‹‹መያዣ አውጥተን እያፈላለግነው ነው›› ፖሊስ
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሰያን ደብር ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ውስጥ፣ በአካባቢው የተመደበ ፖሊስ አርሶ አደሩን ገድሎ መሰወሩን የአካባቢው ነዋሪዎች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡
ሟች አርሶ አደር ጌቱ ዘውገ የሚባል የ27 ዓመት ወጣት መሆኑን የገለጹት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ለመሞቱ ምክንያቱ የሆነው ጥቅምት 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ከአንድ ሌላ አርሶ አደር ጋር በተፈጠረ አለመግባባት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የተጋጩበት ምክንያት ባይታወቅም ሟች አቶ ጌቱ ከአንድ የአካባቢው ሰው ጋር ሲጣላ የአካባቢው ነዋሪዎች ገላግለዋቸው ወደየቤታቸው የሄዱ ቢሆንም፣ በአካባቢው ግጭት እንደነበር ሪፖርት የደረሰው ተጠርጣሪ ምክትል ሳጅን ግርማ ብርሃኑ፣ ወደ ሟች ቤት መምጣቱን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡ ተጠርጣሪው ምክትል ሳጅን ግርማ ሟችን ይጠራና ወደ ፖሊስ ጣቢያ ይዞት ለመሄድ በመነጋገር ላይ እያሉ ሌሎች ሁለት ፖሊሶች ይደርሳሉ፡፡ አንዱ ፖሊስ ሟች ላይ ድብደባ እየፈጸመበት እያለ፣ ምክትል ሳጅኑ በያዘው ክላሽኒኮቭ ጠመንጃ ተኩሶ እንደገደለው የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል፡፡
በወቅቱ በተፈጠረው ግርግር ተጠርጣሪውን ማንም ሊይዘው እንዳልቻለና ወደ ላይ እየተኮሰ ከአካባቢው መሰወሩን የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ በመተባበር በሟች ላይ ድብደባ የፈጸመበት ሌላው ፖሊስ መያዝና በሕግ መጠየቅ ሲገባው፣ ከአካባቢው ዞር ተደርጎ ሌላ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር መመደቡ የአካባቢውን ነዋሪዎች እንዳስቆጣ ተናግረዋል፡፡ ሟች በቅርቡ ትዳር የያዘ መሆኑንና ቤተሰቡን እንደሚረዳ፣ በአካባቢው ተወዳጅ ወጣት አርሶ አደር እንደነበር የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፣ በቤተሰቦቹ ፊት በጠራራ ፀሐይ ገድሎት የተሰወረውን የፖሊስ ባልደረባ የክልሉና የፌዴራል መንግሥት ለሕግ እንዲያቀርቡት ጠይቀዋል፡፡
በአርሶ አደሩ ላይ ተፈጽሟል ስለተባለው የግድያ ወንጀል ማብራርያ እንዲሰጡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደነባ ወረዳ ፖሊስ መምርያ ኃላፊ ኢንስፔክተር መስፍን ደጉ ግድያው መፈጸሙን አረጋግጠዋል፡፡ ወንጀሉ እንደተፈጸመና ተጠርጣሪው ምክትል ሳጅን ግርማ ብርሃኑ ግን እንዳልተያዘ የገለጹት የመምርያ ኃላፊው፣ ፖሊስ ምርመራውን ጨርሶ መያዣ በማውጣት ተጠርጣሪውን ለመያዝ እየሠራ መሆኑንና ከኅብረተሰቡ ጋር ተባብረው በቅርቡ በቁጥጥር ሥር እንደሚያውሉት ተናግረዋል፡፡
ግድያው የተፈጸመው በሁለት ግለሰቦች መካከል በተነሳ ፀብ ምክንያት መሆኑን በተደረገው ምርመራ መረጋገጡን የገለጹት ኢንስፔክተሩ፣ ሟች ለሕግ አልገዛም በማለት በፖሊሶች ላይ ዕርምጃ ሊወስድ ሲል ግድያው ሊፈጸም እንደቻለ መረጃ ማግኘታቸውንም ጠቁመዋል፡፡
የአካባቢው ፖሊስና ነዋሪዎች ተስማምተውና ተከባብረው እንደሚኖሩ የገለጹት የመምርያ ኃላፊው፣ አንዳንድ ጊዜ ሳይታሰብ ወንጀል የሚፈጸም በመሆኑ ፈጻሚውን በሕግ ፊት ማቅረብ ግድ ስለሆነ፣ የተቻለውን ሁሉ በማድረግ ተጠርጣሪውን ይዞ ለማቅረብ አስፈላጊው ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡