የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች የነበሩት አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ አቶ አብርሃ ደስታና አቶ የሺዋስ አሰፋ እንዲሁም አቶ አብርሃም ሰለሞን በሥር ፍርድ ቤት በነፃ መሰናበታቸውን በመቃወም ከሳሽ የፌዴራል አቃቤ ሕግ አቅርቦት የነበረውና በተረኛ ችሎት ‹‹ያስቀርባል›› የተባለው የይግባኝ አቤቱታ፣ በመደበኛ ችሎት ውድቅ ተደረገ፡፡
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ነሐሴ 14 ቀን በሰጠው ብይን፣ አምስቱም ተጠርጣሪዎች መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ብይን መስጠቱ ይታወሳል፡፡ ብይኑን በመቃወም ዓቃቤ ሕግ ነሐሴ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረበውን የይግባኝ አቤቱታ፣ በወቅቱ ተሰይሞ የነበረው ተረኛ ችሎት፣ የሥር ፍርድ ቤት ብይን እንዳይፈጸም በማገድ ለመስከረም 21 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡
መስከረም 21 ቀን 2008 ዓ.ም. ቂሊንጦ ማርያም ቤት የታሰሩት አቶ ሀብታሙ አያሌውና አቶ አብርሃም ሰለሞን ባይቀርቡም ቃሊቲ ማረሚያ ቤት የታሰሩት አቶ አብርሃ ደስታ፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺና አቶ የሺዋስ አሰፋ ያልቀረቡ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ለቃል ክርክር ለጥቅምት 3 ቀን 2008 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ጥቅምት 3 ቀን 2008 ዓ.ም. ለቃል ክርክር ተዘጋጅተው የቀረቡት አምስቱም ተከሳሾች መቅረባቸውን ፍርድ ቤቱ ካረጋገጠ በኋላ፣ ለምን እንደቀረቡ መደበኛ ችሎቱ ጠየቃቸው፡፡ የተከሳሾቹ ጠበቃ አቶ አመሐ መኮንን በሰጡት ምላሽ፣ የሥር ፍርድ ቤት ደንበኞቻቸውን ነሐሴ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በነፃ ካሰናበተ በኋላ ዓቃቤ ሕግ ይግባኝ በማለት ብይኑ ተፈጻሚ እንዳይሆን በማሳገዱ ለክርክር ተዘጋጅተው እንዲቀርቡ መጥሪያ ስለደረሳቸው መቅረባቸውን አስረድተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በመዝገቡ ላይ ምንም ያለው ነገር እንደሌለ ተናግሮ፣ የሥር ፍርድ ቤት የሰጠው ብይን ተገልብጦ ከቀረበ በኋላ ተመርምሮ ‹‹ያስቀርባል ወይም አያስቀርብም›› እንደሚባል በመግለጽ፣ የተረኛ ችሎቱን ትዕዛዝ በማለፍ የቀረበውን መዝገብ መርምሮ ‹‹ያስቀርባል ወይም አያስቀርብም›› የሚለውን ብይን ለመንገር ሌላ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ዓቃቤ ሕግ እንዴት የሥር ፍርድ ቤትን ብይን ሊቃወም እንደቻለና ይግባኝ ያለበትን ምክንያት እንዲያስረዳ ጠይቆት አስረድቷል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በዋናነት ባቀረበው አቤቱታ በተከሳሾቹ ላይ በቂ የሆኑ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ የነበረ ቢሆንም፣ የሥር ፍርድ ቤት በአግባቡ እንዳላየለትና እንዳልመዘነለት አስረድቷል፡፡
በተለይ ተከሳሾቹ የተከሰሱበትን የሽብር ድርጊት የሚያረጋግጡ ሰነዶች ከብሔራዊ ደኅንነት መሥሪያ ቤት የተገኙ ሆነው ሳለ፣ ፍርድ ቤቱ ‹‹ዓቃቤ ሕግ እንደ ክሱ ያላስረዳ በመሆኑ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ ይሰናበቱ›› ማለቱ ተገቢ ባለመሆኑ፣ የሥር ፍርድ ቤት ብይን ተሰርዞ እንዲከላከሉ እንዲወሰንለት ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የሥር ፍርድ ቤትን የውሳኔ መዝገብ መርምሮ ዓቃቤ ሕግ ይግባኝ ያለበት ሁኔታ ‹‹ያስቀርባል ወይም አያስቀርብም›› ለማለት ለጥቅምት 17 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡