‹‹ትክክለኛው የተረጂ ቁጥር ስንት ይሆናል የሚለውን ከጥቅምት ወር መጨረሻ ሳምንት ጀምሮ ለ21 ቀናት መኸር አብቃይ በሆኑ በአርብቶ አደሩ አካባቢዎች የሚደረገው ግምገማ ትክክለኛውን ቁጥር ይዞ ስለሚመጣ በዚያ አግባብ ምላሽ እንሰጣለን፡፡ መንግሥት የአንበሳውን ድርሻ በመያዝ እስካሁን አራት ቢሊዮን ብር መድቦ እየሠራ ነው፡፡ በቀጣይም ከለጋሾች ድጋፍ ባይገኝ መንግሥት ተጨማሪ በጀት በመመደብ ችግሩን እንዳመጣጡ ይመክታል፡፡››
የብሔራዊ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚቴ ጸሐፊ አቶ ምትኩ ካሳ፣ በኢትዮጵያ 8.2 ሚሊዮን ዜጎች ለድርቅ አደጋ በመጋለጣቸው ምክንያት በመንግሥትና በለጋሾች እየተደረገ ስላለው ድጋፍ ጥቅምት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች ከሰጡት ማብራሪያ የተወሰደ፡፡
ኤልኒኖ ተብሎ በሚጠራው የአየር ጸባይ ለውጥ ሳቢያ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በድርቅ የተጠቃች ሲሆን፣ ይህ ክስተት የአገሪቱን የዝናብ ወቅቶች በማዛባት፣ የዝናብ መጠንና ጊዜን በመቀነስ በየአሥር ዓመቱ እየተከሰተ ይገኛል፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች በኤልኒኖ ምክንያት ከፍተኛ የድርቅ አደጋ ያጋጥማቸዋል፡፡