Wednesday, April 17, 2024

የፖለቲካ አለመረጋጋቱ ዳፋ በኢኮኖሚው ላይ ውስብስብ ችግር እንዳያመጣ ሥጋት ፈጥሯል

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ በጥቅምት ወር 2007 ዓ.ም.፣ ሰፊ የሆነውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በመጣበት ዕድገት ለማስቀጠል ከ700 ቢሊዮን ብር በላይ ኢንቨስትመንት ያስፈልጋል ብለው ነበር፡፡

ከሰባት ዓመት በፊት የአገሪቱ አጠቃላይ ምርት (GDP) 370 ቢሊዮን ብር ብቻ እንደነበር ያስታወሱት የባንኩ ገዥ፣ በወቅቱ ደግሞ 1.8 ትሪሊዮን ብር መድረሱን ጠቁመው ነበር፡፡ በዚህ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የአገሪቱ ኢኮኖሚ ለማስቀጠልም የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ከ35 እስከ 40 በመቶ የሚመጥን አዲስ ኢንቨስትመንት መፍጠር እንደሚገባው ያወሳሉ፡፡

የተጠቀሰውን መጠን ኢንቨስትመንት ፋይናንስ ለማድረግ የውጭ ምንዛሪ እንደሚጠይቅ፣ ይህንን የውጭ ምንዛሪ ማቅረብ ካልተቻለ ኢኮኖሚው ሊቆም እንደሚችል ተናግረው ነበር፡፡

በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ የብር ምንዛሪ ተመን እንዲቀንስ የመደረጉ አንደኛው ምክንያት ከዚሁ ጋር የተገናኘ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ከዚህ የብር ምንዛሪ ተመን ለውጥ ጋር ተያይዞ ሊፈጠር የሚችለው አሉታዊ ተፅዕኖ የምርቶች ዋጋ ግሽበት መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ በተለይ ገና ከድርቅ የወጣ ኢኮኖሚ መሆኑንና በፖለቲካ አለመረጋጋት የተከበበ እንደሆነ፣ የዋጋ ግሽበቱ የሸማቾችን ኑሮ በማቃወስ የፖለቲካ አለመረጋጋቱን እንዳያጦዘው በወቅቱ ሥጋታቸውን የገለጹ ነበሩ፡፡

አቶ ተክለ ወልድ የምርቶች ዋጋ መናር የምንዛሪ ለውጥን ተከትሎ የሚመጣ እንደሆነ ቢታወቅም፣ መንግሥት በጥናት ላይ ተመሥርቶ ተግባራዊ የሚያደርገው በመሆኑ የዋጋ ግሽበት ግፊት እንደማይኖረው በወቅቱ ተናግረው ነበር፡፡

በተለይ በ2010 ዓ.ም. ከፍተኛ የግብርና ምርት የሚገኝበት በመሆኑና መንግሥትም የመሠረታዊ ፍጆታ ሸቀጦች የሆኑትን እንደ ስኳር፣ ዘይትና ስንዴ ከውጭ እየገዛ ማከፋፈሉን የሚቀጥል በመሆኑ በምግብ ሸቀጦች ረገድ የሚፈጠር የዋጋ ንረት እንደማይኖር ተናግረው ነበር፡፡ አቶ ተክለ ወልድ ይህንን ይበሉ እንጂ የብር የመግዛት አቅም በአንድ ጊዜ በ15 በመቶ እንዲቀንስ በመደረጉ ምክንያት ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ከወር ወደ ወር እየተመዘገበ ይገኛል፡፡

ለምሳሌ የብር የመግዛት አቅም ከጥቅምት ወር ጀምሮ እንዲቀንስ ከተደረገ በኋላ፣ በኅዳር ወር ከፍተኛ የዋጋ ንረት ተመዝግቧል፡፡ በጥቅምት ወር የነበረው አጠቃላይ ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት 12.2 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ በኅዳር ወር የዋጋ ግሽበቱ 13.6 በመቶ ተመዝግቧል፡፡ ለዋጋ ግሽበቱ ዋነኛ ምክንያት በኅዳር ወር የነበረው የምግብ ነክ የዋጋ ንረት በ18.1 በመቶ ከፍ በማለቱ መሆኑን፣ ከኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የዋጋ ግሽበቱ በዚህ አላበቃም፡፡ በየካቲት ወር 2010 ዓ.ም. 15.6 በመቶ ደርሷል፡፡ በየካቲት ወር ለታየው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት መንስዔው የምግብ ነክ ሸቀጦች ዋጋ በ20.9 በመቶ ጭማሪ በማሳየቱ መሆኑን የስታትስቲክስ ኤጀንሲ ሪፖርት ያሳያል፡፡

‹‹በየካቲት ወር ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር ከእህል ክፍሎች አብዛኞቹ ጭማሪ አሳይተዋል፡፡ በተጨማሪም የጥራጥሬ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋ በመጠኑ ጨምሯል፡፡ በየካቲት ወር የበርበሬና ቅመማ ቅመም ዋጋ በአንድ ወር ውስጥ ባልተለመደ ሁኔታ እጥፍ ጭማሪ በማሳየቱ፣ ለዋጋ ግሽበቱ መጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፤›› ሲል የኤጀንሲው የዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ ያሳያል፡፡

በመሆኑም የብር የመግዛት አቅም እንዲዳከም ሲደረግ በአገሪቱ ከፍተኛ ምርት መመረቱን ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን አቶ ተክለ ወልድ ቢገልጹም፣ እየሆነ ያለው ግን በተቃራኒው ነው፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያዎች የውጭ ምንዛሪ ተመን ለውጥ ሲደረግ የዋጋ ግሽበት መከሰቱ የማይቀር መሆኑን ጠቅሰው፣ አሁን እየታየ ያለው ግን ከምንዛሪ ተመኑ ጋር ቀጥታ ግንኙነት የሌላቸው እንደ ቅመማ ቅመምና ጥራጥሬ መሆናቸው ሌላ ምክንያት ሊኖረው እንደሚችል ጥርጣሬ ያስነሳል ይላሉ፡፡

ምናልባትም ከፖለቲካ አለመረጋጋቱ ጋር ተያይዞ በሰፊው ለረዥም ጊዜ ፍጆታ የሚያገለግል ግዥ ኅብረተሰቡ በመፈጸሙ በጫና የመጣ ከፍተኛ ፍላጎት በመከሰቱ፣ የዋጋ ግሽበቱ ተከትሎ ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ፡፡

በሌላ በኩል ከዚሁ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በዋናነት በኦሮሚያ ክልል የገበያ ማቆም አድማና የትራንስፖርት አድማ በተደጋጋሚ እየተጠራ በመሆኑ ሳቢያ የአቅርቦት እጥረት ይፈጠራል በሚል ግምት (Speculation)፣ ነጋዴዎች የጨመሩት ዋጋ ሊሆን እንደሚችል ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ የኢኮኖሚ ባለሙያ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የሲሚንቶ አምራች ኩባንያዎች የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ ማቀዳቸውን፣ ለዚህ ምክንያታቸው የውጭ ምንዛሪና ለውጥ ዋነኛ ግብዓት የሆነው የድንጋይ ከሰል ዋጋ መጨመር ቢሆንም፣ ከትራንስፖርት አድማው ጋር በተገናኘ የምርት እጥረት ሳይኖር ሲሚንቶ ቸርቻሪዎች የሲሚንቶ ዋጋ ከፋብሪካው ሳይጨምር እነሱ መጨመራቸውን በዋቢነት ያነሳሉ፡፡ ይህንን አስመልክቶ ሪፖርተር ባለፈው ሳምንት ዕትሙ ያወጣውን ዘገባ በማስረጃነት ይጠቅሳሉ፡፡

ፓርላማው በየካቲት ወር 2010 ዓ.ም. ለዕረፍት ከመበተኑ በፊት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ያቀረቡት የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሞገስ ባልቻ የፖለቲካ አለመረጋጋቱን ምክንያት በማድረግ ግብር ያለመክፈል፣ ኪሳራ ወይም ዜሮ ሪፖርት የማድረግ ሰፊ ተግባር መስተዋሉን፣ በዚህም የተነሳ የመንግሥት ገቢ መቀነሱን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም ከፍተኛ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ እየተስተዋለ መሆኑን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በተለይ የወጪ ኮንትሮባንድ በተለይም የገንዘብ ዝውውር በ200 በመቶ መጨመሩን ገልጸዋል፡፡

ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት በተስተዋለበት የአገሪቱ ገበያ ውስጥ ከፍተኛ የዶላር ግዥ እየተስተዋለም ይገኛል፡፡ በአገሪቱ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ በባንክና በጥቁር የዶላር ገበያ መካከል ያለው ልዩነት ሰባት ብር መድረሱን ሪፖርተር ያነጋገራቸው ለገበያው ቅርበት ያላቸው ይናገራሉ፡፡

የአገሮችንና የንግድ ኮርፖሬሽኖችን ኢኮኖሚያዊ ጤናማነትና ሥጋት ትንተና በመሥራት የሚታወቀው ሙዲ (Moody) የተባለ ተንታኝ ኩባንያ ባለፈው ወር የኢትዮጵያ ኢኮኖሚን ጤናማነት አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት፣ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ጤናማነት በሌሎች ፖለቲካዊ ምክንያቶች ካልተቀለበሰ በስተቀር የተረጋጋ (B1) እንደሆነ አመልክቷል፡፡

በተረጋጋው ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ ከአገሪቱ ኢንቨስትመንት ይበልጥ እንደሚደብርና ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትም እንደሚጨምር፣ በተመሳሳይም የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚሻሻል ይተነብያል፡፡

በዚህ የተነሳም የአገሪቱ የውጭ ብድር የመሸከም አቅም ጠንካራ እንደሚሆን ይገልጻል፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን ሊቀለበስ የሚችለው አገሪቱ የውጭ ብድር መበደሯን ከተገመተው በላይ የምትቀጥል ከሆነ ከምታመነጨው የዶላር ገቢ ጋር ሊጣጣም የማይችል በመሆኑ፣ የአገሪቱን የውጭ ዕዳ ሸክም ከፍተኛ እንደሚያደርገው ይገልጻል፡፡

በተለይ የፖለቲካ ውጥረቱ ሙዲ እንደሚገምተው በፍጥነት የማይረጋጋ ከሆነ፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ፍላጎትና ዕድገት በመግታት የአገሪቱን የውጭ ዕዳ ሸክም እንደሚያከብደው ነው፡፡

ሙዲ (Moody) ይህንን ሪፖርት ካወጣ በኋላ በኢትዮጵያ ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፡፡ ይህም የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉን እንደሚጎዳው ቀድሞ በነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተስተዋለውና በመንግሥትም ከተረጋገጠው መረዳት ይቻላል፡፡

መፍትሔው ምንድነው?

የፊሊንስቶን ሪል ስቴት ባለቤት ፀደቀ ይሁኔ (ኢንጂነር) አሁን ያለውን የፖለቲካ አለመረጋጋት የፈጠረው ኢኮኖሚያዊ ችግር እንደሆነ ያምናሉ፡፡ በመሆኑም መፍትሔው ኢኮኖሚያዊ መሆን አለበት በማለት ያሳስባሉ፡፡

በኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች የተፈጠረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ተመልሶ በኢኮኖሚው ላይ ያወሳሰበው ችግር እስካሁን አለመታየቱንም ይገልጻሉ፡፡ ይሁን እንጂ መሠረታዊ ችግሮቹን በፍጥነት በመቅረፍ መፍትሔ ማምጣት ካልተቻለ፣ ከዚህ የበለጠ የፖለቲካ ቀውስ ሊፈጠር እንደሚችል በመግለጽ ሥጋታቸውን ይናገራሉ፡፡

በየዓመቱ 600 ሺሕ ወጣቶች ከዩኒቨርሲቲ እየተመረቁ መሆናቸውን በማንሳት የወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ካልተመለሰ ከፍተኛ ቀውስ የመፈጠር ዕድሉ የከፋ መሆኑን የሚገልጹት ደግሞ፣ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ተንታኝና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ቆስጠንጢኖስ በርሄ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

‹‹ተስፋ ያጣ ወጣት በማንኛውም ነገር ሊታለልና የማንኛውም ነገር አክራሪ (ራዲካላይዝ) ሊደረግ ይችለል፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን ለሪፖርተር ሰጥተዋል፡፡ አሁን ባለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ማለትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሌሉበት የመንግሥት መዋቅር ሙሉ በሙሉ እየሠራ ነው ብለው እንደማያምኑ የሚናገሩት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፣ የወቅቱን የፖለቲካ ውዝግብ በፍጥነት በመፍታት ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪፎርሞችን እንዲያካሂድ ሊደረግ እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡

የውጭ ኢንቨስትመንት ወደ ኢትዮጵያ በስፋት እንዲገባ ማነቆ የሆኑ አሠራሮችን መቅረፍ፣ በብድርና በዕርዳታ ከሚገኝ የውጭ ምንዛሪ ገቢ መላቀቅ፣ የፋይናንስ ሴክተሩን ማጎልበት፣ የውጭ ባንኮች መግባት ካለባቸውም ይህንኑ አስመልክቶ ውይይት መጀመር እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -