– በተጠረጠሩበት ሐሰተኛ ሰነድ መጠቀም ወንጀል ተጨማሪ ጊዜ ተጠየቀባቸው
የእሳቸው ተከታይና የሚሏቸውን ነገር ሁሉ ያደርጉ የነበሩን ግለሰብ ቤት በማሸጥና ገንዘቡንም እንዲፀለይበት በማለት ወስደዋል ተብለው ተጠርጥረው የታሰሩት መምህር ግርማ ወንድሙ፣ በ50,000 ብር ዋስ እንዲለቀቁ ፍርድ ቤት በሰጠው ትዕዛዝ ላይ ፖሊስ ይግባኝ ማለቱ ታወቀ፡፡
የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ወንጀል ችሎት ለመምህር ግርማ የፈቀደውን የ50,000 ብር ዋስትና የተቃወመው ፖሊስ፣ ቅሬታውን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ወንጀል ችሎት አቅርቧል፡፡ ፖሊስ ባቀረበው መከራከሪያ ነጥብ ላይ ብይን ለመስጠት ፍርድ ቤቱ ለኅዳር 13 ቀን 2008 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ተጠርጣሪው ሐሰተኛ ሰነድ መጠቀማቸውን ገልጾ ፖሊስ ባቀረበው ክስ ምክንያት መምህር ግርማ ኅዳር 3 ቀን 2008 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው የነበረ ሲሆን፣ እሳቸው ከቤተክህነት እንደተሰጣቸው የገለጹት ሰነድ በፎረንሲክ ተመርምሮ ሐሰተኛ መሆኑን እንዳረጋገጠ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ሌላ ተጨማሪ የሚመረመር ሰነድ እንዳለውና ተጨማሪ ሰነድ ሰጥተዋል የተባሉት የቤተ ክርስቲያን አባት በአገር ውስጥ አለመኖራቸውን በማስታወቅ፣ ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡
የመምህር ግርማ ጠበቆች ፖሊስ ያቀረበውን ማመልከቻና ተጨማሪ ቀናት በመቃወም፣ ደንበኛቸው በዋስ ተለቀው ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የጠበቆቹን ማመልከቻ በማለፍ የሰባት ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ለፖሊስ ፈቅዷል፡፡