– ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ስላቀረቡት አቤቱታ የተባለ ነገር የለም
እነ አቶ መላኩ ፈንታ አዲስ ከወጣው የጉምሩክ ሕግ ጋር በተያያዘ ለፍርድ ቤት ያቀረቡት ‹‹አላግባብ የተመሠረተብን ክስ ይነሳልን›› ጥያቄ ውድቅ ተደረገ፡፡ የዓቃቤ ሕግን ምስክሮች መሰማት እንዲቀጥል ፍርድ ቤት ጥቅምት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ብይን ሰጠ፡፡
በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረውና ክስ ተመሥርቶባቸው በእስር ላይ የሚገኙት አቶ መላኩ ፈንታና አቶ ገብረ ዋህድ ወልደ ጊዮርጊስን ጨምሮ ስምንት ግለሰቦችና አምስት ኩባንያዎች ላይ ብይን የሰጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ነው፡፡
ተጠርጣሪዎቹ የቀድሞውን የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 622/2001 በአዋጅ ቁጥር 859/2006 ሙሉ በሙሉ መተካቱን በመጥቀስ በቀድሞው አዋጅ በወንጀል የሚያስጠይቀው ጉዳይ በአዲሱ አዋጅ በአስተዳደራዊ ሒደት እንዲፈታ በመደንገጉ፣ ክሳቸው ውድቅ እንዲደረግ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡
ፍርድ ቤቱ አቤቱታቸውን ከተቀበለ በኋላ በአዲሱ አዋጅ አንቀጽ 181(1) ነባሩ አዋጅ ሙሉ በሙሉ እንደተተካ ቢደነገግም፣ አንቀጽ 182 ‹‹በሌሎች ሕጐች የተደነገጉ እንደተጠበቁ ሆነው፣ አዲሱ አዋጅ ከመፅደቁ በፊት በወጣው ሕግ የተጀመሩ ጉዳዮች በነበረበው ሕግ ይቀጥላሉ፤›› ማለቱን ጠቅሷል፡፡
በመሆኑም አገላለጹ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22(2) እና የወንጀል ሕግ አንቀጽ 5(3) ጋር ይቃረናል ወይስ አይቃረንም የሚለውን የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ አጣርቶ እንዲልክለት ማዘዙ ይታወሳል፡፡ ጉባዔውም አይቃረንም የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡ አጣሪ ጉባዔው በአብላጫ ድምፅ ሐምሌ 17 ቀን 2007 የሰጠውን ውሳኔ ሲመረምር የከረመው ፍርድ ቤቱ፣ ጥቅምት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጠው ብይን እሱም አይቃረንም በማለት የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች መሰማት እንዲቀጥሉ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
በመሆኑም በመዝገብ ቁጥር 141352 እና 141356 ላይ ክስ የተመሠረተባቸው እነ አቶ መላኩ ላይ፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ምስክሮች በሳምንት ሦስት ቀናት (ሰኞ፣ ረቡዕና ዓርብ) እንዲሰሙ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ምስክሮች ተሰምተው በተጠናቀቁበት የመዝገብ ቁጥር 141354 ላይ ታህሳስ 13 ቀን 2008 ዓ.ም. ብይን እንደሚሰጥም አስታውቋል፡፡ አንዳንድ ክስ ያላቸው ዶ/ር ፍቅሩ ማሩና አቶ በላቸው በርታ የቀጠሮው ጊዜ እንደተራዘመባቸው በመግለጽ ተቃውሞ አቅርበዋል፡፡
እነ አቶ መላኩ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ የሰጠው ውሳኔ ከተሰጠው ሥልጣን ውጪ መሆኑን በመጥቀስ፣ እንዲሁም ሕግን የመተርጐም ሥልጣን የተሰጠውን የዳኝነት ሥልጣን በመጋፋት ውሳኔ መስጠቱ ተገቢ አለመሆኑን ጠቅሰው ለፌደሬሽን ምክር ቤት አቤቱታ ያስገቡ ቢሆንም በጉዳዩ ላይ የተባለ ነገር የለም፡፡