብቻ ሳይሆን በፍፁም መወገድ ያለበት ነው፡፡ መንግሥት በሕጉ መሠረት ሥራውን ሲያከናውን የፖለቲካው መስመር ራሱን ችሎ መሄድ አለበት፡፡ መንግሥት ተቀዳሚ ተግባሩ የመላውን ሕዝብ ጥቅም ማስከበርና ደኅንነቱን ማስጠበቅ ሲሆን፣ የፖለቲካ ፓርቲ ደግሞ እስከ ቀጣዩ ምርጫ ድረስ የሕዝብን ልብ እያማለለ ሥራውን ማከናወን ነው፡፡ ገዥ ፓርቲ መሆን ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚ ፓርቲ መሆንም ግዴታ ነው፡፡ ይኼንንም የሚወስነው የሕዝብ ድምፅ ብቻ መሆኑ መታመን አለበት፡፡ እስካሁን የተመጣበት መንገድ ጥሩ ስላልነበረ በርካታ ችግሮች አጋጥመዋል፡፡ ከፍተኛ ጉዳትም ደርሷል፡፡ ኢሕአዴግ በዚህ ስሜት ቀሪዎቹን ሁለት ዓመታት በማገባደድ፣ መጪውን ምርጫ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ የማድረግ ኃላፊነትን ማሰብ አለበት፡፡ የተተኪው መሪ ሚናም ይህንን በኩረ ሐሳብ ማስፈጸም መሆን ሲችል ለሕዝብ እንደ ትልቅ ስጦታ ይቆጠራል፡፡ መንግሥት ኃላፊ ሲሆን አገር ግን ለትውልዶች የምትላለፍ ናት፡፡ በትውልድና በታሪክ ላለመጠየቅ ሕዝብን ማሰብ ይገባል፡፡

  አሁን ከኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችም ሆነ ከዋናው ግንባር ይልቅ አሸናፊ መሆን ያለበት ሕዝብ ነው፡፡ በመላ አገሪቱ በአራቱም ማዕዘናት የሚኖረው መላው ሕዝብ የሥልጣኑ ዋነኛ ባለቤት መሆኑ መታመን ይኖርበታል፡፡ አሁን የሚተካው መሪም ሆነ ወደፊት አገሪቱን የመምራት ዕድሉን የሚያገኙ ዜጎች በጥልቅ ማሰብ ያለባቸው፣ ለዘመኑ ትውልድ የሚመጥን ኃላፊነት እንዳለባቸው ነው፡፡ ይህ ትውልድ ዘመኑ ካፈራው ዕውቀትና ቴክኖሎጂ ተቋዳሽ ስለሆነ አገሩ ከሌሎች የሠለጠኑ አገሮች ተርታ እንድትሠለፍ ይፈልጋል፡፡ በአገሩ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና እንዲኖር ምኞቱ ነው፡፡ በሌሎች አገሮች የሚያየው ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ይናፍቀዋል፡፡ ሰብዓዊ መብቱ ተከብሮ በነፃነት መኖር ያምረዋል፡፡ ወደ አመፅና ብጥብጥ ከሚመሩ ኋላቀርና ብልሹ አሠራሮች በመላቀቅ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሠፈነበት ሥርዓት እንዲኖር አጥብቆ ይፈልጋል፡፡ ይህንን ከግምት ውስጥ ያስገባ ዓላማ የሰነቀ መሪ የሕዝብን ልብ ማሸነፍ ይችላል፡፡ ከጥላቻና ከጽንፈኝነት የተላቀቀ ማኅበረሰብ መፍጠር የሚቻለው የጋራ ግብና ራዕይ የሚኖርበት ዓውድ ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ሕዝብም የሚፈልገው ይህንን ነው፡፡

  ደጋግመን እንደምንለው ኢትዮጵያ ታላቅ አገር ናት፡፡ የታላቅ ሕዝብም አገር ናት፡፡ ይህ ኩሩ፣ ጨዋና አስተዋይ ሕዝብ በአግባቡ የሚመራው ካገኘ ታላላቅ ገድሎችን እንደሚፈጽም በታሪክም አስመስክሯል፡፡ ከጦር ሜዳ ውሎ ጀምሮ በተለያዩ ዘርፎች አንቱ የተባሉ አኩሪ ዜጎች የወጡት ከዚህ ታላቅ ሕዝብ ውስጥ ነው፡፡ ይህንን ሕዝብ መምራት አለመቻል ያመጣውንም ጣጣ በሚገባ ለማየት ተችሏል፡፡ አሁን ኢትዮጵያዊነት ማሸነፍ አለበት መባል ይኖርበታል፡፡ ኢሕአዴግ ሊቀመንበሩን ሲመርጥና ወደ ፓርላማ አምርቶ ተተኪውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሰይም፣ ከጎራ አስተሳሰብና ቡድንተኝነት በላይ አገር የምትባል የጋራ ቤት እንዳለች አፅንኦት መስጠት ይገባል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን በአስተሳሰብ ብንለያይ እንኳ ለዚህች ታላቅ አገር ህልውና ስንል፣ በዚህ ታሪካዊ ወቅት የጋራ የሆነ ነገር ሊኖረን የግድ ይላል፡፡ ለአገሩ የሚቆረቆርና ቅን የሆነ ዜጋ ይህንን አስተዋይና ተምሳሌታዊ ሕዝብ አይዘነጋም፡፡ ይህ አገሩን ከምንም ነገር በላይ የሚያስቀድም ሕዝብ ደግሞ ሊከበርም ሊደመጥም ይገባል፡፡ ሕዝብ በዚህች አገር ከምንም ነገር በላይ መሆን አለበት! ከተተኪው መሪ ምርጫ በላይ የተመሪ ሕዝብ ጉዳይ ማሳሰብ አለበት! 

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ለካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ስድስት የቦርድ አባላት ተሾሙ

  ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የቦርድ ሰብሳቢ ሆነዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

  የትጥቅ  መፍታት ሒደትና የሰላም እንቅፋቶች

  የትግራይ ተራሮች ከጦር መሣሪያ ጩኸት የተገላገሉ ይመስላል፡፡ በየምሽጉ አድፍጠው...

  በሙስና የተጠረጠሩ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ነው

  ብሔራዊ ፀረ ሙስና ኮሚቴ በክልሎችም ሊቋቋም ነው በቅርቡ ተቋቁሞ ወደ...

  የኢንሹራንስ ዘርፉን የሚመራና የሚቆጣጠር ራሱን የቻለ ተቋም የመመሥረት ጥያቄ ተቀባይነት አገኘ

  የኢንሹራንስ (መድን) ዘርፍን የመቆጣጠርና የመከታተል ኃላፊነት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...

  ዘንድሮ የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተናን በበይነ መረብ ለማድረግ ዝግጅት መጀመሩ ተገለጸ

  በሁሉም መደበኛና መደበኛ ባልሆኑ መርሐ ግብሮች የሚመረቁ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ምሁራንና ልሂቃን ከአስተዋዩ ሕዝብ ታሪክ ተማሩ!

  አገራዊ ምክክሩን ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ባለበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት፣ የኢትዮጵያን የትናንት ትውልዶችና የዛሬውን ይዘት መመርመር አስፈላጊ ነው፡፡ ያለፉት ዘመናት ትውልዶች ለአገራቸው የነበራቸው ቀናዒነት የፈለቀበት...

  ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ ዋጋ ያስከፍላል!

  በኳታር እየተከናወነ ያለው የዓለም ዋንጫ በእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ ያልተጠበቁ ማራኪ ቴክኒኮችንና ታክቲኮችን ከአስገራሚ ውጤቶች ጋር እያስኮመኮመ፣ ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎታና ዝና ላይ ተመሥርቶ...

  መንግሥት ለአገር የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ያዳምጥ!

  በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን የማዳመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሥራውን ሲያከናውንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃው በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ...