Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ቡና ወደ ምርት ገበያ መግባቱ ለእኔ የሚያሳምም ከባድ አደጋ ነው››

አቶ አበራ ቶላ፣ የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ቦርድ ሰብሳቢ

በማኔጅመንትና በፐብሊክ አድሚኒስትሬሽን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በሊደርሺፕ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል፡፡ አቶ አበራ ቶላ በኦክስፋም ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ብሎም በቀጣናው ዋና ኃላፊ በመሆን ለረጅም ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ከኦክስፋም ጋር በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያ ደሃ ገበሬዎች በትልልቅ ኩባንያዎች የሚደርስባቸውን ጫና በማስመልከት ባስተጋቡት ዓለም አቀፍ ድምፅ ይታወሳሉ፡፡ አቶ አበራ ‹‹ሜክ ትሬድ ፌር›› ወይም ‘ንግድን ፍትሐዊ ማድረግ’ በሚለው የኦክስፋም ዘመቻ በቡና አምራች ኢትዮጵያውያን ላይ ይደርስ የነበረውን ጫና በመጋፈጥ፣ የኢትዮጵያ ቡና ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ በመሟገት የተንቀሳቀሱበት ወቅት የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ከዚህ ተግባራቸው ባሻገር ከሁለት ትልልቅ የዓለም ኩባንያዎች ጋር የተፋጠጡበት ጊዜም አይዘነጋም፡፡ ኔስሌና ስታርባክስን ከመሳሰሉ ኩባንያዎች ጋርም የተፋጠጡበትን ዘመቻ አከናውነው በድል ተወጥተዋል፡፡ ከሁለቱ ኩባንያዎች ጋር የነበረው ሙግት በኢትዮጵያ መብት ላይ ያነጣጠረ ነበር፡፡ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የሚደገፈውን ሲነርጎስ ኢንስቲትዩት በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ለትርፍ ያልቆመውና የመንግሥትን ሥራዎች የሚያግዘው ይህ ተቋም በግብርና ዘርፍ ላይ የሚታዩ ተቋማዊ ችግሮችን ከመቅረፍ ባሻገር፣ የአመራር ግለሰቦች የብቃትና የአመራር ክህሎት ላይ ያተኩራል፡፡ በዋናነት በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲና በግብርና ሚኒስቴር መካከል የነበሩ አለመጣጣሞችን በመሸምገልና የሥራ ድርሻዎችን በመመጠን ረገድ አቶ አበራ የሚመሩት ሲነርጎስ ኢንስቲትዩት ትልቁን ድርሻ ተወጥቷል፡፡ ከዚህ ኃላፊነታቸው ጎን ለጎንም የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክን በቦርድ ሰብሳቢነት የሚመሩት አቶ አበራ፣ ከአሥራት ሥዩም ጋር ባደረጉት ቆይታ በቡና ዘርፍ ላይ ከሚታዩት ችግሮች፣ የምርት ገበያው በቡና ላይ አሳድሯል ካሉት ተፅዕኖ እስከ ፋይናንስ ዘርፉ ባሉት ጉዳዮች ላይ ሐሳባቸውን አካፍለዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት እየተሳተፉበት ካለው ተቋም እንጀምር፡፡ ሲነርጎስ ምንድነው የሚሠራው? ምንስ ላይ ያተኩራል?

አቶ አበራ፡- ለትርፍ ባልተቋቋሙ ድርጅቶች ውስጥ ለብዙ ዓመታት ሠርቻለሁ፡፡ ከሃያ ዓመታት በላይ አገልግያለሁ፡፡ ከአገር በቀል እስከ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ ተሳትፎ ነበረኝ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚጠቀሱት አንዱ ኦክስፋም ነው፡፡ ለተቋሙ ከኢትዮጵያ ዳይሬክተርነት እስከ ቀጣናው ዳይሬክተርነት ባለው እርከን ላይ ሠርቻለሁ፡፡ ኦክስፋም በጣም ጠንካራና ትልቅ ድርጅት ሲሆን፣ በይበልጥ በሰብዓዊና በዘመቻ እንዲሁም በቅስቀሳና በፖሊሲ የለውጥ ሥራዎች በጣም ጠንካራ ሆኖ እየሠራ የሚገኝ ድርጅት ነው፡፡ በዚህ ተቋም በቀጣና ደረጃ ብዙ ሥራዎች ሠርተናል፡፡ እዚህ አገርም በልማት በኩል ብዙ ጠንካራ ሥራዎችን ሠርተናል፡፡ በዓለም ላይ ከ14 ያላነሱ ኦክስፋሞች አሉ፡፡ በእኛ ቀጣና የ14ቱን ድርጅቶች ስሠራ ቆይቻለሁ፡፡ ወደ ሲነርጎስ ኢንስቲትዩት ስንመጣ ግን የተለየ ድርጅት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ድህነትን ወይም በዚሁ ሳቢያ የተገፉትን የሚመለከት ነው፡፡ ይህ ተቋም የተቋቋመው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ከቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ባደረጉት የልማት ስምምነት መሠረት የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ተመሠረተ፡፡ ኤጀንሲው ሲቋቋም ጀምሮ እነ ኦክስፋም መሠረቱን ጥለዋል፡፡ ሲቋቋም የሁላችንም ተስፋ ስለሆነ ውይይት ስናደርግ ኤጀንሲው በግብርና መስክ ሊሠሩ የሚችሉ ሰዎችን ከመላው ዓለም አሰባስበን፣ በተለይ ኢትዮጵያዊ ዳያስፖራዎችን በማምጣት ለግብርናው ዘርፍ ኃይል መስጠት ነበር ተግባሩ፡፡ አቅም ለመስጠት ነው የተቋቋመው፡፡ ሜከንዚ በተባለው የአሜሪካ ድርጅት በኩል በተደረገ ጥናት ግብርናው ስድስት ማነቆዎች እንዳሉበት ከጅምሩ ታውቆ ነበር፡፡

ለምሳሌ በኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል ችግር ነበር፡፡ በአፈር ላይ ችግር ነበር፡፡ በግብዓት አቅርቦት፣ በፀረ አረምና በመሳሰሉት ችግሮች ላይ ለመሥራትና ለማገዝ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤንጀሲ ተቋቁሟል፡፡ የመንግሥት ድርጅት ሆኖ መቋቋሙ ግዴታ ስለነበር ኤጀንሲው በመንግሥት ሥር ሆኗል፡፡ የመንግሥት ድርጅት ብቻም ሳይሆን የኤጀንሲው ሰብሳቢም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆነዋል፡፡ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትርም እንደ ቀድሞው ሁሉ ምክር ቤቱን በሰብሳቢነት ይመራሉ፡፡ አዲሱን ኤጀንሲ ካለው ሥርዓትና መዋቅር ጋር እንዴት አጣጥሞ መሄድ ይቻላል የሚለው ትልቅ ጥያቄ ነበር፡፡  በፋውንዴሽኑና በጠቅላይ ሚኒስትሩም በኩል ይህ ጥያቄ ይጉላላ ነበር፡፡ የምናመጣቸውን ሰዎች በሲቪል ሰርቪስ መዋቅርና ደመወዝ እርከን መሠረት ለማስተናገድ አይቻልም፡፡ የተለየ ነገር ያስፈልገው እንደነበር ተስማምተናል፡፡ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ማስገባት አይቻልም፡፡ የቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የጥናቱም የኤጀንሲውም መመሥረት ዋና አመንጪ በመሆኑ ባለቤትነቱም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር አብሮ ሊነሳ የሚችል ስለነበር፣ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ስናስብ በዚህ መስክ ሥራውን  ለየት ባለ መልኩ ሊሠራ የሚችል ማነው ተብሎ ሲፈለግ፣ ኒውዮርክ የሚገኘው ሲነርጎስ ነው የተገኘው፡፡ ይህ ተቋም በፋውንዴሽኑ በኩል ትልቅ አክብሮት የሚሰጠው ነው፡፡ በአፍሪካ አገሮችም ልምድ አለው፡፡ ስለዚህ ሲነርጎስ በዚህ አማካይነት መጣ፡፡ እኔም ኦክስፋምን ትቼ ወደ ሲነርጎስ መጣሁ ማለት ነው፡፡ የሲነርጎስ ኢንስቲትዩት ሥራ ምንድነው ከተባለ ከግለሰብ ይጀምራል፡፡ ግለሰቦች ተቋማትን ትራንስፎርም ከማድረጋቸው በፊት ራሳቸውን እንዴት መቀየር አለባቸው የሚል መነሻ አለው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በርካታ የአሠራር ፖሊሲዎችን ቀድቷል፡፡

ለምሳሌ መሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ ወይም ቢፒአር አለ፡፡ ቢፒአርን የተረጎመው ቢዝነስ ስኮር ካርድ የምንለው አሠራር ነው፡፡ ይህ ሒደት እያንዳንዱ ሰው እንዴት እንደምትሠራ እያየ ውጤቱን ይሰጣል፡፡ ሆኖም ግን ክፍተት አይተንበታል፡፡ ሥርዓቱ ተስተካከለ፡፡ በቢፒአር የተሸለሙ ድርጅቶች አሉ፡፡ የውልና ማስረጃ ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ተሸላሚ ነው፡፡ ይህ ጥሩ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ስለሰውየውስ? ያልታየው ክፍል ይህ ነው፡፡ በመሆኑም ሰዎችን በሁለትና በሦስት መንገዶች ማብቃት ይቻላል፡፡ አንደኛው መደበኛ የሆነውን ሥልጠና በመስጠት ማብቃት የቆየው አካሄድ ነው፡፡ አሁን ግን ግለሰቡ ጥሩ አምራች፣ ጥሩ ዜጋ፣ ጥሩ ሠራተኛ እንዲሆን ሊረዳ ይገባዋል፡፡ ግለሰቡ ራሱን ወደ ውስጥ ማየት ይኖርበታል፡፡ ለምንድነው ይህንን ሥራ የምሠራው? እፈልገዋለሁ ወይ? ተስፋ አይበታለሁ ወይ? የምመኘው ነገር ነው ወይ? ብሎ ራሱን ማየት አለበት፡፡ ትራንስፎርሜሽን በግለሰብ ውስጥም መምጣት አለበት፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ወደ ሥርዓት ይኬዳል፡፡ ያ ግለሰብ የሥርዓት ለውጥ እንዴት ማምጣት ይችላል ወደሚለው እንሄዳለን፡፡ የሲነርጎስ ሥራ ይኼ ነው፡፡ ‹‹ብሪጂንግ ሊደርሺፕ›› ወይም አመራሮችን ማገናኘት የሚባል አሠራር አለ፡፡ ጥሩ መሪ ሲኖር ያንን ሰው ከሌላው ጋር ማገናኘት፣ ኔትወርክ መፍጠር ማለት ነው፡፡ ለአራት ዓመት ያህል ሲነርጎስ ተጨባጭ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል፡፡ መቶ በመቶ የሲነርጎስ ሥራ የመንግሥት ሥራ ነው፡፡ በጀቱም የመንግሥት ነው፡፡ ምንም እንኳ የተቋሙ ስም መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም ቢመስልም፣ የሚንቀሳቀሰው ለትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲና ለግብርና መስክ የተመደበ ገንዘብ በመጠቀም ነው፡፡ የእነ ቢል ጌትስ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ በግብርናና በጤና መስኮች ላይ ዕርዳታ ያደርጋል፡፡ ጥሩ ሥራ የተሠራው ምንድነው ካልን ኤጀንሲው ከግብርና ሚኒስቴር ጋር ተዋህዶ መሥራት እንዲችል ማድረግ ነው፡፡ ሁልጊዜ በነበረውና አዲስ በሚመጣው መካከል ግጭቶች ይኖራሉ፡፡ ለኤጀንሲው ያሰባሰብናቸው ሰዎች በጣም ወጣቶችና ፈጣኖች ናቸው፡፡ በግብርና አካባቢ ደግሞ ለብዙ ዓመት የነበረ ሥርዓት አለ፡፡ ልማድ አለ፡፡ ይህንን ወደ አንድ ማዕቀፍ ማምጣት ለሲነርጎስ ከባድ ነበር፡፡ ኤጀንሲው ከግብርና ምርምር፣ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከእያንዳንዱ የሚኒስቴር ዘርፍ ጋር ተጣጥሞ እንዲሠራ ማድረግ በጣም ፈታኝ ሆኖብን ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ሥራ ምን ያህል ርቀት ተጓዛችሁ? በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲና በግብርና ሚኒስቴር መካከል ተዋህዶ መሥራቱ ላይ ያለመግባባት ነበር፡፡ በግብርና ሚኒስቴር ሥር ያሉ ሥራዎችን ለመወጣት ኤጀንሲው በገለልተኝነት የሚሠራባቸው አካሄዶች አሉ፡፡ ከሁለቱ የትኛውን ነው የሚመለከተው የሚሉ ጥያቄዎችን በመሰንዘር ሰዎች ሲቸገሩ ይታያል፡፡ በማግባባት ደረጃ እስከምን ሠርታችኋል? በሁለቱ መካከል የሥራ ክፍፍል አለ?

አቶ አበራ፡- ይኼ አንዱ ዋናው ሥራችን ነበር፡፡ የኤጀንሲውንና የግብርና አመራሮችን ይዘን ዓውደ ጥናት አካሂደናል፡፡ ምንድነው ግራ መጋባቱ? ግጭቱ ምኑ ጋ ነው ያለው? የሚለውን ማውጣት ነበረብን፡፡ ይኼንን ማድረግ አንዱ ሥራችን ነበር፡፡ ነገሮች እየወጡ መጡ፡፡ ለምሳሌ ግጭት ከነበረበት አንዱ መስክ ኤጀንሲው የተግባር ሥራ ይሠራል ወይስ አይሠራም የሚለው ጥያቄ ነበር፡፡ ኤጀንሲው ተግባራዊ ሥራዎች ውስጥ መግባት ሳይሆን ግብርና ሚኒስቴርን ማብቃት፣ በግብርና ሚኒስቴር ውስጥ የጎደለውን ሥራ መሙላት ነበር የኤጀንሲው ተግባር፡፡ እርግጥ ኤጀንሲው ወደ ተግባር ሥራዎች ውስጥ የገባባቸው አካሄዶች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ወጣቶች በመሆናቸው ለውጥና ውጤት፣ የሚታይና የሚጨበጥ ሥራ ማሳየት ይፈልጋሉ፡፡ እነዚህ ውጤቶች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ደረጃ የሚታወቁ ናቸው፡፡ ነገር ግን ውጤቶቹን ማሳየት ያለባቸው ከግብርና ሚኒስቴር ጋር አብሮ በመሥራትና በጋራ በመንቀሳቀስ ነው፡፡ እነዚህ ሲሮጡ እነዚያ ሲጎትቱ ችግር ይመጣል ማለት ነው፡፡ ወደ ኋላ ጎተታችሁን ብለው ጠይቀው ምላሽ ሲያጡ በራሳቸው የመሄድ አዝማሚያ ነበር፡፡ በራሳቸው ወደ መስክ መሄድ መጀመራቸው ደግሞ አለመግባባቱን ይበልጥ አሰፋው፡፡ በተለይ በኤክስቴንሽንና በምርምር አካባቢ አለመግባባቶች ተፈጠሩ፡፡ ይህንን ማስቆም ነበረብን፡፡ ኃላፊነቶችና ሚናዎችን በግልጽ ለይቶ ማስቀመጥ ነበረብን፡፡ የኤጀንሲውና የግብርና ኤክስቴንሽንና ምርምር ሚናዎች ምንድን ናቸው ብለን መለየት ነበረብን፡፡ ለየብቻ ያላቸውን ሚናና ኃላፊነት በመደንገግ ግር የሚያሰኙትን በመለየት አውጥተናል፡፡ ዕቅድ ሲያወጡም ለየብቻቸው በመሆኑ ግቦቻቸውና ዓላማቸውም ላይ መለያየት ተፈጥሯል፡፡ እነዚህን ማጣጣም እንደሚገባ አይተን አስተካክለናል፡፡ በዚህ መሠረት ለዓመት ተኩል በሰላም ለመጓዝ ችለዋል፡፡ እኛም እንከታተላለን፡፡ የሁለቱም አመራሮች በየሳምንቱ እየተገናኙ ይነጋገራሉ፡፡ ይህ እንግዲህ መስተፃምር ወይም ‹‹አላይንመንት›› የምንለው ነው፡፡

የሚገርመው ግን በግብርና ሚኒስቴር ውስጥ በርካታ ዘርፎች አሉ፡፡ የተፈጥሮ ሀብት፣ የእንስሳት፣ ወዘተ. ዘርፎች ቢኖሩም እርስ በርስ አይናበቡም ነበር፡፡ ይኼ ግን በአገሪቱ ያለ ችግር ነው፡፡ በእያንዳንዱ ሚኒስቴር ውስጥ ያለ ችግር ነው፡፡ ጥሩ ምሳሌ ለመስጠት የኅብረት ሥራ ማኅበራትን እንውሰድ፡፡ እነዚህ በጣም ፈታኝ ነበሩ፡፡ ሊወድቁ ደርሰው የነበሩ ናቸው፡፡ በኀብረት ሥራ ማኅበራት ዳይሬክተሬቶች በኩል ግባቸውና ተልዕኳቸው ላይ ምንም ዓይነት ስምምነት አልነበረም፡፡ የሚደንቅ ልዩነት ነበር፡፡ ምንም ዓይነት ተዛምዶ አልነበራቸውም፡፡ አምስት ያህል ዳይሬክቶሬቶች አሉ፡፡ በሚና ተልዕኳቸው ላይ እርስ በርስ የሚጋጩ ነበሩ፡፡ ግብና ተልዕኳቸውንም የሚጠራጠሩ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ እያንዳንዱን ዳይሬክቶሬት ወስደን መነሻ ግባችሁ ምን እንደሆነ ግለጹ እያልን የየክፍሉን ሰዎች እንጠይቅ ነበር፡፡ የመጀመሪያውን ችግር የምታገኘው እዚህ ላይ ነው፡፡ ይህንን የምናደርግባቸው ቴክኖሎጂዎች አሉን፡፡ ‘ቴሪዩ’ የሚባል ቴክኖሎጂ አለ፡፡ የሚሺጋን ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ የሠራው ነው፡፡ ሥልጠናውን የሚሰጡልን ሰዎች ከዚሁ ተቋም የሚመጡ ናቸው፡፡ በየጊዜው አራትም አምስትም ይመጡልናል፡፡

ሪፖርተር፡- ቴሪዩ ምንድነው? ምንድነው የሚሠራው?

አቶ አበራ፡- ንድፈ ሐሳብ ነው፡፡ አንድን ሥራ ከየት አንስተህ እስከ የት ይዘው መሄድ እንደምትችል የምታይበት ነው፡፡ የታሰበውን ተዛምዶ ወይም ጥምረት ለመፍጠር እንዴት እንደምትሄድበት የሚሳያሳይ የንድፈ ሐሳብ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ በጣም ጠቅሞናል፡፡

ሪፖርተር፡- የትብብር ጉዳይም ይነሳል፡፡ በበርካታ የመንግሥት ኤጀንሲዎች መካከልና በግሉ ዘርፍ ያለመተባበርና ያለመዛመድ ችግር ጎልቶ ይታያል፡፡ የእናንተ ሥራ በግብርና መስክ ላይ እየሠራ ነው፡፡ ወደ ሌሎች ዘርፎች የመግባት ዓላማ አላችሁ?

አቶ አበራ፡- በጀት ይገድበናል፡፡ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ግብርና ሚኒስቴር ብርሃን አሳይታችሁናል፡፡ ኤክስቴንሽንና ምርምር፣ ዕቅድ ክፍልና ምርምር ያሉት አሁን ደህና ናቸው፡፡ አሁን ትልቅ ችግር ያለብን ከክልሎች ጋር ነው ብለዋል፡፡ በግብርና በኩል አገሪቱን የሚመግቡ አራት ትልልቅ ክልሎች አሉ፡፡ ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎችን ሄደን በምናይበት ጊዜ ልዩነት አለ፡፡  ከአማራ ክልል ጀምረን ከግብርና ሚኒስቴር ጋር አብረን ስናወያያቸው ልዩነታቸው የትዬለሌ ነው፡፡ ምንም እንኳ የዕድገትና ትንራንስፎርሜሽን ዕቅድ ነው ሁሉንም የሚመራው ቢባልም አመለካከታቸው እንኳ የተለያየ ነው፡፡ የክልሉ ዕቅድ ከግብርና ሚኒስቴር ዕቅድ ለየብቻው ነው፡፡ በሁለቱ መካከል የዕቅድ ክፍሎች ቢኖሩም ብዙም አይተዋወቁም፡፡ ሚኒስቴሩ ሪፖርት ይጠይቃል፣ በጊዜው የሚያቀርብለት የለም፡፡ በሕገ መንግሥቱ ክልሉ ተጠያቂነቱ ለራሱ ነው፡፡ የግብርና ቢሮ ኃላፊ የክልሉ ፕሬዚዳንት ለሚጠይቀው ነው ቅድሚያ የሚሰጠው፣ ለዚህ አይደለም፡፡ ሌሎች ልዩነቶችም አሉ፡፡ በክልል ደረጃ ጥሩ የሰው ኃይል አቅም አለ፡፡ ተነሳሽነቱም ጠንካራ ነው፡፡ ትግራይንም፣ አማራንም ብትወስድ ጥሩ ነገር አለ፡፡ ነገር ግን ግጭት የሚያስነሱ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ የደመወዝ ልዩነት አለ፡፡ በአመለካከትና በሥነ ምግባርም ልዩነት ይታያል፡፡ አንድ ማዕከላዊ ዕቅድ ስላለ ይኼንን አንድ ላይ ብናመጣው ለአገር ይጠቅማል ብለን አስረድተናል፡፡ ሚናቸውንና ኃላፊነታቸውን በማየት ለግጭት ምክንያት የሆኑትን በማውጣት ብንሠራና የእነሱን ዓላማ ግብ ብናዋህደው ውጤታማ ሊሆን ይችላል፡፡ ሚኒስቴሪ ብዙ የአገር ሀብት ስላለው ይህንን ለመጠቀም አብረው ማቀድ አለባቸው፡፡ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትርጉም እንዲኖረው አብረው ማቀድ አለባቸው፡፡ በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ውጤት አይተናል፡፡ ፌደራልና ክልሎች አብረው እየሠሩ ነው፡፡ በጥቂቱም ቢሆን በግብርና መስክ የሚታዩትን ግጭቶች አስወግደናል፡፡ መናበብና ማናበብ ተችሏል፡፡ ማን ምን እንደሚሠራ ያውቃል፡፡ ዘንድሮ በአራቱ ክልሎችና በግብርና ሚኒስቴር መካከል ጥሩ ግንኙነቶች ተፈጥረዋል፡፡ ይህንን ጉዳይ የሚከታተሉ ሰዎችን መርጠናል፡፡ በጋራ በሦስት ወራት እየተገናኙ የሚሠሩ ሰዎች ተመርጠዋል፡፡ ሲነርጎስ በርጅቶች መካከል፣ በይበልጥም በአንድ ሚኒስቴር ውስጥ ያለውን ሥራ በማቀናጀት እንዲሠሩ የሚያግዝ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ሌሎች የዘርፍ መሥሪያ ቤቶች የመስፋት ዕቅድ አለው?

አቶ አበራ፡- ወደ ሌሎች ዘርፎች ለመግባት አላሰብንበትም ማለት ሳይሆን፣ እኛ የምናገኘው የሥራ ማስኬጃና ቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የሰጠንም በግብርና መስክ ላይ እንድንሠራ የሚያጠንጥን ነው፡፡ ነገር ግን ባለን ልምድና የምንጠቀምባቸውን ሥልቶች በማሰብሰብ ሌሎች የመጣጣምና የመናበብ ችግሮች አሉብን ብለው የሚያምኑ ተቋማትና ሚኒስቴሮች፣ እንዲሁም መሪዎቻቸው እንደ መሪ እንዲበቁ ነው የምንሠራው፡፡ እኛ ከሌሎች አሠራሮች በተለየ መልኩ ግለሰቡን ነው የምናየው፡፡ ግለሰቡን ከሥርዓቱ ጋር እንዴት ማዋሀድ ይቻላል የሚለውን ነው የምናየው፡፡ በዚህ በኩል ድጋፍ የሚፈልጉ ተቋማት ካሉ መርዳት ይቻላል፡፡        

ሪፖርተር፡- በግብርና ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ በቅንጅትና በማዛመድ ሥራዎች ላይ ተሳትፎ እንዳላችሁ ይታወቃል፡፡ ዕቅዱ ለግብርና ዘርፍ ከመጀመሪያው ምን አዲስ ነገር ይዞ ሊመጣ ይችላል?

አቶ አበራ፡- ከመጀመሪያው ዕቅድ በተለየ በዚህ ዝግጅት ላይ በእኛ በኩል በብዛት የተሳተፈው የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ነው፡፡ አራት ትልልቅ ምሰሶዎች አሉት፡፡ ምርታማነቱን፣ የተፈጥሮ ሀብቱን፣ የአደጋና የምግብ ዋስትና፣ እንዲሁም ተቋማዊ አቅም ግንባታ የሚሉት ናቸው፡፡ ሌሎቹ ሦስቱ ምሰሶዎች ተግባራዊ የሚደረጉት በመንግሥት ነው፡፡ በግብርና ሚኒስቴር ሙሉ ኃላፊነት ይተገበራሉ፡፡ በሒደቱ ኤጀንሲው የሚያስፈልገውን  ነገር እያሟላ ግብርና ሚኒስቴር ዕቅዱን እንዲያሳካ ያግዛል፡፡ እኛ እንደ ሲነርጎስ በአራተኛው ማለትም ተቋማዊ አቅም ግንባታ ላይ ግብርና ሚኒስቴርንም ሆነ ኤጀንሲው ያቀዱትን ዕቅድ እንዲያሳኩ የመርዳት ሥራ እንሠራለን፡፡ እነሱ በሚፈልጉት ልክ እናግዛለን፡፡ ለምሳሌ ግብርና ሚኒስቴር ሁለት ነገሮችን ጠይቋል፡፡ የሰው ሀብት ስትራቴጂን ጠይቋል፡፡ ይህንን ስትራቴጂ በሲነርጎስ በኩል ሠርተን ጨርሰናል፡፡ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ሊያሳካለት የሚችል የሰው ኃይል አለው ወይ? የሚለው ተሠርቷል፡፡ ይኼ የሚያሳየው ዕቅዱን ለማሳካት ግብርና ሚኒስቴር ከበፊቱ ለየት የሚልበት አንዱ አካሄድ ይኼ ነው፡፡ ወደ ውስጥ አይቶ ይኼ ኃይል ያስፈልገኛል በማለት ወደፊት ለመንደርደር እየተዘጋጀ ነው ማለት ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ አሁን እያደረግን ያለነው የክልል ግብርና ቢሮዎችና ሚኒስቴሩ የተቋማዊ አቅም ምን ይመስላል የሚለውን አብረን አይተናል፡፡ ክፍተቶችን ለማየት የሚያስችሉ ጥናቶችን ለማድረግ ለአማካሪዎች ሰጥተናል፡፡ በሔክታር ምርታማነቱን 18 ወይም 20 ኩንታል በማድረግ ካለፈው ዕቅድ ይበልጥ ለመጨመር መታሰቡ በጥራትም በብዛትም ለየት ያለ ነው፡፡ እዚያ ለመድረስ ምን ያስፈልጋል የሚለው ላይ ካለፈው ይልቅ ስትራቴጂካዊ አካሄድ ይታያል፡፡ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ያሉትን ክፍተቶች አንጥረን እናወጣና የመሙላት አቅም ምን እንደሚመስል እናያለን፡፡

ሪፖርተር፡- ስለግብርና ዘርፍ ስንነጋገር አንድ ለየት ያለው ነገር የአነስተኛ ገበሬዎች ምርታማነትን የመጨመር ዕቅድ በንፅፅር እየተሳካ ይመስላል፡፡ ሆኖም ግን በሰፋፊ እርሻዎች ላይ የግሉን ዘርፍ ለማስገባትና ውጤት ለማግኘት ሰፊ የእርሻ መሬት ቢዘጋጅም፣ አነስተኛ ገበሬው የደረሰበት ጫፍ ሊደርስ አልቻለም፡፡ መሠረታዊ ችግሩ ምንድነው ብለው ያስባሉ?

አቶ አበራ፡- የአገራችንን ተጫበጭ ሁኔታ ማየት ጠቃሚ ነው፡፡  ዝም ብለን ያለንን ሀብትና ጥሪት ሰፋፊ እርሻ ላይ ማዋል ነው የሚሻል ወይስ አነስተኛ ገበሬው ላይ በምርታማነት መልኩ ማዋል ነው የሚሻለው የሚለው አመለካከት ነው፡፡ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ጀምሮ በደርግም የመንግሥት እርሻዎች የተሠሩ አሉ፡፡ ይኼ መንግሥትም ለተለያዩ ሰዎች በርካታ ማበረታቻዎችን በመስጠት ሰፋፊ እርሻዎችን ለመሳብ ተሞክሯል፡፡ ነግር ግን ይህን ያህል ውጤት ያመጡልን አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ያለን አማራጭ ወይም ደግሞ ትክክኛው አመለካከት አነስተኛውን ገበሬ ይበልጥ ምርታማ ማድረግ ነው፡፡ ቴክኖሎጂና ኢንቨስትመንት ጨምረንለት መሬቱን የበለጠ ምርታማ ብናደርገው፣ በሳይንሳዊ መንገድ ብንቃኘው የአገራችንን የምግብ ዋስትና እናስጠብቃለን፡፡ እስራኤልን፣ ሌሎችም እንደ ኮሪያ ያሉትን ስናይ የመሬትና የሰው ምርታማነት ፍላጎትን ለመሸፈን ተችሏል፡፡ ሲነርጎስም ይህንን ነው የሚያግዘው፡፡ ወደ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የዞረውና ክላስተር ስትራቴጂ የምንለው አሠራርና የሸቀጥ ንግድ ካላስተር የሚባል አካሄድ አለ፡፡ ለምሳሌ ብናይ የቢራ ገብስን ምርታማነት ለማሻሻል ከሌላ ነገር ሳይደባለቅ በራሱ ብቻ በተከለለ አካባቢ ኢንቨስት ተደርጎበት ማስኬድ ማለት ነው፡፡ ምርቱ ብቻም ሳይሆን ወደ ማቀነባበሩ ከዚያም ወደ እሴት ጭመራ ከገበሬው ወደ ፋብሪካ እየሄደ የሚስፋፋበትን መንገድ እያየን ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት 16 የግብርና ሸቀጦችን ለይተናል፡፡ በሁለት ዓመት ውስጥ ለውጥ ያመጣሉ ተብለው የተያዙ የግብርና ምርት ሸቀጦች ናቸው፡፡

ሰሞኑን እኔው ራሴ የተሳተፍኩበት የስንዴ ምርት ክላስተር ሆሳዕና ላይ አቋቁመናል፡፡ ምንድነው? የተደረገው ሆሳዕና አካባቢ የሚመረተውን የስንዴ ምርት እንዴት መጨመር ይቻላል የሚለው ታይቷል፡፡ ለዚህ ግብርና ሚኒስቴርና ሌሎች ተቋማት ኃላፊነት አላባቸው፡፡ ከምርት ቀጥሎ ግን ማቀነባበሩ መቀጠል አለበት፡፡ ወፍጮ ቤቶች መኖር አለባቸው፡፡ ከዚያ በኋላ እንደ ፓስታ፣ ማካሮኒ እያደረጉ የሚያመርቱ ፋብሪካዎች መኖር አለባቸው፡፡ ሌሎችም እንዲሁ፡፡ ይህ በሆሳዕና አካባቢ ነው እንዲሆን የሚጠበቀው፡፡ ይህንን ለመፍጠር በሆሳዕና አካካቢ በስንዴ ላይ ባለድርሻ የሆኑ እንማን ናቸው የሚለውን አይተናል፡፡ ጥሩ አምራች ገበሬዎች አሉ፡፡ ማኅበራት አሉ፡፡ ምርጥ ዘር የሚያቀርቡ አሉ፡፡ የግልም የመንግሥትም የሆኑ ማዳበሪያ የሚያቀርቡ ድርጅቶች፣ ከዚያም ባንኮችና አነስተኛ ገንዘብ አቅራቢ ድርጅቶች ይኖራሉ፡፡ ወፍጮ ቤቶች አሉ፡፡ እነዚህን አንድ ላይ ለማምጣት ችለናል፡፡ ከሃምሳ በላይ ባለድርሻዎችን በስንዴ ዙሪያ ኑሯቸውን የገነቡ ናቸው፡፡ ከዚህ በፊት እነዚህ ይረሱ ነበር፡፡ እነዚህ ከተረሱ ደግሞ ማቀድ አይቻልም፡፡ አሁን ያደረግነው ምንድነው? ገበሬውን ምን ያህል ማምረት እንደሚችል፣ ባንኮችና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት በዚህ አካባቢ ለስንዴ ምን ያህል ገንዘብ ሊያበድሩ እንዳዘጋጁ፣ ምን ያህል ምርጥ ዘር እንዳለ፣ ምን ያህል ማዳበሪያ እንዳለ፣ ገዥውም ምን ያህል ቶን መግዛት እንደሚችል፣ ወፍጮ ቤቱን ምን ያህል መፍጨት እንደሚችሉ አጥንተን ዝርዝር ዕቅድ አወጣን፡፡ በሆሳዕና አካባቢ ስለ ስንዴ መረጃ የሚፈልግ ካለ ዝርዝር ሒደቱን ለማወቅ ቀላል ይሆንለታል ማለት ነው፡፡ ገንዘብ ለማምጣትም ቀላል ይሆናል፡፡ ኢንቨስተር መጥቶ ስንዴ ላይ ሊሠራ ቢፈልግ ይቀለዋል፡፡ ባንኮች ብድር አስቀምጠዋል፡፡ ለጋሾችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለኅብረት ሥራ ማኅበራት ገንዘብ መስጠት ይፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን በምን መልኩ እንደሚሰጡ አያውቁም ነበር፡፡ የግሉ ዘርፍ ስንዴ ወደ ማምረት ወይም ሩዝ ወደ ማብቀል መግባት የለበትም፡፡ የሩዝ ፋብሪካውን ግን መክፈት ይችላል፡፡ አቅራቢ ስላለው፡፡ ከአሁን በኋላ አቅራቢ አጣለሁ ብሎ አይጨነቅም፡፡ ክላስተሩ ከተፈጠረ ምን ያህል ስንዴ በየዓመቱ እንደሚኖረው፣ ምርቱ የሚጠፋም ከሆነ በምን ያህል እንደሚጠፋ፣ የሚጨምር ከሆነም በምን ያህል እንደሚጨምር ቀደም ብሎ ያውቃል፡፡ ብዙ ምሳሌዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ በኬንያ የአናናስ እርሻን አይቻለሁ፡፡ በየሱፐር ማርኬቱ የምንገዛው የታሸገ አናናስ ከኬንያ የክላስተር አመራረት የተገኘ ነው፡፡ በዚህ ኬንያ ጥሩ ውጤት አስመዝግባለች፡፡ የአናናስ ክላስተር አላቸው፡፡ የማንጎና የአቮካዶ ክላስተር አላቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ከስንዴ ባሻገር ለክላስተር የተመረጡ የግብርና ምርቶች የትኞቹ ናቸው?

አቶ አበራ፡- ሰሊጥ፣ የብቅል ገብስ፣ በቆሎ ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ፣ ቦሎቄ በደቡብ ክልል አለ፡፡ በእነዚህ ሠርተን ለማየት እንችላለን፡፡ ለበርበሬ ማረቆን መውሰድ እንችላለን፡፡ በርበሬ ላይ እሴት በመጨመር ተዓምር መሥራት ይቻላል፡፡ በተለያየ መንገድ እያሸግን ቅመም ያለው፣ ቅመም የሌለው፣ ወዘተ. እያልክ ለውጭ ሳይቀር ኤክስፖርት ለማድረግ የሚያቃጥልና የማያቃጥል በማድረግ ለገበያ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ፋብሪካዎች በዚህ መንገድ አንዱን ምርት በብዙ ዓይነት እሴት በመጨመር ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ ለመድኃኒትነት ሊያቀርቡት ይችላሉ፡፡ አሜሪካኖች ከማሽላ ሰላሳ ዓይነት ምርት ያወጣሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ለኢንዱስትሪ መነሻ ይሆናል ማለት ነው?

አቶ አበራ፡- በጣም እንጂ፡፡ ገበሬውን ሳናፈናቅል ውጤት ማምጣት እንችላለን፡፡ አሁን ያለውን የገበሬውን ገቢ ካሳደግህ፣ ገበሬውም ልጁን ማስተማር ከቻለ መሬቱ ላይ ልጁ አይቆይም፡፡ ኮሌጅ ገብቶ ትምህርቱን ካጠና ወደ ኢንዱስትሪ ወይም ወደ አገልግሎት መስክ ይገባል ማለት ነው፡፡ ወደ ሌላ ዓለም ነው የሚያቀናው፡፡ በማሳው ላይ የገበሬውን ሕይወት ብትቀይር፣ ግብዓት ብትሰጠው፣ ገበሬው ልጆቹን ካስተማረ፣ ኑሮውን ከቀየረ፣ ጤናማ ከሆነ፣ መሬቱ ላይ የሚቆየው ሰው እያነሰ ይሄዳል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለግብርና ስንነጋገር ስለግብርና ኤክስፖርት ዘርፍ እናነሳለን፡፡ በዚህ መስክ ቡና ይነሳል፡፡ በኦክስፋም ቆይታዎ የቡና ባለቤትነት መብትን ለማስከበር ከ13 ዓመት በፊት የተካሄደው ዘመቻ ይታወሳል፡፡ ያኔ የነበረው ችግር ምን ነበር? ዘመቻውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመክፈት የተነሳችሁበት ዓላማ ምን ነበር?

አቶ አበራ፡- በኦክስፋም የከፈተው ዘመቻ ‹‹ኦክስፋም ሜክ ትሬድ ፌር›› የሚል መጠሪያ ይዞ ነበር የወጣው፡፡ ይህንን ይዞ የወጣው የዓለም የንግድ ሥርዓት ፍትሐዊ አይደለም፣ ለሀብታሙ የሚያደላና ደሃውን የበለጠ ደሃ የሚያደርግ ነው የሚል መነሻ በመያዝ ነው፡፡ በወቅቱ በተደረገ ጥናት መሠረት እኛ ጥሬ ዕቃ ለበለፀገው ዓለም እናቀርባለን፡፡ እንደ ቡና፣ ሰሊጥ፣ ቦሎቄ፣ ጥጥ፣ የመሳሰሉትን ጥሬ ዕቃዎች ለፋብሪካዎቻቸው እንሰጣለን፡፡ እነሱ ግን የፈለጋቸውን ዋጋ ነበር የሚሰጡን፡፡ ዋጋ ተቀባዮች በመሆናችን የሰጡንን እንቀበል ነበር፡፡ ይኼ ፍትሐዊ አይደለም፡፡ ሌሎችም በርካታ ሸቀጦች ነበሩ ዘመቻ የተወጣባቸው፡፡ እንግዲህ ይህንን ፍትሐዊ ያልሆነ የንግድ ሥርዓትን በመመልከት ኦክስፋም በመላው ዓለም ዘመቻ ከፍቶ ነበር፡፡ በጊዜው ድንቅ ጥናቶች ይፋ ተደርገው ነበር፡፡ የንግድ ፍትሐዊነት ዘመቻው ግን ዝም ብሎ አየር ላይ የነበረ ነው፡፡ የበለፀገው ክፍል እንዴት ደሃውን ወገን እንደሚበዘብዝ የሚሳይ ብቻ ነበር፡፡ ዘመቻውን ወደ አፍሪካ በይበልጥም ወደ ኢትዮጵያ ስናመጣው እኔ ለምመራው ቢሮ ግን ፈታኝ ሆኖብኝ ነበር፡፡ እንዴት በአንዴ ነው ተጨባጭ የማደርገው የሚለው በግሌ ፈታኝ ሆኖብኛል፡፡ በዚያን ወቅት ታስታውሱ ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ ድርቅ ገብቶ ነበር፡፡ ከድርቁ ጎን ደግሞ የቡና ዋጋ ተንኮታኩቶ ነበር፡፡ የይርጋ ጨፌ ቡና ዋጋ በኪሎ ሦስት ብር ነበር፡፡ ዲላ ሁለት ብር ከምናምን ነበር፡፡ ገበሬው በዚያን ወቅት እንደምታስታውሱት በተለይ በጅማ፣ በወለጋ አካባቢ ንብረቱን መሸጥ ሁሉ ጀምሮ ነበር፡፡ የቤቱን ጣሪያ ክዳን አውርዶ የሸጠ ገበሬ አለ፡፡ ልጆቹን ከትምህርት ቤት ያስወጣ ገበሬም ነበር፡፡ ቡና በጠቅላላው አክሳሪ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ማሰብ የቻልኩት ነገር ይህንን ተጨባጭ ነገር ወደ ዓለም ክስተት መቀየር ነው፡፡ 13 ገጽ የምትሆን ‹‹ክራይሲስ ኢን ዘ በርዝ ፕሌስ ኦፍ ኮፊ›› (በቡና ትውልድ አገር ውስጥ የተከሰተ ቀውስ) የሚል ጥናት በጅማ አካባቢ ከሌሎች ጓደኞቼ ጋር በመሆን ሠርተን ለኦክስፋም ሰጠን፡፡ ስለወደደውም የቡና ዘመቻ እናድርግ ተባለ፡፡ ስምምነት ላይ ሲደረስ ያንን ተግባራዊ ለማድረግ ‹‹ፓወር አናሊሲስ›› የምንለው ነገር አለ፡፡ ያሰብኩትን ከግብ ለማድረስ ምን ያስፈልገኛል ብለህ ታጠናለህ፡፡ በዚህ ጥናት መሠረት ባለቤቱ መንግሥት በመሆኑ መንግሥት በምን ያህል ደረጃ መሳተፍ አለበት ብለን አየን፡፡ የመጀመሪያ ያደረግሁት የወቅቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ማማከር ነበር፡፡ በጣም አመኑበት፣ ወደዱት፡፡ እንዲያውም አብረን እንደምንሠራና ይኼን ነገር በተፈለገው ደረጃ እንድንሄድበት ትልቅ ድጋፍ ሰጡን፡፡ ያንን ድጋፍ ካገኘን በኋላ ገፋንበት፡፡

የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ የቡና ኮንፈራንስ አዲስ አበባ ላይ ጠራን፡፡ በዚያ ኮንፈረንስ ላይ በዓለም ላይ የታወቁትን ቡና ቆዪዎችንና ገዥዎችን ጋበዝን፡፡ ክሳራሊ፣ ኔስሌ፣ ስታርባክስ፣ ፕሮክተር ኤንድ ጋምብል፣ እነዚህ የመሳሰሉ እነ ኮፕሬቲቭ ኮፊ የሚባሉትን ተቋማትንና በዓለም ላይ አሉ የሚባሉትን የቡና ገዥዎች ጋበዝን፡፡ ከሚዲያ እንደ ቢቢሲ፣ ሲኤንኤን፣ ሮይተርስ የመሳሰሉትን፣ ከአገር ውስጥ ያሉትን ያህል ጨምሮ 160 እንግዶች ተጠርተው ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች ከመጡ በኋላ ሁለት ቦታ በመክፈል አንደኛው ጅማ ጮጬ በሚባለውና ቡና ተገኘ ወደሚባልበት አካባቢ እንዲሄድ አደረግን፡፡ ሁለተኛውን ቡድን ይርጋ ጨፌ ሲዳሞን እንዲያይ አደረግን፡፡ የሚያዩት ቡና ምን እንደሚመስልና የቡና ገበሬ ሕይወት ምን እንደሚመስል እንዲያዩ ወደ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍል ላክን፡፡ በወቅቱ የግብርና ኃላፊ የበነሩት የአሁኑ ኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሙክታር ከድር ነበሩ፡፡ በዚህ በደቡብ ክልል ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የወቅቱ የክልሉ ፕሬዚዳንት ስለነበሩ፣ የገበሬ ሕይወት ምን እንደሚመስል ለጎብኚዎች አሳይተዋቸዋል፡፡ ጉብኝታቸውን ጨርሰው ሲመጡ ኮንፈረንሱን አዘጋጀን፡፡ በስብሰባው ላይ ገበሬውን በመወከል እንዲናገሩ ያደረግነው ከጎብኚዎቹ መካከል ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጠንካራ ንግግር በማድረጋቸውም እስካሁን ድረስ በፍትሐዊ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ይጠቀሳል፡፡ ይህ ሒደት ዓለም አቀፍ ተሰሚነት አስገኘ፡፡ የኢትዮጵያ ቡና አስገኚነት በስፋት ተወራለት፡፡ ሚዲያውም፣ ኮሌጆችም ስለኢትዮጰያ ማውራት ጀመሩ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ለውጦች ታዩ፡፡ የቡና ዋጋም መነሳት ጀመረ፡፡ ደስ የሚለው ሌላው ነገር መንግሥት ገበሬው ቡናውን ወደ ውጭ እንዲልክ መፍቀዱ ነበር፡፡ በዚያ ሰሞን አንድ ኮንቴይነር የገበሬ የቡና ከኅብረት ሥራ ማኅበር በኦክስፋም አማካይነት ወደ አሜሪካ ወጥቶ ነበር፡፡ ይኼ ጅማሮ ነበር፡፡ የዘመቻና አድቮኬሲ ኃይል ምን ያህል እንደሆነ ለመጥቀስ ያህል ነው፡፡ የአገር ውስጥ ሚዲያዎች ገበሬው ቡና ስላላዋጣው በቡና ምትክ ጫት እንዲተክል ሲጠይቁም ነበር፡፡ ይኼ ግን ትክክለኛ አለመሆኑን በማስረዳት በቆሎም ሆነ ጫት ጊዜያዊ በመሆኑ የቡናን ያህል ውጤት አያመጣም ብለን በመከራከራችን ቡናችን ለማንሰራራት ቻለ፡፡

ሪፖርተር፡ ከዚሁ ከፍትሐዊ የንግድ አሠራር ማስፋን ጋር የተያያዘ ዘመቻ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ትልቅ ምዕራፍ ተብሎ የሚጠቀሰው ኔስሌ ከሚባለው ኩባንያ ጋር የነበረው ከፍተኛ አለመግባባት ነው፡፡ ከስታርባክስ ጋር በቡና ባለቤትነትና መገኛነት ላይ የነበረው ጥያቄም ዓለም አቀፍ መነጋገሪያ ነበርና ይህንን ሒደት ቢያስታውሱ?

አቶ አበራ፡- ያ ዘመቻ በተወሰነ ደረጃ ለኢትዮጵያ መንግሥት የአግባብነት ዕድል ሰጠው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ድሆችና ዕድል ያላገኙትን በመወከል በተናገረ ቁጥር አድማጭ አገኘ፡፡ አቶ መለስ በብዙ መድረኮች ላይ ይህንን በሚመለከት ተናግረዋል፡፡ በብዙ አገሮች ተጋብዘው አስተጋብተዋል፡፡ የእኛ  ዩኒየንና ማኅበራት በአሜሪካ ኮንግረስና በኋይት ሃውስ ቤተ መንግሥት ሄደው ተናግረዋል፡፡ በአውሮፓ ፓርላማ ተገኝተው ተናግረዋል፡፡ በኦክስፋም ድጋፍ ማለት ነው፡፡ ይኼ ሲሆን ግን ትልቅ ችግር የፈጠረብን ኔስሌ ኩባንያ ነው፡፡ ይህ ኩባንያ ቡና ብቻም ሳይሆን ሌሎች ምግቦችንም ያመርታል፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ የጀርመኖች ንብረት የነበረ ትልቅ የሥጋ ፋብሪካ ነበር፡፡ ያንን ፋብሪካ ከባለሀብቶቹ ኔስሌ ገዝቶት ነበር፡፡ ኔስሌ ከመግዛቱ በፊት ግን ፋብሪካውን የደርግ መንግሥት ይወርሰዋል፡፡ ወርሶትም ግን ካሳውን ልክፈል ብሎ ነበር፡፡ ይኼንን ፋብሪካ ስታቋቁሙ ምን ያህል ሀብትና ንብረት ኢንቨስት እንዳደረጋችሁ ስለምናውቅ ያንን ገንዘብ እንስጣችሁ በማለት ደርግ ያቀረበውን ጥያቄ ባለንብረቶቹ ሳይቀበሉት ቀሩ፡፡ ጉዳዩ እየተጓተተ እስከዚህ መንግሥት መጥቷል፡፡ የኢሕኣዴግ መንግሥትም ልክፈል እያለ ነው፡፡ ኔስሌ ከገዛውም በኋላ መንግሥት ልክፈል ብሎ ነበር፡፡ እነሱ ግን እምቢ በማለት ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ወስደውታል፡፡

ሪፖርተር፡- እምቢ ያሉበት ምክንያት ግን ምንድን ነበር?

አቶ አበራ፡- ሰዎቹ ፋብሪካውን ሲያቋቁሙ ያወጡት ገንዘብ ስምንት ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ቢሆን ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ያንን ልክፈል እያለ ነው፡፡ እነሱ ግን አሁን ባለው የገበያ ዋጋና አሁን ባለው የዶላር ምንዛሪ ክፈሉን ነው የሚሉት፡፡ ገንዘቡ አሁን ሄዶ ሄዶ ወደ 160 ወይም 170 ሚሊዮን ዶላር ክፈሉን እያሉ ነው ማለት ነው፡፡ ይኼ ነው አስቸጋሪው ነገር፡፡ ለዚያ ኩባንያ ይህንን ያህል መክፈሉ አግባብ አይደለም ነው የመንግሥት አቋም፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ይኼው እንደደረሰን ከኦክስፋም ዘመቻ አዘጋጆች ጋር ተወያየንበት፡፡ ኦክስፋም ለዓለም ይፋ እናደርገዋለን ብለን በመወሰን ተዘጋጀንበት፡፡ ኔስሌ ምንም ነገር ሳይሰማ ቢያንስ በ14 ትልልቅ ከተሞች ውስጥ እንደ ስዊዘርላንድ፣ ኔዘርላንድስ፣ ጀርመን፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ እንግሊዝ፣ አሜሪካ ሁሉ ላይ አጠናክረን ዘመቻውን የሚያካሂዱ አዘጋጅተን ኔስሌ ምንም በፈረጆቹ ገና በዓል ወቅት መልዕክቱን ለዓለም አወጣን፡፡ ድርቅ ባለበት አገር ኔስሌ ብር ክፈሉኝ ይላል የሚል ዘመቻ ተከፈተ፡፡ በጣም ኃይለኛ መልዕክት ነበር፡፡ በቀጣዩ ጠዋት የኔስሌ ገበያ ዘጭ አለ፡፡ በመጀመሪያ ስብሰባው የቦርድና የማኔጅመንት ሰብስብ የኢትዮጵያ መንግሥት ገንዘቡን መክፈል አለበት አለ፡፡ ምክንያቱም በርካታ ኢንቨስትሮች ንብረታችን ይወረሳል ብለው ስለሚፈሩ ብዙ እንዲመጡ ከፈለጋችሁ ይህንን ገንዘብ መክፈል አለባችሁ አሉ፡፡ እኛ ግን የቤት ሥራችንን ሠርተን ነበር የሄድነው፡፡ በወቅቱ ወደ ኢትዮጵያ የመጣ ኢንቨስተር እንደሌለ ስናሳውቅ ከበፊቱ የበለጠ ሕዝብ ወጣ፡፡ ኔስሌ ችግር ውስጥ ገባ፡፡ ጊዜው የገና በዓል ነው፡፡ ስለዚህም ቦርዱ እንደገና ተሰብስቦ ሲያቀርብ የነበረውን የገንዘብ ጥያቄ አነሳ፡፡ እኛ በጠየቅነው መሠረት ሲሆን ያ ገንዘብ እዚህ ለሰብዓዊ ሥራዎች እንዲውል ጠይቀን ነበር፡፡ በኔስሌ ምክትል ፕሬዚዳንት የሚመራ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ እንልካለን ብለው ወሰኑ፡፡ በድብቅ አምስት ልዑካን ወደ ኢትዮጵያ መንግሥት መጡ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም ይህንን አሳውቆኝ ስለነበር መምጣታቸውን ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ኔስሌ እኔንና ኦክስፋምን ይጠላ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ምክትል ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ሙሉ ቀፀላ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትን የወከልነው እኔና እሳቸው ነበርን፡፡ በዚያው ስምምነት ተደረሰ፡፡ ተፈራርመን ገንዘቡንም ሰጡ፡፡

ሪፖርተር፡- ከስታርባክስ ጋር የነበረው ሁኔታስ እንዴት ተስተናግዶ ነበር?

አቶ አበራ፡- የሁለት ዓመት ዘመቻውን ካደረግን በኋላ እንደ አዕምሯዊ ንብረት የኢትዮጵያ ቡናዎችን ማንም ሰው እንዳይወስዳቸው አሜሪካ ውስጥ በሚገኘው ጽሕፈት ቤት ለማስመዝገብ በኦክስፋም በኩል ተንቀሳቀስን፡፡ ይርጋ ጨፌንና ሐረርን አስመዘገብን፡፡ ሲዳሞን ስንል ባለቤት አለው ተባልን፡፡ ማን እንደሆነ እንዲነግሩን ስንጠይቅ ሚስጥር ሊያደርጉት ፈለጉ፡፡ ባለቤቱን ንገሩን፣ ዝርፊያ ተካሂዷል ማለት ነው ብለን ወጠርናቸው፡፡ ኋላ ላይ ባለቤቱ ስታርባክስ መሆኑን ነገሩን፡፡ ይህንን ስናውቅ ተቸገርን፡፡ ምን እናድርግ የሚለውን ስናስብ ነው፡፡ የአሜሪካ ትልቅ ኩባንያ በመሆኑ ቡና አልገዛም ቢል ገበሬዎችን ይጎዳ ይሆን የሚሉ ጥያቄዎች አስጨነቁን፡፡ ስለዚህ ይኼንን ወደ አንድ ዕርምጃ ከመሄዳችን በፊት ሲያትል ሄደን ስታርባክሶችን አነጋገርን፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ዳግ ሃል የሚባሉትን ሰው አግኝተን አነጋገርናቸው፡፡ በጥሩ መንፈስ አልተቀበሉንም፡፡ ሽማግሌም ላክንባቸው፡፡ ይኼ ነገር አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል አልናቸው፡፡ ፈቃዱና ባለቤትነቱ የኢትዮጵያ ቢሆን ምንም የሚጎዱት ነገር የለም ብለን ብናስረዳም አልተቀበሉም፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ሞከርን ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ሦስተኛው ላይ ጠንካራ የሆነው ችግር ኦክስፋም አሜሪካ በአሜሪካ ድርጅቶች ላይ ዘመቻ ለማድረግ አለመቻሉ ነው፡፡ የኦክስፋም በጀት የአሜሪካ ሕዝብ በጀት ስለሆነ መልሰህ በዚያው ገንዘብ በአሜሪካ ኩባንያ ላይ ዘመቻ ማድረጉ ነበር አስቸጋሪው፡፡ ቦርዱ ቢቸገርም ደስ የሚለው ነገር በመጨረሻው የእኛ መከራከሪያ ጠንካራ ስለነበርና ኦክስፋም ለመብት ተቆርቋሪ ነኝ ስለሚል፣ የገበሬው ድምፅ ነኝ ስለሚል መቆየም የለበትም የሚለው መከራከሪያም ስለበለጠ የኦክስፋም ቦርድ ዘመቻ እንዲከፈት ፈቀደ፡፡ አሁንም ይህንን ዘመቻ ከመንግሥት ጋር ነው አብረን የሠራነው፡፡ ይበልጡን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ነበር፡፡ ከባድ ሥጋትም የነበረው ነው፡፡ ቡናችንን አልገዛም ሊል ይችላል የሚል ሥጋት አለ፡፡ ስለዚህ ስትራቴጂካዊ ሆኖ መሄድ ያስፈልግ ስለነበር በእሳቸው ምክር ነበር እያንዳንዱን ዕርምጃ የምንሄደው፡፡ ሁሉም የመንግሥት አካል ከታች እስከ ላይ ዝግጁ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ከዘመቻው በኋላ የመጣውን ሁላችንም እናስታውሳለን፡፡ ለመሆኑ የቡና ባለቤትነት መብቶችን አስመዝግበን ጨርሰናል? ምን ያህል የቤት ሥራችንን ሠርተናል? አገር በቀል በሆኑ ምርቶች ላይ ምን የሠራነው ነገር አለ?

አቶ አበራ፡- ብዙ የተሠራ አለ፡፡ የዘመቻው አንዱ ውጤት የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ጽሕፈት ቤት እንዲቋቋም ማስቻሉ ነው፡፡ እየሠራ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ተቋም ምን ያህል ጠንካራ ነው? ምን ያህል አቅምና ትኩረት ተሰጥቶታል? ለሚለው ብዙ የማውቀው ነገር የለም፡፡ ጽሕፈት ቤቱ እንዳለና ብዙ ጠንካራ ሰዎች በውስጡ እንዳሉ አውቃለሁ፡፡  እንግዲህ የአቅም ጉዳይም አለ፡፡ ይህንን ስንል ያሉንን ሀብቶች ማስመዝገብ መቻል ነው፡፡ ይኼ የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊነት ነው፡፡ ገብስ፣ ስንዴ፣ ጤፍ ወዘተ. ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህን ማስመዝገብ የዚህ ጽሕፈት ቤት ኃላፊነት ነው፡፡ እነዚህ ሀብቶች ናቸው፡፡ ብዙ ነገሮችን ከጭቅጭቅ ማዳን እንችላለን፡፡ ልክ የጤፍ ጉዳይ አከራካሪ እንደሆነው ማለት ነው፡፡ አንዳንዴ በእነዚህ ዙሪያ የምንሠራቸው ስህተቶች አገርን ሊጎዱ ይችላሉ፡፡ ጠልቄ ባላውቀውም በጤፍ ላይ የተሠራ ስህተት አለ ብዬ አምናለሁ፡፡ ጤፍ ለሆላንዶች በሰዎች ጫና ሲሰጥ ሒደቱን መከታተል የብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ኃላፊነት ነበር፡፡ ኢንስቲትዩቱ ጤፉ እንዲሰጥ በሚፈቅድበት ጊዜ በርካታ ነገሮች መታየት ነበረባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ከቡና ሳንወጣ በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ኤክስፖርት ላይ እየወረደ የመጣ አፈጻጸም እያየን ነው፡፡ በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት ለቡና አስከፊ ጊዜያት እንደነበሩ ታዝበናል፡፡ መሠረታዊ የቡና ዘርፍ ችግሮች ምንድን ናቸው? ወደ ምርት ገበያ ከገባ በኋላ ቡና ለውጥ አምጥቷል የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ የእርስዎ አመለካከት ምንድነው?

አቶ አበራ፡- እንደ ግለሰብ ወይም ዘርፉን እንደሚወድ ሰው ለመናገር ያህል፣ እንደ እኔ የቡና ትልቁ ውጤቱ ልማቱ ነው፡፡ ባለፈው ዘመን በቡናና ሻይ ልማት ተቋም በኩል በጥሩ ሁኔታ ሲጓዝ ነበር፡፡ አንቱ የተባሉ ሰዎች ይሠሩበት የነበረ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቡና ላይ የሚሠሩ አዋቂዎች አሉን፡፡ በጥናቱም ሆነ በሌላውም በኩል፡፡ የአዋቂዎች እጥረት አልነበረብንም፡፡ መንግሥትም ትኩረት ሰጥቶት ሲሠራበት፣ ለብዙ ዓመታትም ጠንካራ የሚባሉ እንደ ከፋ የቡና ማበጠሪያ ያሉት ተቋማት ተመሥርተው ነበር፡፡ ቅምሻና ሙከራ የምናደርግባቸው ተቋማትና አንቱ ተባሉ የቡና ጣዕምን አብጥርጥረው የሚያውቁ ሰዎች ነበሩን፡፡ ጠንካራ የነበሩትን ተቋማት ይብልጥ አጠንክረን መቀጠል ነበረብን ነው የእኔ አቋም፡፡ በዚህ አቋሜ ከብዙ ሰዎች ጋር ላልስማማ እችላለሁ፡፡ ቡናችን ብዙውን የውጭ ምንዛሪ የምናገኝበት እስከሆነ ድረስ እንደ ዋዛ መታየት አልነበረበትም ብዬ አምናለሁ፡፡ ያኔ የነበሩትን ጠንካራ ተቋማት እየገነባን መሄድ ነበረብን፡፡ እንዲሁ ወደ ግል ለማዛወር ብቻ ማሰብ አልነበረብንም ነው የእኔ አቋም፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ቡና ወደ ምርት ገበያ መግባቱ ለእኔ የሚያሳምምና ከባድ አደጋ ነበር፡፡ በወቅቱ ከሚቀርቡኝ ባለሥልጣናት፣ ከማውቃቸው አጋሮች፣ ቡና ውስጥ ካሉ ላኪዎችና ጥናት አጥኚዎችም ጋር የተነጋገርነውና ከመሆኑም በፊት ስንለምን የነበረው እባካችሁ ቡናን ወደ ምርት ገበያ አታስገቡ፣ ምርት ገበያው ስንዴውን፣ በቆሎውን የመሳሰሉ ጥራጥሬውን ተከትሎ ይሂድ ብለን ነበር፡፡ የኢትዮጵያን ወገብ ይዞ የማይኼደውን ዘርፍ በምርት ገበያው እንከተል ብለን ነበር፡፡ ቦሎቄ ባይመረት የምናጣው ትንሽ ነገር ነው፡፡ በቆሎ ተመጋቢ ሕዝብ ቢኖረንም የቡናን ያህል ስለማይጎዳን፣ ቡና ብዙ ነገራችንን የሚይዝ ስለሆነ በነበረው ተቋማዊ አሠራር እንዲቀጥል ነበር ውትወታችን፡፡ የፈራነው ደረሰ፡፡ አንደኛ ለዘመናት የቆየውን ተቋም ምርት ገበያው ለመምራት ምን ዓይነት ተቋማዊ ብቃትና አቅም አለው የሚል ነበር ሙግታችን፡፡ ሁለተኛ ባለድርሻዎቹን በምትረብሽበት ጊዜ የምትከፍለው ዋጋ አለ፡፡ የቡና ዋጋ ቀነሰ ያልከው እየከፈልን ያለነው ዋጋ ነው፡፡ ባለድርሻ ስንል ገዥ፣ አቅራቢና አምራቹ አለ፡፡ ሁሉም ወደ ምርት ገበያ ይምጣ ሲባል ተረብሿል ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው ሁለት ሦስት ዓመት ኪሳራ የታየው፡፡ በግሌ ምርት ገበያ ቡናውን ባይዝ ኖሮ ቡናችን አሁን ያጣውን ዋጋ አያጣም ነበር የሚል ዕምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ቡናን በተመለከተ መንግሥት ወደ ሌላ ዓይነት ተቋማዊ አደረጃጀት እየሄደ ነው፡፡ ቀድሞ እንደነበረው የቡናና ሻይ ልማት ተቋም በግብርና ሚኒስቴር ሥር ሆኖ እንዲመሠረት ታስቧል፡፡ ይህ መደረጉ የቡናውን ዘርፍ ለማንሰራራት ያግዛል ይላሉ?

አቶ አበራ፡- መልሶ ቢቋቋም ደስ ይለኛል፡፡ በባለሥልጣን ደረጃ ቢደራጅ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ነገር ግን ምንድነው የሚሠራው ነው ጥያቄው፡፡ ሁለት ነገሮችን ቢሠራ ደስ ይለኛል፡፡ አንደኛው ልማቱን ነው፡፡ እንደ ዱሮው ቡና ላይ አተኩሮ በባለቤትነት ልማት ማካሄድ ነው፡፡ ምርትን የመጨመር፣ ጥራቱን የመጨመር፣ የጥናት መሠረቱን የማስፋት፣ ከክልሎች ጋር ተዛምዶ በመሥራት ውጤት ሊመጣ ይችላል፡፡ እንደ ተጨማሪ ቢሆን የምመኘው ግን የንግዱንም ክፍል ቢይዝ ነው፡፡ ውጭ የሚሸጡ ቡናዎች ምን ያህል ሸጥን? ምን ያህል አተረፍን? የሚሉትን ለማየት ጭምር ቢደራጅ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ያውቁታል፡፡ ልምዱም አለ፡፡ በቅርቡ የስታርባክስ ሰዎች ቢሮዬ መጥተው ሳነጋግራቸው ነበር፡፡ በዚሁ በተባለው ተቋማዊ አደረጃጀት ላይ አውርተናል፡፡ ተዓማኒነትና መተማመንን እንደገና ለመገንባት ይችላሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ በርካታ ገዥዎች ስታርባክስን ጨምሮ ዕምነት አጥተዋል፡፡ የተሰጠንን ቡና ብቻ ነው የምንገዛው፡፡ ቡናው የትና እንዴት እንደተመረተ (ትሬሰብሊቲ) ለማወቅ ሳንችል እየገዛን ነው እያሉ ነው፡፡ ለዚህ ነው አሁን ወደ አምራቾቹ፣ ወደ አራሾቹ፣ ወደ ኅብረት ሥራ ማኅበራቱ አዳልተው ቡናውን የሚገዙት፡፡ በትንሹም ቢሆን ይሻላል ብለው እየገዙ ነው፡፡ እሱንም ቢሆን ግን በጥርጣሬ ነው፡፡ ቡናችንን በብዛት ስንሸጥ የነበረው በዋናው በቀጥታው መንገድ ነበር፡፡ የሚያመጣው ገንዘብም ይኼ የተሻለ ስለሆነ በብዛት የሚሸጥበትን መንገድ ማጠናከር ይገባል፡፡ የሚመጣው ተቋም ንግዱን እንዴት እንደሚያስኬደው ጥሩ አመራር ያስፈልገዋል የተባለው ተቋም ከተቋቋመ፣ ንግዱንም ልማቱንም አብሮ ቢሠራ ጥሩ ነው የሚል ዕምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ከግብርናው እንውጣና የፋይናንስ ዘርፉ ላይ ካለዎት ተሳትፎ የሚያያዝ ጥያቄ ላንሳ፡፡ የአሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ የቦርድ ሰብሳቢ እንደመሆንዎ በቅርቡ ከብሔራዊ ባንክ ዘርፉን ለማጠናከር፣ ኮርፖሬት ገቨርናንስን በሚመለከት አዲስ ሕግ ወጥቷል፡፡ ከአክሲዮን ባለድርሻዎችና ከሀብት መጠን ጋር በተያያዘ መመርያዎች ወጥተዋል፡፡ ገዥው ባንክ ባንኮች ካፒታላቸውን እንዲያሳድጉ ግፊት እያደረገ ነው፡፡ የዚህ ዕርምጃ ዓላማው ባንኮችን ማጠናከር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ትናንሽ ባንኮች ከትልልቆቹ ወይም በአቅማቸው ከሚመጣጠኑት ጋር እንዲዋሀዱ የሚያስገድድ ነው የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ መዋሀድን እርስዎ ይደግፋሉ ወይስ ተወዳዳሪነትን በማስፈን በርካታ ባንኮች እንዲሳተፉ ማድረጉ ይመረጣል? ሚዛኑ እንዴት ይታያል?

አቶ አበራ፡- ብሔራዊ ባንክ ያወጣው የተቋማትን ኃላፊነት የሚመለከተው ሕግ የምንደግፈውና መሆንም ያለበት ነው፡፡ አገር እየገነባን ስለሆነ በአንዱ እየገነባን በአንዱ ማፍረስ እንዳይሆን ሕጉ ጥሩ ነው፡፡ በግሌ ብሔራዊ ባንክ በተጠያቂነት መስክ ያወጣውን ሕግ እረዳዋለሁ፣ እንደግፈዋለሁም፡፡ ለምሳሌ ባንኮች ባለድርሻዎች አሏቸው፡፡ አንዳንዶቹ ዛቅ አድርገው የወሰዱ አሉ፡፡ አምስትም ስድስትም ሚሊዮን ድርሻ ያላቸው አሉ፡፡ እንደ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ያለው ዘንድ ስትሄድ በአራት ሺሕ ብር የአክሲዮን ድርሻ መግዛት ትችላለህ፡፡ አልገደበውም ማለቴ ነው፡፡ አራት ሚሊዮን የያዘውና አራት ሺሕ ብር የገዛውን ሰውዬ እንዴት አድርገህ ነው በእኩል ድምፅ የምታስተናግደው? በድምፅ ብልጫ በምታስወስንበት ጊዜ ብዙ ድርሻ ያለው ሰውዬ ከመቶ እጥፍ በላይ ድርሻ ስላለው አነስተኛው ሰውዬ ድምፁ ብዙም ተሰሚነት የለውም፡፡ ይኼንን ለማቻቻል ብሔራዊ ባንክ ያደረገውን ጥረት አድንቀናል፡፡ የቦርዱ አንድ አራተኛው ድርሻ ማለትም 12 የቦርድ አባላት ቢኖሩ አራቱ ሰዎች ይህንን ድምፅ መስጠት አለባቸው የሚለውን አመለካከት ነው ያመጣው፡፡ አራቱ ሰዎች አነስተኛ ድምፅ ባላቸው ባለድርሻዎች የተመረጡ መሆን አለባቸው ነው ያለው፡፡ እንዲህ ያሉት ነገሮች የምታበረታታቸው ናቸው፡፡ ሌሎችም የቦርድ ኃላፊነቶች መጥተዋል፡፡ ለምሳሌ የእኛን ቦርድ ብትወስድ ማንም ብድር አያፀድቅም፡፡ መቶም ሁለት መቶ ሚሊዮንም ብድር ብትጠይቅ ማኔጅመንቱ ነው የሚወስነው፡፡ ገንዘብም ሰጥተህ እንደ ቦርድ መልሰህ ራስህን ኦዲት አታደርግም፡፡ የእኛ ሥራ ኦዲት ማድረግ ነው፡፡ መከታተልና የባለድርሻውን ጥቅም ማስጠበቅ ነው፡፡ ይህንን ከአራት ዓመት በፊት ተቀብለን ስንተገብር ቆይተናል፡፡ የገጠመን ችግር የለም፡፡

ነገር ግን ቦርድ ብድር እንዲያፀድቅ የሚፈልጉ ባንኮች አሉ፡፡ እኛ አቅጣጫ እንድንቀይስ፣ ሪስክ እንድንቀንስ ነው የሚፈለገው፡፡ ሌላው ሁሉን ነገር በምክንያታዊነት ብናይ ጥሩ ነው፡፡ ሒደቱ የሚፈጥረውን ነገር ማየት ይኖርብናል፡፡ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ጠንካራ ሆኖ ለመቀጠል ካፒታሉን ማሳደግ አለበት፡፡ የአንድ ቢሊዮን ብር ካፒታል ባንክ መሆን የለበትም፡፡ ብሔራዊ ባንክ ዝቅተኛው ካፒታላችሁ 500 ሚሊዮን ብር ይሁን ብሏል፡፡ ይኼ ትልቅ ነገር አይደለም ባይ ነኝ፡፡ በአምስት ዓመት ውስጥ ሁለት ቢሊዮን ብር መድረስ አለበት መባሉም እንዲሁ፡፡ አምስት ዓመት ረጅም ጊዜ ነው፡፡ እየሠራ ያለ የፋይናንስ ተቋም ይህንን ካፒታል ማሳደግ አለበት፡፡ አለበለዚያ እየሠራ አይደለም፡፡ የአንዳንዱ ችግር ካፒታሉን ማሳደግ አይፈልግም፡፡ ለምንድነው ቢባል የትርፍ ድርሻ ክፍፍል (ዲቪደንድ) በሚደረግበት ጊዜ ክፍፍሉ የሚደረገው በካፒታል ልክ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ባንክ ካፒታሉ ሦስት ቢሊዮን ብር ቢሆንና በዓመቱ ያስመዘገበው ትርፍ ከታክስ በኋላ 300 ሚሊዮን ብር ቢሆን ይህ ትርፍ ለሦስት ቢሊዮን ብሩ ይካፈላል ማለት ነው፡፡ ወደ አሥር በመቶ ማለት ነው የትርፍ ክፍፍሉ፡፡ ሰው ሁሉ ይኼንን  አይፈልግም፡፡ ስለዚህ ድርሻዬን አልሸጥም ወይም ካፒታሌን አላሳድግም ይላል፡፡ ካፒታሉ 80 ወይም 200 ሚሊዮን ብር ቢሆን የሚያተርፈው ትርፍ 50 ከመቶ ይደርሳል፡፡ ለዚህ ሲባል ነው ባለአክሲዮኖች ካፒታል ማሳደጉን የማይፈልጉት፡፡

ነገር ግን ለባንኩ መሠረት ይሰጠዋል፡፡ ካፒታሉ ትልቅ ሲሆን በደንብ ምቾት ኖሮት ወደ ፈለገበት ኢንቨስትመንት መሄድ ይችላል፡፡ መንግሥትም ይፈቅድለታል፡፡ መንግሥት ኢንቨስት ስታደርግ ካፒታልህን ነው የሚጠይቅህ፡፡ ድጋፍ አለህ ማለት ነው፡፡ እንደ እኔ አሁን ያሉት ባንኮች መንግሥት ባስቀመጠው የአምስት ዓመት ጊዜ ገደብ መሠረት ካፒታላቸውን ያሳድጋሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ ቅርንጫፍ ማስፋፋት እኛም የገፋንበት ነው፡፡ ባንካችን ከ150 በላይ ቅርንጫፎች በመክፈት ከግል ባንኮች ሦስተኛ ነን፡፡ መንግሥት ግፉበት እያለ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ለእኛ ጥሩ ነው፡፡ በፊት ቅርንጫፍ ስትከፍት እንዴት ሳታሳውቀኝ ከፈትክ ብሎ ነበር የሚቆጣጠርህ፡፡ አሁን ግን ክፈት አግዝሃለሁ ካለ መክፈት ነው፡፡ አገር ያሳድጋል፡፡ እኔ ሳየው ቅርንጫፍ መክፈቱም ሆነ ካፒታል ማሳደጉ፣ ተቀማጭ ገንዘብ ማከማቸቱ ሁሉ አወንታዊ ነው፡፡ ሁሉም ባንክ መሥራት አለበት፡፡ መንግሥት ምን ያህል ገንዘብ ሕዝብ እጅ እንዳለ ያውቃል፡፡ ምን ያህሉ ባንኮች ዘንድ እንዳለ ያውቃል፡፡ በባንክ ውስጥ ያለው ገንዘብ ምን ያህል እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር ባልችልም፣ ኢኮኖሚው ውስጥ ከሚንቀሳቀሰው ውስጥ አንድ አሥረኛ እንኳ አይሆንም፡፡

ስለዚህ ተቀማጭ ጨምሩ ሲል ተቀማጭ ገንዘብ ለመሰብሰብ ስትራቴጂ አውጡ ማለቱ ነው፡፡ እኛ ጥሩ ልምድ አለን፡፡ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ትርፋችን ከሌሎች ባንኮች የተለየ ዓይነት ነው፡፡ ከምንሰጣቸው ብድሮች ነው የምናተርፈው፡፡ ከውጭ ባንክ አገልግሎት አይደለም፡፡ ሌሎች ትልልቅ ባንኮች ግን በዚህ መንገድ ነው የሚያተርፉት፡፡ እርግጥ ከብድር የምታገኘው ትርፍ ብዙ መንገድ ያስኬድሃል፡፡ አሥር ሚሊዮን ብር ቢኖርህ ይህንን ለአንድ ሰው ልስጥ ወይስ ለሃያ ሰው ልስጥ ብለህ መወሰን ማለት ነው፡፡ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ሁለተኛውን ስትራቴጂ ይከተላል፡፡ እነዚህን ተበዳሪዎች ኮትኩቼ ባሳድግ ነገ እያንዳንዳቸው አሥር ሚሊዮን ሊበደሩኝ ይችላሉ ብሎ ያምናል፡፡ የሚከፍለው ክፍያም የአስተዳደር ወጪ ነው፡፡ ሃያ ሰው ለማስተናገድ አራት ያህል ሰው ትቀጥራለህ፡፡ ዕድገቴ የአገርም ዕድገት ነው ብለህ ካሰብክ በዚህኛው መንገድ ነው ኢንቨስት የምታደርገው፡፡ የአሁኑ ትርፍ ላይ የአስተዳደር ወጪህ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ወደፊት ግን ትልቅ ጥቅም እንደምታገኝ አስበህ መሄድ ማለት ነው፡፡ በዓለም ላይ እንደ ኢትዮጵያ ባንኮች የሚያተርፍ የለም፡፡ ያንን ትርፍ በአገርና ወገን ላይ ኢንቨስት ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- በዘርፉ 18 የሚደርሱ ባንኮች አሉ፡፡ ወደፊት እየተዋሀደ የሚሄድ ዘርፍ ነው? ወይስ ተወዳዳሪ ሆነው ተበራክተው የሚሄዱ ባንኮች ያሉበት ዘርፍ ሆኖ ይቀጥላል ብለው ያስባሉ?

አቶ አበራ፡- አሁን ያለነውም በቂ አይደለንም፡፡ ሰፊ ዕድል አላቸው፡፡ ለመዋሀድ የባለአክሲዮኖች ጫና መኖር አለበት፡፡ ውጥረት መታየት አለበት፡፡ ብሔራዊ ባንክ ውህደትን አስመልክቶ ያወጣው ሕግ የለም፡፡ ያንን ሕግ ሲያወጣ የሆነ ነገር አስቧል ትላለህ፡፡ ኬንያ 70 ያህል ባንኮች አሏቸው፡፡ ሁሉም እየተፋፈገ እየሠራ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ያሉን 18 ባንኮች በጣም ጠንካራ እየሆኑና ራሳቸውን እያወጡ በመሄድ፣ በጥንካሬያቸው ሌሎች ባንኮች እንዳይፈጠሩ እንዳይወለዱ ጫና ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ በአሮሚያ ሥር የሚንቀሳቀሱ ኦሮሚያ ኅብረት ሥራና ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንኮች አሉ፡፡ ሌላ ሦስተኛ ለመምጣት ከባድ ይሆናል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና መከማቸት ለትግራይ ክልል ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ሥጋት ይፈጥራል›› አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ባለሙያ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ ለማኅበራዊ ቀውስ ምክንያትም ሆኗል፡፡ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ...

‹‹በሌሎች ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከትግራይ አንፃር አነስተኛ ነው ብዬ ለመግለጽ አልችልም›› ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ...

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችና ሠራተኞች በአገሪቱ በሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞች፣ ድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእጅጉ ተፈትነው ነበር። በኮቪድ-19...

‹‹የውጭ ዜጎች ንብረት እንዲያፈሩ መፍቀድ ከፍተኛ ጥቅም አለው›› ቆስጠንጢኖስ በርሃ (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ ከእነዚህ የውይይት መድረኮች መካከል ከከፍተኛ የግብር ከፋዮች ወይም ታማኝ ግብር ከፋዮች...