Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኦሮሞን ሕዝብ ነፃ ለማውጣትና ክልሉን ለመገንጠል ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ 29 ተጠርጣሪዎች ተከሰሱ

የኦሮሞን ሕዝብ ነፃ ለማውጣትና ክልሉን ለመገንጠል ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ 29 ተጠርጣሪዎች ተከሰሱ

ቀን:

– ባለሥልጣናት አየር መንገድና ኤምባሲዎች ዒላማዎቻቸው ነበሩ ተብሏል

የኦሮሞን ሕዝብ ነፃ ለማውጣትና ክልሉን ከፌዴሬሽኑ ለመገንጠል፣ በአዲስ አበባ ከተማና በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል የተባሉ 29 ተጠርጣሪዎች፣ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 14ኛ እና 19ኛ ወንጀል ችሎቶች ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተባቸው ተጠርጣሪዎች የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አባላት ሆነው፣ ከድርጅቱ አመራሮች ተልዕኮ በመቀበልና ዓላማውን ለማስፈጸም በአገሪቱ መንግሥት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር፣ ኅብረተሰቡን ለማስፈራራት፣ በአዲስ አበባ ከተማና በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የሽብር ተግባር ወንጀል ለመፈጸም ሲዘጋጁ ሲንቀሳቀሱ በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን፣ የተመሠረተባቸው ክስ ያስረዳል፡፡

በኤምባሲዎችና በአየር መንገዱ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ከኬንያ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከሦስት ግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን ሞጆ ከተማ ውስጥ በ2005 ዓ.ም. ቤት ተከራይቶ ለሦስት ወራት ሲንቀሳቀስ ነበር የተባለው ተከሳሽ፣ በቅጽል ስሙ ጫላ ኢብራሂም የሚባለው ቦሰት በቀለ ሮባ፣ ከኦነግ አመራሮች የተሰጠውን ተልዕኮ ለመፈጸም ሲንቀሳቀስ ሰኔ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ አካባቢ በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር መዋሉን የዓቃቤ ሕግ ክስ ይገልጻል፡፡

ነዋሪነቱ ኬንያ ናይሮቢ የሆነውና አብደላ መሐመድ የተባለው ሌላው ተከሳሽ ደግሞ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትን እንዲገድልና በመንግሥት ተቋማት ላይ ጥቃት እንዲፈጽም ከኦነግ አመራሮች የተሰጠውን ትዕዛዝ ለመፈጸም፣ ከኬንያ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ወደ አዳማ ለመሄድ በጉዞ ላይ እያለ፣ ሞጆ ከተማ በሰኔ ወር 2007 ዓ.ም. በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር መዋሉን ክሱ ያስረዳል፡፡

ራሳቸውን በሴል በማደራጀትና የሥራ ክፍፍል በማድረግ ምዕራብ ሸዋ ዞን አደአ በርጋ ወረዳ ኦሎንኮሚ አካባቢ በሚገኘው ጫካ ውስጥ ለሚገኘው የኦነግ ቡድን፣ የስንቅና ትጥቅ ድጋፍ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ፣ የመንግሥት ሠራተኞችን ለመግደል ሲያሴሩና ለግድያ በተመረጡ ሠራተኞች መኖሪያ ቤትም ሲመላለሱ ነበር ከተባሉት ውስጥ በቅጽል ስሙ ማሞ የሚባለው ኦላና ከበደ ደምሴ፣ መገርሳ ፈቃዱ፣ አርገሞሲሳ ሌንዲሳ፣ ምክትል ሳጅን መሠረት ኦቡማ፣ አብዲሳ ኢፋና ዋርደር ተመስገን ፀጋዬ የተባሉትን ተከሳሾች ዓቃቤ ሕግ በቀደምትነት ጠቅሷል፡፡

ተከሳሾቹ በኬንያና በተለያዩ አካባቢዎች ሥልጠና በመውሰድ የጦር መሣሪያ አፈታትና አገጣጠም፣ ቦምብ ውርወራና ዒላማ ተኩስ በመሠልጠን፣ ሌሎችን በመመልመል፣ ሰላማዊ ሰው በመምሰልና ለሕዝቡ ተቆርቋሪ በመሆን፣ ኅብረተሰቡ አምስት አምስት ብር መዋጮ እንዲከፍል በመቀስቀስ፣ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመገርሰስ፣ በሴል በመደራጀት እየተንቀሳቀሱ እንደነበር የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

የኦነግን ተልዕኮ በመቀበል የአገሪቱን ሕዝቦች አንድነት ለማፈራረስ፣ የኦሮሞን ሕዝብ ነፃ ለማውጣትና ክልሉን ከፌዴሬሽን ለመገንጠል በሚል ዓላማ፣ የሽብር ተግባር ወንጀል ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ በ2007 ዓ.ም. በተለያየ ጊዜና ቦታ በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ውለው፣ ጥቅምት 24 እና 25 ቀን 2008 ዓ.ም. ክስ የተመሠረተባቸው 29 ተጠርጣሪዎች ናቸው፡፡ ተጠርጣሪ ተከሳሾች ቦሰት በቀለ ሮባ፣ አብደላ መሐመድ፣ አብዲ ዋቆ፣ ፋንታሌ ሮባ፣ ቦሩ ሀዌ፣ ጄሎ ፈንታሌ፣ ሁሴን አዲ፣ ሻሾ አድማሱ፣ ኦላና ከበደ፣ ወልዴ ሞቱማ፣ መገርሳ ፈቃዱ፣ አርገሞ ሲሳ ሌንጂሳ፣ ምክትል ሳጅን መሠረት ኦቡማ፣ አብዲሳ ኢፋ፣ ዋርደር ተመስገን ፀጋዬ፣ ተመስገን ወርዶፋ፣ ቦኪ እሸቱ፣ ብርሃኑ ቦኪ፣ ማሙሽ ቦኪ፣ ፍቃዱ አዱኛ፣ መኮንን ዘውዴ፣ ወርቁ ጉርሙ፣ ገረሙ አዱኛ፣ ደረጄ ታዬ፣ ጃለታ ሰንዳፋ፣ ላቀው ሮቤ፣ እንግዳ ቁሲ፣ ቶሽሌ ተስፋና ታደሰ ዓለሙ መሆናቸውን የዓቃቤ ክስ ይዘረዝራል፡፡       

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...