የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ከአራት ዓመታት በፊት የገዛቸው የተለያዩ ግዙፍ ማሽኖች ተጥለው እየዛጉና እየተበላሹ መሆኑ ተጠቆመ፡፡
ባለሥልጣኑ በብዙ ሚሊዮን ብር እንደገዛቸው የተጠቆሙት ማሽኖች፣ ዓመታዊ የተሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ መመርመሪያ ማሽንና የወደቁ ተሽከርካሪዎች ማንሻ ክሬን ናቸው፡፡ የተሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ መመርመርያ ማሽኑ ያለምንም አገልግሎት በዋናው መሥሪያ ቤት ግቢ ውስጥ ተጥሎ እንደሚገኝ የሪፖርተር ምንጮች ተናግረዋል፡፡
በ2003 ዓ.ም. እንደተገዙ የተገለጸው የተሽከርካሪ ብቃት መለኪያ ማሽኖች ሁለት መሆናቸውን የጠቆሙት ምንጮች፣ አንደኛው ማሽን ድሬዳዋ ለሚገኘው የተቋሙ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት የተላከ ቢሆንም፣ በተመሳሳይ ሁኔታ ያለአገልግሎት መቀመጡን አስረድተዋል፡፡
ማሽኖቹ በዋናነት የተገዙት ያለምንም የሰዎች ንክኪ ከሙስና በፀዳ አሠራር የተሽከርካሪዎችን ብቃት ለማረጋገጥ ቢሆንም፣ ባልታወቀ ምክንያት ላለፉት አራት ዓመታት ተጥለው እንደሚገኙ ምንጮች አክለዋል፡፡ ማሽኖቹ በሥራ ላይ ቢውሉ ሠራተኞች በሥነ ምግባር ሥራቸውን እንደሚያከናውኑ፣ አንዳንድ የተሽከርካሪ ባለንብረቶችና የተቋሙ ሠራተኞች ከሚፈጽሙት የሙስና ተግባር እንደሚታቀቡ፣ ከዚህም በተጨማሪ በተሽከርካሪዎች የብቃትና የቴክኒክ ችግር ምክንያት በዜጎች ላይ የሚደርሰውን የተሽከርካሪ አደጋም ለመከላከል ይቻል እንደነበር ምንጮች ተናግረዋል፡፡
በመንገድ ላይ ከባድ ተሽከርካሪዎች ተበላሽተው ቢቆሙ፣ ቢገለበጡና የተለያዩ ችግሮች ቢያጋጥማቸው መተላለፊያ መንገዶችን ለቀናት ዘግተው እንዳይከርሙ በፍጥነትና በቅልጥፍና ለማንሳት እንዲቻል ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዛ ክሬን ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ ሚሌ ላይ ቆሞ እንደሚገኝም ምንጮች አስረድተዋል፡፡ ክሬኑ ያልተነሳው ‹‹ኦፕሬተር የለም›› በሚል ሰበብ መሆኑንም አክለዋል፡፡ ክሬኑ ከቆመበት ጊዜ አንስቶ ባለሥልጣኑ ሰዎችን ማሠልጠን ቢጀምር ማስመጣት ይቻል እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡
የፌዴራል መንገዶች ባለሥልጣን ኃላፊዎች በሚሊዮኖች በሚገመት የመንግሥትና የሕዝብ ገንዘብ የተገዙ ማሽኖች ያለምንም አገልግሎት ቆመዋል መባሉን አስመልክቶ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጥረት ተደርጎ ነበር፡፡ የተሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የመንገድ ደኅንነት ድጋፍ ሰጪ ዳይሬክቶሬት፣ ዳይሬክተር እንዲሁም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊውን ለማግኘት በቢሮአቸው ሪፖርተር የተገኘ ቢሆንም፣ አንዱ ሌላውን ምላሽ መስጠት እንዳለበት ከመግለጽ ባለፈ በማሽኖቹ ጉዳይ ላይ ለተነሳው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡