Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊኦርኪድ አሸናፊ የሆነበት የ42 ሚሊዮን ብር የፍትሐ ብሔር ጉዳይ ለሰበር ያስቀርባል ተባለ

ኦርኪድ አሸናፊ የሆነበት የ42 ሚሊዮን ብር የፍትሐ ብሔር ጉዳይ ለሰበር ያስቀርባል ተባለ

ቀን:

የጀርመን ዜግነት ባላቸው አቶ ዮናስ ካሳሁንና በኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መካከል በነበረው የ42 ሚሊዮን ብር የፍትሐ ብሔር ክስ ክርክር፣ ኦርኪድ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረበው ይግባኝ ተቀባይነት አግኝቶ የነበረ ቢሆንም፣ መሠረታዊ የሕግ ስህተት እንደተፈጸመ ተገልጾ ጉዳዩ ወደ ሰበር ችሎት በመሄዱ፣ ችሎቱ ጥቅምት 23 ቀን 2008 ዓ.ም. እንደሚያስቀርብ አስታውቆ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

የፍትሐ ብሔር ክሱ በሁለቱ ተከራካሪ ወገኖች መካከል የተጀመረው እ.ኤ.አ. ጁላይ 9 ቀን 2011 በተከበረው የደቡብ ሱዳን የነፃነት ቀን በዓል ጋር በተገናኘ ነው፡፡ አቶ ዮናስ በኦርኪድ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ተፈርሞ መስከረም 9 ቀን 2004 ዓ.ም. የተሰጣቸው የ42 ሚሊዮን ብር (1.7 ሚሊዮን ዩሮ) መተማመኛ ሰነድ ቃል የተገባላቸው ሊተገበር ባለመቻሉ ክስ በመመሥረታቸው ነው፡፡ የመጀመሪያውን የክስ ሒደት የመረመረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ የሰነድ ማስረጃዎችን በፌዴራል ፖሊስ ፎረንሲክ ምርመራ ማዕከል አስመርምሮ፣ ሰነዱ በኦርኪድ ምክትል ሥራ አስኪያጅ መፈረሙንና ማኅተሙም የኦርኪድ መሆኑን በማረጋገጥ፣ ኦርኪድ ክፍያውን ከነወለዱ እንዲፈጽም ፍርድ መስጠቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ የሥር ፍርድ ቤት ማስረጃውን በደንብ እንዳልመረመረለት በመግለጽ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ያለው ኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ፣ ያቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት በማግኘቱ ሰፊ ክርክር ተደርጐበት፣ በሥር ፍርድ ቤት ለአቶ ዮናስ የተወሰነው 42 ሚሊዮን ብር የፍትሐ ብሔር ፍርድ፣ ሐምሌ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ውድቅ ተደርጐ ኦርኪድ በነፃ ተሰናብቶ ነበር፡፡

አቶ ዮናስ በጠበቃቸው አቶ አመሐ መኮንን አማካይነት ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጠውን ፍርድ በመቃወም ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ‹‹መሠረታዊ የሕግ ጥሰት ተፈጽሟል›› በማለት፣ 19 ገጽ የይግባኝ አቤቱታ አቅርበው እንደነበር ሰነዶች ያመለክታሉ፡፡

ኦርኪድ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብሎ አሸናፊ የሆነባቸው በከፍተኛው ፍርድ ቤት ያላነሳቸው አዳዲስ ክርክሮች መሆናቸውን ጠበቃ አመሐ ጠቅሰዋል፡፡ ኦርኪድ የመተማመኛ ሰነዱ በፎረንሲክ ተመርምሮ ትክክለኛነቱ ቢረጋገጥም የፎረንሲክ ምርመራ ውጤት አስተማማኝ ማስረጃ አለመሆኑን ጠቅሶ በሌላ ዘዴ እንዲጣራለት ያቀረበው አቤቱታ መታለፉን፣ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሰጠው ትርጉም ስህተት እንዳለው፣ በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት የእህት ኩባንያ ጽንሰ ሐሳብ የለም ብሎ የተከራከረው እንደታለፈበት ገልጸዋል፡፡ የሥር ፍርድ ቤት ጉዳዩን የማየት ሥረ ነገር ሥልጣን እንደሌለው ያቀረበው ደግሞ አዲስ ነው፡፡

አቶ አመሐ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ባቀረቡዋቸው አቤቱታዎች በሰጡት ምላሽ፣ ኦርኪድ እህት ኩባንያውን ሶልዳን ኢንተርናሽናልን ወክሎ ‹‹እከፍላለሁ›› ብሎ ለደንበኛቸው በሰጣቸው መተማመኛ ሰነድ አማካይነት ሊከፍላቸው እንደሚገባ፣ ሰነዱ በመንግሥታዊው ተቋም ፎረንሲክ ተመርምሮ የተረጋገጠ በመሆኑ ዳግመኛ ምርመራ እንደማያስፈልገው፣ ለበዓሉ ከጀርመን ተገዝተው የቀረቡ ዕቃዎች በኩባንያዎቹ ደብዳቤዎች በደጋፊ ማስረጃነት የቀረቡ መሆናቸውንና በራሳቸው ብቻ አስተማማኝ መሆናቸውን፣ በመተማመኛ ሰነዱ ላይ ያሉትን ቃላት በሰው ይረጋገጥልኝ ማለት የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 2005 እና 2006 ድንጋጌዎችን የሚጥስ በመሆኑና ሌሎችንም በመጥቀስ ተቃውመዋል፡፡ ሁለቱም ወገኖች ሰፊ ክርክር አድርገዋል፡፡

ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአቶ ዮናስና በኦርኪድ መካከል ያለው ክርክር ነጥሮ እንዲወጣ፣ ‹‹መተማመኛ ሰነዱ ሊገደድ ይገባል ወይስ አይገባም?›› የሚለውን ጭብጥ መያዝ ሲገባው፣ ሰፊና ከዋናው ሐሳብና ጭብጥ የራቀ ጭብጥ በመያዝ፣ ተገቢ ያልሆነ ፍርድ መስጠቱን ለሰበር ባቀረቡት አቤቱታ ገልጸዋል፡፡ የሥር ፍርድ ቤት በሰፊው ካከራከረ በኋላ፣ አቶ ዮናስ በዝግጅት ላይ የተሳተፉት ከሶልዳን ኢንተርናሽናል ጋር ባደረጉት የንዑስ ሥራ ተቋራጭነት፣ ወይም የጥቅም ተካፋይ ለመሆን በተደረገ የውል ግንኙነት መሆኑን የሚያስረዳ ሰነድ ስለማቅረባቸው፣ ለመተማመኛ ሰነዱ ሦስተኛ ወገን የሆነው የሶልዳንን ዕዳ ኦርኪድ በግዴታ እንዲከፍል ከማድረግ ባለፈ፣ ተክቶ እንዲከፍል መብት እንደማይሰጠውና የኦርኪድ ምክትል ሥራ አስኪያጅ የስጦታ መተማመኛ ሰነድ፣ ከሥልጣናቸውም ሆነ ከማኅበሩ የንግድ ዓላማ ወሰን ውጪ መሆኑን ገልጾ ኦርኪድ ሊከፍል እንደማይችል ፍርድ ሰጥቷል፡፡

ነገር ግን አቶ ዮናስ መሠረታዊ የሕግ ስህተቶች እንደተፈጸሙ ለሰበር ሰሚው ችሎት ባቀረቡት አቤቱታ እንደገለጹት፣ መሠረታዊው ክርክር ኦርኪድ በምክትል ሥራ አስኪያጁ ፈርሞ የሰጠው መተማመኛ ሰነድ፣ ‹‹ሊገደድ ይገባል ወይስ አይገባም›› የሚለው መታየት አለበት፡፡ ምክንያቱም ኦርኪድ ሐሰተኛ ሰነድ ነው ብሎ ተከራክሯል፡፡ በመተማመኛ ሰነዱ ላይ ያረፈው ፊርማና ማኅተም የኦርኪድ ምክትል ሥራ አስኪያጅና የድርጅቱ ማኅተም መሆን አለመሆኑ ሊጣራ ይገባል፡፡ ፎረንሲክ በዚህ ላይ የሰጠው አስተያየት ‹‹ሊስተካከል ይገባል ወይስ አይገባም?›› የሚለው ሊታይ እንደሚገባም ጠቅሰዋል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት፣ ‹‹የመተማመኛ ሰነዱ ተዓማኒነት የለውም›› በማለት ሲወስን በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 2008 ላይ የተደነገገውን በመጣስ መሠረታዊ የሕግ ስህተት መፈጸሙን አመልክተዋል፡፡

ሰበር ሰሚው ችሎት በቅጽ 12 መዝገብ ቁጥር 14981 ላይ የባለሙያ አስተያየት ሊስተባበል የሚችል ማስረጃ መሆኑን የገለጸ ቢሆንም፣ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ግን ‹‹አስተባብሏል ወይስ አላስተባበለም?›› ሳይል የፎረንሲክ የምርመራ ውጤትን ወደ ጐን በመተው ‹‹የሰነድ ማስረጃው ተዓማኒነት የለውም›› በማለት የሰጠው ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት መሆኑን ጠበቃ አመሐ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ሰበር ሰሚ ችሎቱ የፎረንሲክ ባለሙያ የተረጋገጠው የመተማመኛ ሰነድ ያልተስተባበለ በመሆኑ፣ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ እንዲሻርላቸው ጠይቀዋል፡፡

ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ከእሱ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌለውና ‹‹ሰነዱ ትክክለኛ ነው ወይስ በተጭበረበረ መንገድ የተዘጋጀ ነው?›› የሚለውን ለመለየት፣ አቶ ዮናስ በመዝገብ ቁጥር 108335 የኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ አኪኮ ሥዩምን ኢሜል አድራሻ የይለፍ ቃል፣ ባልታወቀ መንገድ በመጠቀም ወንጀል ጥፋተኛ የተባሉበትን መዝገብ በማስረጃነት ተቀብሎ ውሳኔ መስጠቱ፣ መሠረታዊ የሕግ ስህተት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2006 የጽሑፍ ሰነድ በማስረጃነት በሚቀርብበት ጊዜ፤ በጽሑፍ ላይ ስለሰፈሩት ቃላት ተቃራኒ የሆነ የህሊና ግምት ማስረጃ ማቅረብ እንደማይችል በመደንገግ፣ የህሊና ግምት ማስረጃ ተቀባይነት እንደሌለው ማስፈሩን የገለጹት ጠበቃ አመሐ፣ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ይኸንን ድንጋጌ በመተላለፍና በማስረጃ ሥነ-ሕግ (Jurisprudence) መሠረት፣ ሊቀበል የማይገባውን የባህሪ ማስረጃ በመቀበል፣ በህሊና ግምት ላይ ተመሥርቶ የሰጠው ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ‹‹የመተማመኛ ሰነዱ ተዓማኒነት የለውም›› የማለት ድምዳሜ ላይ የደረሰው፣ ሰነዱ ሐሰተኛ ስለመሆኑ ወይም የፎረንሲክ ምርመራ ውጤት ስህተት ያለበት መሆኑን የሚያሳይ ወይም የሚያስተባብል ማስረጃ ቀርቦለት አለመሆኑንም ጠበቃው ገልጸዋል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በማስረጃ ሕግና መርህ መሠረት ፍርድ ቤቱ አግባብነት የሌለውን የባህሪ ማስረጃ በመቀበሉና በአቶ ዮናስ ላይ ከወዲሁ በጐ ያልሆነ አመለካከት በመያዙ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የመተማመኛ ሰነዱ ላይ የሰፈሩትን ፍሬ ነገሮች ከተዋዋዮቹ ፈቃድና ፍላጐት ውጪ በመሄድ ትርጓሜ መስጠቱ፣ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 1733 ላይ የተደነገገውን የሚጣረስና መሠረታዊ የሕግ ስህተት መፈጸሙንም አቶ አመሐ አስረድተዋል፡፡

‹‹1.7 ሚሊዮን ዩሮ እከፍላለሁ›› ከሚለው ቃል ውጪ በመሄድና ከጭብጡ በመራቅ የተሰጠው የመተማመኛ ሰነድ፣ አቶ ዮናስ አገልግሎት የሰጡት ሶልዳን ለተባለው ኩባንያ በመሆኑ፣ የሦስተኛ ወገን የሆነውን የሶልዳን ኢንተርናሽናልን ዕዳ እከፍላለሁ የሚል እንደሆነ ትርጓሜ መስጠቱ የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 1733 ከመተላለፉም ባሻገር፣ ፍርድ ቤቱ በትርጉም ሰበብ አቶ ዮናስና ኦርኪድ ያልተዋዋሉትን አዲስ ውል መፍጠሩ፣ መሠረታዊ የሕግ ስህተት መፈጸሙን እንደሚያስረዳ አብራርተዋል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የኦርኪድን የማስረዳት ሸክም ያላግባብ ወደ አቶ ዮናስ በማዞር፣ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 2019(2) አተረጓጐም ላይ መሠረታዊ የሕግ ስህተት መፈጸሙንም አክለዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የንግድ ሕግ ቁጥር 528 ስለ ሥራ አስኪያጆች ሥልጣን ያሰፈረውንም ድንጋጌ ላይም መሠረታዊ የሕግ ስህተት መፈጸሙን አብራርተዋል፡፡

ይግባኝ ሰሚው ጠቅላይ ፍርድ ቤት የኦርኪድ ምክትል ሥራ አስኪያጅ የፈጸሙት ተግባር ከማኅበሩ ዓላማ ወሰን ውጪ መሆኑን በመግለጽ፣ በተከራካሪ ወገኖች ያልተነሳ አዲስ ጭብጥ መሠረት አድርጐ የሰጠው ውሳኔ፣ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 328(3) መሠረት የሰፈረውን የመሰማት መብትን የጣሰና መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት መሆኑን አቶ አመሐ ገልጸዋል፡፡

ኦርኪድ ከማኅበሩ የንግድ ዓላማ ጋር በማያያዝ በምክትል ሥራ አስኪያጁ የተሰጠውን የዕዳ መተማመኛ በመቃወም በከፍተኛው ፍርድ ቤት ያቀረበው ክርክር ሳይኖር፣ የተሰጠው የዕዳ መተማመኛ ከኦርኪድ የንግድ ዓላማ ውጪ እንደሆነ ተደርጐ በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የተሰጠው ውሳኔ፣ የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 3293ን የሚቃረንና ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 37791 ከሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ጋር የሚጋጭ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በሦስት ዳኞች የተመረመረው አቤቱታ ‹‹ያስቀርባል›› ተብሎ፣ የኦርኪድን መልስና የአቶ ዮናስን የመልስ መልስ ለመስማት በመዝገብ ቤት በኩል እንዲፈጸም ታዞ ለፍርድ ለታኅሳስ 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ተቀጥሯል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...