Monday, July 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዲሱ ምደባ ሒልተን ሆቴልን ወደ ሦስት ኮከብ ዝቅ አደረገው

ተዛማጅ ፅሁፎች

 

– ራዲሰንን ጨምሮ አራት ሆቴሎች አምስት ኮከብ ተብለዋል

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ጋር በመተባበር በዘረጋው የሆቴሎች ደረጃ ምደባ ፕሮግራም መሠረት፣ አንጋፋው ሒልተን አዲስ ሆቴል ወደ ሦስት ኮከብነት ደረጃ ዝቅ አለ፡፡

ሚኒስቴሩ ጥቅምት 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ውጤት መሠረት 68 ሆቴሎች በደረጃ ምደባው ተካተዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 28 ሆቴሎች ከደረጃ በታች ወይም ‹‹ዜሮ ኮከብ›› ሲደረጉ፣ ሸራተን አዲስ፣ ራዲሰን ብሉ፣ ካፒታል ሆቴልና ስፓ እንዲሁም ኢልሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል ባለአምስት ኮከብ ደረጃን እንዳገኙ ይፋ ተደርጓል፡፡ ከዚህ ባሻገር 27 ሆቴሎች መሠረታዊ የደኅንነት፣ የሳኒቴሽንና የኃይጂን አጠባበቅ ሠርቲፊኬቶችን ሊያቀርቡ ባለመቻላቸው፣ ከደረጃ ምዘናው ውጪ መደረጋቸው ተገልጿል፡፡ እንደ ዋቢ ሸበሌና ሐራምቤ ያሉትን ጨምሮ በርካታ ሆቴሎች የደረጃ ውጤት ያላካተታቸው ሆነዋል፡፡ 

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ታደለች ዳለቾና የዓለም ቱሪዝም ድርጅትን የመዛኞች ቡድን የመሩት ጄምስ ማክ ግሬጎር ከሌሎች ኃላፊዎች ጋር በመሆን በሰጡት ማብራሪያ፣ የባለአምስት ኮከብ ደረጃን ያገኙት ሆቴሎች ለደረጃው ከተቀመጡት 2,249 ነጥቦች ውስጥ 80 ከመቶ በማምጣቸው ነው ተብሏል፡፡ ማክ ግሬጎር እንዳብራሩት፣ ምዘናው በዓለም ላይ ያለውን የኮከብ ደረጃ አሰጣጥ የተከተለና የዓለም ባንክ ያዘጋጀው መሥፈርት ነው፡፡

በመመዘኛው መሠረት ከ68ቱ ውስጥ 25 ሆቴሎች ባለሦስት ኮከብ ደረጃን አግኝተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆነው ሒልተን ሆቴል ለመሆን ችሏል፡፡ ይሁንና ሒልተን አምስት ኮከብ ደረጃን እንደያዘ፣ በቅርቡ ሲካሄድ ከነበረው ምዘና አኳያም ደረጃው አራት ኮከብ ደረጃ እንደሆነ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ሚኒስቴሩ ይፋ ባደረገው ውጤት መሠረት ግን ወደ ሦስት አሽቆልቁሏል፡፡ በአገሪቱ በዘመናዊ ሆቴል ሥራ ዓለም አቀፍ ብራንድ ወይም መለያ ይዞ በመምጣት ፈር ቀዳጅ የሆነው ሒልተን በመንግሥት ባለቤትነት የሚተዳደር ሲሆን፣ በሆቴሉ ከተስተናገዱ ትዕይንቶች መካከል ‹‹ሻፍት ኢን አፍሪካ›› የተሰኘው የቆየ ፊልም የተወሰኑ ገቢሮች በሒልተን ውስጥ መቀረፃቸው አይዘነጋም፡፡ ሪፖርተር የሒልተን ሆቴል ሥራ አመራሮችን ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

በአንፃሩ ራዲሰን ብሉ ባለአራት ኮከብ ማግኘቱ ሲገለጽ የቆየ ቢሆንም ባለአምስት ኮከብ ለመሆን የበቃ ሲሆን፣ ሆቴሉ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ባለአራት ኮከብ ደረጃን ይዞ ለመሥራት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ከዚህ ባሻገር ሸራተን ሆቴል ከባለአምስት ኮከብነት ደረጃ በላይ እንደሚገባው በመግለጽ ቅሬታ አቅርቦ ነበር፡፡ ቅሬታውን ተከትሎ ሁለት ጊዜ በተለያዩ መዛኞች ተመሳሳይ ነጥብ በማምጣቱ ከዚህ ቀደም ባገኘው አምስት ኮከብ ደረጃ እንዲወሰን መደረጉን ኃላፊዎቹ ጠቁመዋል፡፡ ግሬጎር እንዳስረዱት ሸራተን የዴሉክስ ደረጃ እንዲሰጠው ከቀረቡለት መመዘኛዎች ውስጥ ማለትም 2,249 ነጥቦች ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ ውጤት ማስመዝገብ ይገባው ነበር፡፡ ይህ ሊሆን ባለመቻሉ ባለአምስት ኮከብ ሆኗል ብለዋል፡፡

በጠቅላላው ከተመዘኑት 68 ሆቴሎች ውስጥ አራት ባለአምስት ኮከብ፣ 13 ባለአራት ኮከብ፣ 25 ባለሦስት ኮበብ፣ 19 ባለሁለት ኮከብ፣ ሰባት ባለአንድ ኮከብ ደረጃን እንደያዙ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ ይጠቁማል፡፡

 በሆቴሎች የደኅንነት ሥርዓት ማለትም በመወጣጫ፣ በመተላለፊያ ኮሪደሮችና በእሳት መከላከያ ቅድመ ጥንቃቄ ሥርዓቶች፣ በማብሰያ ቤት ንፅህናና አያያዝ፣ በመጠቀሚያ ቁሳቁሶች ይዘት፣ በምንጣፍ፣ በአልባሳት፣ በመኝታ ቤት ንፅህናና በሌሎችም 12 ዋና ዋና ክፍሎች የተከፋፈሉ 2,249 መለኪያ ነጥቦች ላይ በመንተራስ ምዘና መደረጉ የተገለጸ ሲሆን፣ አብዛኞቹ ሆቴሎች የሳኒቴሽንና የኃይጅን ችግሮች ታይቶባቸዋል፡፡ በተለይ በወጥ ቤት አካባቢ የሚታዩ መዝረክረኮች ጎልተው መታየታቸውን ግሬጎር አስታውቀዋል፡፡

ከዚህም ሲያልፍ በርካታ ሆቴሎች በባለሙያ ከመመራት ይልቅ በዘመድ አዝማድ እንደሚተዳደሩ ገልጸዋል፡፡  በመጪዎቹ ሦስትና አራት ዓመታት ውስጥ በግንባታ ላይ የሚገኙ ሆቴሎች ሥራ ሲጀምሩ ከአሥር ሺሕ በላይ የሠለጠኑ ባለሙያዎች እንደሚያስፈልጉ የሚገምቱት ግሬጎር፣ ይህንን ያህል ባለሙያ ለሆቴል ኢንዱስትሪው ማቅረብ ስለመቻሉም ሥጋት እንደገባቸው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡  

አዲስ አበባን ጨምሮ በአገሪቱ 400 ሆቴሎችን በኮከብ ደረጃ ለመመዘን የተዘረጋው ፕሮግራም የአዲስ አበባን አጠናቆ ወደ ክልሎች አቅንቷል፡፡ የአማራ፣ የኦሮሚያ፣ የትግራይና የደቡብ ክልሎች ባለኮከብ ሆቴሎች ምዘና እየተካሄደባቸው ነው፡፡ በእነዚህ ክልሎችም ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ አምስት የሚጠበቁ ሆቴሎች በርካታ ሲሆኑ፣ በየክልሉ ያሉ ኢንስፔክተሮችም ከወትሮው በተሻለ ለሆቴሎች የሳኒቴሽን፣ የኃይጂንና የደኅንነት ሥርዓቶች ትኩረት መስጠት እንደጀመሩ ግሬጎር ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ 

መንግሥት የተገኘው ውጤት ሊያስከትል የሚችለው ተፅዕኖ ተመልክቷል ወይ? ከውጤቱ በመነሳት ምዘናው የተካሄደበት ወቅት ትክክለኛው ጊዜ ነው ወይ? በማለት ሪፖርተር ለኃላፊዎቹ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ወይዘሮ ታደለች ሲመልሱ ውጤቱ አዎንታዊ ተፅዕኖ እንዳለውና የአገሪቱን የቱሪዝም ገጽታ እንደሚያጎላው አስረድተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ለበርካታ ዓመታት ሳይቀር በቆየውና ጊዜው ያለፈበትን የደረጃ መመዘኛ በመቀየር አዲስ የደረጃ አሰጣጥ እንዲካሄድ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ባወጣው ደንብ መሠረት፣ አዲስ የደረጃ ምዘና መስጫ መሥፈርት ማዘጋጀት በማስፈለጉ ያንን መተካት ጊዜው እንደሚጠይቅ አብራርተዋል፡፡ ይሁንና ሆቴሎች የደረጃ አሰጣጡ ገበያ እንዳያሳጣቸውና ኪሳራ እንዳያስከትልባቸው በመሥጋት፣ መንግሥት በጥንቃቄ እንዲተገብረውና ጊዜ እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ መቆየታቸውም ይታወሳል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከዓለም ቱሪዝም ድርጅት ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት ለሦስት ዓመታት የሚቆይ ትብብር በሁለቱ መካከል የተደረሰ ሲሆን፣ የድርጅቱ ባለሙያዎች በየዓመቱ ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ የሆቴሎችን ደረጃ እንደሚገመግሙ ስምምነቱ ያካትታል፡፡ በመሆኑም በየሦስት ዓመቱ አዲስ የሆቴል ምዘና የሚደረግ ሲሆን፣ ደረጃ ማሻሻል የሚፈልጉ ሆቴሎች በየዓመቱ ክለሳ ማድረግ የሚችሉበት አሠራር መፈጠሩን ሚኒስትር ዴኤታዋ አስታውቀዋል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከዓለም ቱሪዝም ድርጅት ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት በተከናወነው የሆቴሎች የደረጃ ምደባ ሥራ በአዲስ አበባ ከተማ የሚኙ ሆቴሎች ያገኙት የደረጃ ምደባ ውጤት፤

ተ.ቁ

የሆቴሉ ስም

ያገኙት የኮከብ ደረጃ

1

ሸራተን አዲስ ሆቴል

5 ኮከብ

2

ኢሊሊ ሆቴል

5 ኮከብ

3

ካፒታል ሆቴል

5 ኮከብ

4

ራዲሰን ብሉ ሆቴል

5 ኮከብ

5

ኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ

4 ኮከብ

6

ሐርመኒ ሆቴል

4 ኮከብ

7

ድሪምላይነር ሆቴል

4 ኮከብ

8

ጁፒተር ሆቴል /ካዛንቺስ/

4 ኮከብ

9

ሳሮማሪያ ሆቴል

4 ኮከብ

10

ደብረዳሞ ሆቴል

4 ኮከብ

11

ናዝራ ሆቴል

4 ኮከብ

12

ፍሬንዲሺፕ ሆቴል

4 ኮከብ

13

ኔክሰስ ሆቴል

4 ኮከብ

14

ዋሽንግተን ሆቴል

4 ኮከብ

15

ሳሬም ኢንተርናሽናል ሆቴል

4 ኮከብ

16

ጁፒተር ሆቴል /ቦሌ/

4 ኮከብ

17

ተገን ገስት አኮሞዴሽን ሆቴል

4 ኮከብ

18

ዘ ሬዚደንስ ሆቴል

3 ኮከብ

19

ኡማ ሆቴል

3 ኮከብ

20

ሒልተን አዲስ

3 ኮከብ

21

ሲዮናት ሆቴል

3 ኮከብ

22

ቢርጋርደን ኢን

3 ኮከብ

23

አዲስ ሪጀንሲ ሆቴል

3 ኮከብ

24

እምቢልታ ሆቴል

3 ኮከብ

25

አፍሮዳይት ሆቴል

3 ኮከብ

26

ኪንግስ ሆቴል

3 ኮከብ

27

ዋሳማር ሆቴል

3 ኮከብ

28

ካራቫን ሆቴል

3 ኮከብ

29

በሻሌ ሆቴል

3 ኮከብ

30

ሞናርክ ሆቴል

3 ኮከብ

31

አዲሲኒያ ሆቴል

3 ኮከብ

32

ቶፕ ቴን ሆቴል

3 ኮከብ

33

ክራውን ሆቴል

3 ኮከብ

34

አምባሳደር ሆቴል

3 ኮከብ

35

ሲያን ሲቲ ሆቴል

3 ኮከብ

36

ሲድራ ሆቴል

3 ኮከብ

37

አራራት ሆቴል

3 ኮከብ

38

ግሎባል ሆቴል

3 ኮከብ

39

አዲስ ቪው ሆቴል

3 ኮከብ

40

ካሌብ ሆቴል

3 ኮከብ

41

ፓኖራማ ሆቴል

3 ኮከብ

42

ሶሎቴ ሆቴል

3 ኮከብ

43

ትሪኒቲ ሆቴል

2 ኮከብ

44

ሆሜጅ ሆቴል

2 ኮከብ

45

ደሳለኝ ሆቴል

2 ኮከብ

46

ራስ አምባ ሆቴል

2 ኮከብ

47

ፓስፊክ ሆቴል

2 ኮከብ

48

ኢምፓየር አዲስ ሆቴል

2 ኮከብ

49

ቸርችል ሆቴል

2 ኮከብ

50

ግራንድ ዮርዳኖስ ሆቴል

2 ኮከብ

51

ኬዜድ ሆቴል

2 ኮከብ

52

አክሱም ሆቴል

2 ኮከብ

53

ግዮን ሆቴል

2 ኮከብ

54

ንግሥተ ሳባ ሆቴል

2 ኮከብ

55

ቀነኒሳ ሆቴል

2 ኮከብ

56

ዳሙ ሆቴል

2 ኮከብ

57

ሶራምባ ሆቴል

2 ኮከብ

58

አስትራ ሆቴል

2 ኮከብ

59

ሃይሚ አፓርትመንት ሆቴል

2 ኮከብ

60

ኤድና አዲስ ሆቴል

2 ኮከብ

61

ዴስቲኒ አዲስ ሆቴል

2 ኮከብ

62

ኤጂ ፓላስ ሆቴል

1 ኮከብ

63

ሰሜን ሆቴል

1 ኮከብ

64

ኢትዮጵያ ሆቴል

1 ኮከብ

65

ናርዳን ሆቴል

1 ኮከብ

66

ኤም ኤን ኢንተርናሽናል ሆቴል

1 ኮከብ

67

ፓራማውንት ሆቴል

1 ኮከብ

68

ስሪዴይስ ኢንተርናሽናል ሆቴል

1 ኮከብ

 

የአዲስ አበባ ሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ውጤት ማጠቃለያ መግለጫ

ተ.ቁ

የኮከብ ደረጃ

የሆቴሎች ብዛት

በመቶኛ

1

5

4

5.9

2

4

13

19.1

3

3

25

36.8

4

2

19

27.9

5

1

7

10.3

ድምር

68

100

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች