Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየዓለም ባንክ መንግሥት ለከተሞች መሬት የሚያቀርብበትን አሠራር መቀየር አለበት አለ

የዓለም ባንክ መንግሥት ለከተሞች መሬት የሚያቀርብበትን አሠራር መቀየር አለበት አለ

ቀን:

– ‹‹በመሬት አቅርቦት ላይ ብቻ የሚሠራ ኮርፖሬሽን ይቋቋማል›› የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር

የዓለም ባንክ ላለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ከተሞች ላይ ባደረገው ጥናት፣ መንግሥት እስካሁን ሲተገብር የቆየውን የመሬት አቅርቦት ሥርዓት መቀየር ካልቻለ፣ እ.ኤ.አ. በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ መሠለፍ እንደማይቻል አስታወቀ፡፡

የዓለም ባንክ ኢትዮጵያውያን ኤክስፐርቶችን ጨምሮ ከእስያ፣ ከአውሮፓ፣ በአፍሪካ ከሚገኙ ትላልቅ ዩኒቨርሲቲዎች የተሰባሰቡ ምርጥ ዕውቀት አላቸው የተባሉ ምሁራን በመላ ኢትዮጵያ የሚገኙ ከተሞችን የመሬት አቅርቦት፣ የቤቶች ግንባታ፣ የመሠረተ ልማት ግንባታና የሥራ ፈጠራን በሚመለከት ያጠኑትን የጥናት ውጤት፣ መስከረም 27 ቀን 2008 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ይፋ አድርጓል፡፡

በዓለም ባንክ ከፍተኛ የከተማ ልማት ስፔሻሊስትና የጥናት ቡድኑ መሪ አቶ አበባው ዓለማየሁ እንደገለጹት፣ በአሁኑ ጊዜ በከተሞች ውስጥ የሚኖረው የሕዝብ ቁጥር ከጠቅላላው የአገሪቱ ሕዝብ 20 በመቶ ነው፡፡ በሚቀጥሉት ሁለት አሠርት ዓመታት ቁጥሩ 42 ሚሊዮን ይደርሳል ወይም ይበልጣል፡፡ ይኼ ማለት ደግሞ ብዙ ሰዎች በከተማ መኖር ስለሚችሉ ቤት፣ መሠረተ ልማቶችና መሬት በዋናነት እንደሚያስፈልጉ ገልጸዋል፡፡

መንግሥት አሁን መሬት እያቀረበ ያለው በሁለት መንገዶች ማለትም በቀጥታ (በድርድር) እና በጨረታ መሆኑን በጥናቱም የተረጋገጠና እየተሠራበት መሆኑን የገለጹት አቶ አበባው፣ 95 በመቶ የሚሆነው በድርድር እንደሆነ፣ አምስት በመቶው ብቻ በጨረታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መሬት በድርድር ሲሰጥ በዝቅተኛ ዋጋ በመሆኑ መሬቱን ለማልማት የሚወጣውን ዋጋ የማይመልስ ስለሚሆን፣ በጨረታ ቢቀርብ ኪራይ ሰብሳቢነትንም የሚያስቀር መሆኑን አስረድተዋል፡፡ 95 በመቶ የሚሆነውን መሬት በድርድር (በአሎኬሺን) እየተሰጠ እ.ኤ.አ. በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሠለፍ እንደማይቻል አክለዋል፡፡

ለመንግሥት ድርጅቶች መሬቱን ለማልማት በወጣው ዋጋ፣ ለማኅበራዊ አገልግሎቶችና መሬት ገዝተው ቤት መገንባት ለማይችሉ አቅም ለሌላቸው ደግሞ ከዋጋ በታች ቢሰጥ ችግር እንደማይኖረው ጠቁመዋል፡፡

ኤክስፐርቶቹ በጥናታቸው ያረጋገጡት በከተማ የሚኖረው ሕዝብ ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ፣ በከተማ አስተዳደር ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሥራ ዕድል መፍጠር ካልተቻለ ማለትም፣ ማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ በማስፋፋት ያለውን የሰው ኃይል መጠቀም ካልተቻለ፣ የሥራ አጥ ቁጥር እየጨመረ እንደሚሄድ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት አሁን እየሠራው ስላለው የቤቶች ፕሮግራም በሚመለከት አስተያየት የሰጡት አቶ አበባው፣ መንግሥት ቤት መገንባት ያለበት ምንም ገቢ ለሌላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አሁን ባለው የቤቶች ፕሮግራም ቤት እያገኘ ያለው ከፍተኛ ገቢ ያለው ሊሆን ስለሚችል፣ በጥልቀት ጥናት በማድረግ ችግረኛውንና ከፍተኛ ገቢ ያለውን በመለየት መሆን ስላለበት አሠራሩን ሊፈትሽ እንደሚገባ በጥናቱ መጠቆሙ ተገልጿል፡፡  

የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ከተሞች ላይ ያደረገውን ጥናት በማድነቅና በጥናቱ ወቅት ከአጥኝዎቹ ጋር ተቀራርበው በመወያየት ምክሮችን በመለዋወጥ በተገኘው ውጤት መደሰታቸውን የገለጹት የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር አቶ መኩሪያ ኃይሌ፣ ኤክስፐርቶቹ በጥናታቸው የመሬት አቅርቦትንና ሌሎች ከከተማ ፅዳትና ፕላን ጋር በተገናኘ ያቀረቡትን የማሻሻያ ሐሳብ መንግሥት መቶ በመቶ እንደሚቀበለው አረጋግጠዋል፡፡

በጥናቱ ሁለት ትልልቅ ሥራዎች መከናወናቸውን የጠቆሙት አቶ መኩሪያ፣ በከተሞች የማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ መስፋፋት፣ እንዲሁም የአቅም ግንባታ ሥራ መሠራት እንዳለበት የቀረበው አስተያየት እጅግ በጣም ወሳኝ መሆኑን ተናግረው፣ ‹‹በፖለቲካ መድረካችን የገመገምነው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዳችን ያካተትነው ነው፡፡ በከተሞቻችን ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት ያለንን አምራች የሰው ኃይል መጠቀምና በአገሪቱም ላይ የተሳካ ለውጥ ማምጣት ነው፤›› ብለዋል፡፡

በመሬት አቅርቦት ዙሪያ አደረጃጀቱን በመፈተሽ መሬት በራሱ አቅርቦት የራሱን ገቢ የሚያገኝበትና የራሱን ወጪ የሚሸፍንበት አሠራር ላይ እንደሚደርስ ተናግረው፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች በመሬት አቅርቦት ዙሪያ የሚሠራ ኮርፖሬሽን እንደሚቋቋም ተናግረዋል፡፡

የቤት ልማት ግንባታን በሚመለከት አነስተኛ ገቢ ላለውና ለመንግሥት ሠራተኛ እየዋለ እንዳልሆነ በሚመለከት በጥናቱ የተሰጠውን አስተያየት በሚመለከት፣ አሠራሩን መፈተሽ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረው፣ ‹‹ኅብረተሰቡ ቤቶቹ በፍጥነት ይገንቡ›› እያለ በመሆኑ፣ በጥናቱ የተሰጠውን አስተያየት መንግሥት ሙሉ በሙሉ እንደማይቀበለውና በቤት ልማቱ እንደሚገፋበት አስታውቀዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...