Monday, May 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉከአዲሱ የኢሕአዴግ ፓርላማ ምን ይጠበቃል?

ከአዲሱ የኢሕአዴግ ፓርላማ ምን ይጠበቃል?

ቀን:

በልዑል ዘሩ

የኢትዮጵያ የፓርላማ ታሪክ ቢያንስ ከስምንት አሥርት ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረ ነው፡፡ ዛሬ በመሀል አራት ኪሎ በጥንት ግርማ ሞገስ ‹‹ጉብ›› ያለው ባለ ትልቅ የጣሪያ ሰዓቱ ፓርላማ ሕንፃና ግቢ ሥራ የጀመረው፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን መሆኑን ለአሁኑ ትውልድ መንገር ያስፈልጋል፡፡

ይሁንና ያለፉት ሦስት መንግሥታት በፓርላማው ታሪክ ውስጥ ያላቸው አሻራ ተመሳስሎም፣ ልዩነትም እንዳላቸው ጠቀስ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ተመሳስሏቸው አፄ ኃይለ ሥላሴ፣ ደርግም ሆነ ኢሕአዴግ (እንደራሴ፣ የሸንጐ አባልና የሕዝብ ተወካዮች) በሚል በአዳራሹ የሚሰይሟቸው ሰዎች ከሕዝብ የወጡ ይበሏቸው እንጂ፣ አስተሳሰባቸውንና የሥርዓቱን ፖለቲካዊ እምነት የያዙትን ነው፡፡ ልዩነቱ ደግሞ በአፄ ኃይለ ሥላሴም ሆነ በደርግ የግል ተወዳዳሪዎች ይኖሩ እንደሆነ እንጂ፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አስተሳሰብን የሚያራምዱ ተፎካካሪዎች አይታሰቡም፡፡ በኢሕአዴግ ዘመን ይኼ ቢያንስ በአራት የምርጫ ዙሮች በእንጭጭ ደረጃ መታየት ችሏል፡፡ ‹‹የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት›› የሚባለውን ዘፈን ያህል ባይሆንም፡፡

- Advertisement -

በዚህ ጽሑፍ የሦስቱን መንግሥታት ፓርላማዎች በማወዳደርና በማመሳሰል ጊዜ ላጠፋባችሁ አልሻም፡፡ ይልቁንም ሰሞኑን ሥራውን የጀመረው አምስተኛው የኢፌዴሪ ፓርላማ (ሙሉ በሙሉ የኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ተወካዮች 547 ወንበሮች የያዙበት) አቅጣጫ ምን መሆን አለበት? የሚል መወያያ ላነሳ ወደድኩ፡፡

በነገራችን ላይ አምስተኛው ፓርላማ የተለያዩ አስተሳሰቦችና የፖለቲካ አማራጮችን ያነገቡ የአገሪቱ ዜጐች ተወካዮችን ለማስተናገድ ባይችልም፣ በብሔረሰብና በፆታ ስብጥሩ ከፍተኛ መሻሻል የታየበት ነው፡፡ በመላው አገሪቱ የመንቀሳቀስ ዕድል ያላቸው የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ያቀረቧቸው ዕጩዎች የአካባቢው የብሔር ተወላጆች ናቸው፡፡ በፆታ ረገድም ለመጀመሪያ ጊዜ ዘንድሮ 212 ሴቶች ወደ ፓርላማ መግባታቸው ታይቷል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ ባለፈው ሳምንት በኢቢሲ ‹‹አንድ ለአንድ›› ፕሮግራም ላይ እንደተናገሩት፣ ሕግ አውጭው አካል ከመቼውም ጊዜ በተሻለ አስፈጻሚውን የመደገፍ፣ የመከታተልና የመቆጣጠር ሥራ አከናውኗል ብለዋል፡፡ በአምስተኛው ዙር የምክር ቤት አምስት ዓመታትም በዋናነት የመልካም አስተዳደር መስፈንና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ላይ በመመሥረት፣ አገሪቱ የጀመረችው ፈጣን ዕድገት በሕዝቡ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ እንዲሄድ መሥራት ይጠበቅበታል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ይህን ጥቅል ሐሳብ አስመልክተን ያነጋገርኳቸው ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ቅርበት ያላቸው ምሁራን ግን የአፈ ጉባዔውን ሐሳብ አይቀበሉትም፡፡ ‹‹ለፖለቲካ ፍጆታ›› የተባለ ገለጻ ብቻ ሲሉም ያጣጥሉታል፡፡ በተለይ ፓርላማው ‹‹የኢሕአዴግ ብቻ›› ከመሆኑ አንፃር ምክር ቤቱ ከገዥው ፓርቲ ተሿሚ አስፈጻሚዎች ሙሉ በሙሉ ተፅዕኖ ነፃ የሚሆንበት ምንም ዕድል የሌለው መሆኑ እየታወቀ፣ ከኢሕአዴግ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ አስተሳሰብ ውጪ ቢያንስ በቃል ደረጃ እንኳን በማይተነፈስበት አኳኋን፣ እንዴት ያለ ጠንካራ ክርክርና የቼክና ባላንስ ሥርዓት ሊዘረጋ ይችላል ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

በእርግጥ በምርጫ ፖለቲካ ውስጥ የፓርላማ ወንበሮች ለተፎካካሪዎች በድልድል የሚከፋፈሉ አይደሉም፡፡ ፍርድ ሰጪ የሆነው መላው የአገሪቱ ሕዝብ በምርጫ ካርዱ የሚሰጠውን ውሳኔ ከመቀበል ውጪም ሌላ አማራጭ የለም፡፡ ነገር ግን የአንድ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ገጽታ ብቻ ሳይሆን በመድበለ ፓርቲ ሥርዓት የሚገነባ ምክር ቤት ውስጥ የተለያዩ የፖለቲካ አስተሳሰቦች መታደም ዋነኛ መገለጫ ነው፡፡

በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባለ የብዝኃነት ክምችት ባለበት (የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የፖለቲካ አመለካከት፣ የፆታ፣ ወዘተ) እንዲሁም ካሳለፍናቸው የታሪክ ሒደቶች አንፃር በበርካታ አወዛጋቢ ሁነቶች በተሞላ ማኅበረሰብ ውስጥ የአንድ ፖለቲካ ፓርቲ አስተሳሰብ፣ ሙሉ በሙሉ በአገሪቱ ዜጐች ድጋፍ አግኝቶ ኢሕአዴግ ተመረጠ የሚለውን ድምዳሜ ለመቀበል አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ይህ እውነት መሬት ላይ ያለና የተፈጸመ ነው ከተባለም፣ ሌሎች ከተፎካካሪዎች መዳከም፣ አለመቻልና ተመራጭነት ማጣት ጋር የሚያያዙ ጉዳዮች ይነሳሉ፡፡

ይህን አስመልክተው በቪኦኤ የአማርኛው ክፍለ ጊዜ ሐሳባቸውን የገለጹት ዶ/ር አክሎግ ቢራራ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ፓርላሜንታዊ ዴሞክራሲ ወደኋላ እየተመለሰ ለመሆኑ ከማሳያዎቹ አንደኛው፣ ሥርዓቱን ሊገዳደሩ የሚችሉ ኅብረ ብሔራዊ ገጽታ ያላቸው ፓርቲዎች ፈራረሰዋል፡፡ በተቃውሞው ፖለቲካ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሚባሉ መሪዎች ተሰደዋል፣ ታስረዋል አልያም ‹ወደ ድሮ ፖለቲካና ኮረንቲ› እሳቤ ገብተዋል፡፡ ይህ በሆነበት ለብቻህ ተወዳድረህ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩን በሸምቀቆ ውስጥ አድርጎ ምርጫ አካሂጃለሁ ማለት የሚያስገኘው ይህን ዓይነቱን ፓርላማ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ ጋር ቢስማሙም ችግሩን በመንግሥትና በገዥው ፓርቲ ላይ ብቻ ከማላከክ በላይ በተፎካካሪው ኃይል ላይ ማሳረፍ የሚፈልጉ ደግሞ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ መምህር ናቸው፡፡ ‹‹እውነት ለመናገር አሁን የዚህችን ውስብስብና ዘርፈ ብዙ ችግሮች ውስጥ ያለፈች አገር ዕዳ ሁሉ ተሸክሞ ለመምራት የሚችል ስብስብ ያለው የፖለቲካ ኃይል በአገራችን አለ ወይ?›› በማለት ይጠይቃሉ፡፡ አንዳንዱ በፍርኃት እግሩን እየጐተተ፣ ሌላው ለኑሮ ብቻ የፖለቲካ ማኅበርን እንደ አክሲዮን መሥርቶ አንዳንዱም ‹‹ፓርቲ አለው›› እንዲባል ብቻ በምርጫ እየተወዳደረ ተለጣፊና አድርባይ እየተባለ ባለበት ሁኔታ፣ ሕዝብ በማያውቀው ሀቅ ላይ እንዴት ይህንን ዓይነቱን ተቃዋሚ ሊመርጥ ይችላል? ወደደውም ጠላው በዚህ ሁኔታ ከኢሕአዴግ የተሻለ አማራጭ (በፍርኃትም ጭምር) መቼ አገኘ በማለት ይሞግታሉ፡፡

‹‹እንግዲህ በእነዚህ ውዝግቦች ውስጥ እያለን ነው አምስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምን ይጠበቅበታል?›› በማለት ባለቀ በደቀቀው ጉዳይ ላይ አቅጣጫ ለማመላከት የፈለግኩት፡፡ በእርግጥም አምስተኛውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተመለከተ የወደፊቱን ጊዜ ከሕዝብ ጥቅም አኳያ ከማመላከት ውጪ አማራጭም አይኖርም፡፡ ስለሆነም ወደ እሱ እናምራ፡፡

ፓርላማውን ሕዝብ የሚያዳምጥበት ሥርዓት ይስፋ!

ቀደም ሲል እንደተገለጸው ፓርላማው በኢሕአዴግ ጠቅላይነት የተመሠረተ ቢሆንም፣ 547 የምርጫ ክልሎችን የወከሉ አባላት አሉት፡፡ ከአራቱም የአገሪቱ አቅጣጫ ከቆላም፣ ከደጋም፣ አደጉ ከሚባሉትም ሆነ ከታዳጊ ክልሎች የተውጣጡ እነዚህ የሕዝብ ተወካዮች በዓመት ሁለት ጊዜ ወደመረጣቸው ሕዝብ ሄደው የሚወያዩበት፣ ድክመትና ጥንካሬዎችን በመፈተሽ መፍትሔ የሚሰጡበትና የታችኛውን መንግሥታዊ መዋቅር የሚቆጣጠሩበት ሥርዓት አለ፡፡

በተግባር ሲታይ ግን እጅግ ደካማ ነው፡፡ በበጀትና በሎጂስቲክስ እጥረትም ሆነ በራሳቸው በምክር ቤት አባላት ቁርጠኝነት መጥፋት የሚታየው ይህ ዝቅተኛ አፈጻጸም የታየበት ሥራ፣ ሕዝቡ ተመራጮችን እንዳይተማመንባቸው አድርጎታል፡፡ አዲስ አበባ ገብተው በቴሌቪዥን እንያቸው፣ ቦሌ አፓርታማ ይቀመጡና ልጆቻቸውን ያስተምሩ እንጂ ምን ይፈይዱልናል የሚለው ዜጋ ቁጥር ትንሽ አይደለም፡፡

እዚህ ላይ በተለይ መፈተሽ ያለበት የምክር ቤት አባላቱ እጅ እያወጡ የኢሕአዴግን አዋጅ ለማፅደቅ ብቻ የተመረጡ አይደለም፡፡ ይልቁንም ‹‹ሕዝቡ ምን ይላል?›› የሚለውን ድምፅ ማዳመጥ ያስፈልጋል፡፡ ፈጥኖ የሚታረመውን እንዲስተካከል ማድረግ፣ ያልታረመውን ወደ ቋሚ ኮሚቴዎች ምክር ቤቱ ራሱና ሌሎች ሕጋዊ መሥሪያ ቤቶች (እንባ ጠባቂ፣ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ወይም ሌላ) ወስዶ ከውጤት ማድረስ አለባቸው፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ የፓርላማ አባላቱ የኢሕአዴግ አባላት (ተወካዮች) ቢሆኑም፣ የሕግና የህሊና ግዴታ ያለባቸው በመሆናቸው ነው፡፡ ተጠሪነታቸውም ለሕዝብ በመሆኑ ነው፡፡

ፓርላማው አድማጭ መሆን አለበት ሲባል አንዱ ከላይ የጠቀስነው ተመራጮች ወደ ሕዝብ ወርደው ሕዝቡን የሚደርሱበት መንገድ ሲሆን፣ ሌሎች አካሄዶችም አሉ፡፡ አንደኛው በሚወጡ አዋጆች፣ የሕግ ማዕቀፎችና ደንቦች ረቂቅ ላይ ሕዝቡን የማወያየት ተግባር ነው፡፡ በተለይ ባለድርሻ አካላት (ዜጐች፣ ባለሀብቶች፣ የግል ድርጅቶችና ማኅበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት…) የሚባሉትን በንቃት በማሳተፍ ነው፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ ‹‹ይኼ አዋጅ ሊፀድቅ ነው፡፡ ሐሳባችሁን በዚህ ስልክ ደውላችሁ ንገሩን፤›› ማለት ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ይልቁንም የማዳመጫ (ሒሪንግ) መርሐ ግብሮችን በማስፋት የዜጐችን የመሳተፍ ዕድላቸውን ማጠናከር ይገባል፡፡ የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ካለበት ደካማ ሁኔታ ወጥቶ በድረ ገጽና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መረጃ ለመሰብሰብ፣ በአስተያየት መስጫና ተንቀሳቃሽ የሕዝብ ድምፅ መቀበያ ማዕከላት አድማጭ ሊሆን ይገባል፡፡ ካልሆነ ግን ለማለት ብቻ አድማጭ ነን ማለት የትም አያደርስም፡፡

ፓርላማው የቁጥጥር ሥርዓት ጀመረ እንጂ ጥርስ አላወጣም

አንድ የተቃዋሚና አንድ የግል ተወዳዳሪ ወንበር ብቻ የያዙበትና 545 ወንበሮች በኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች የተሞላበት ያለፈው አራተኛ ምክር ቤት ከሚገለጽበት በጐ ተግባሮች አንዱ የቋሚ ኮሚቴዎች እንቅስቃሴ ነው፡፡ በተለይ በመስክም ሆነ በክልል የሚገኙ ፕሮጀክቶችን፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን አፈጻጸም ድክመትና ጥንካሬ እያጠራ ጠበቅ ያለ ሒስ መስጠቱ አንድ በጐ ዕርምጃ ነው፡፡ ችግሩ ግን በአንድ በኩል አጠናክሮ በተከታታይ እየሄደበት አይደለም፡፡ በሌላ በኩል የሚታዩ ክፍተቶችን ከመናገር አልፎ አጠናክሮ የማጋለጥና አስፈጻሚው ራሱን እንዲያርም የማዘዝ አቅም የለውም፡፡ ሰሞኑን አቶ አባዱላ በግልጽ እንደተናገሩት፣ ‹‹የሌባና ፖሊስ ሥራ አንሠራም›› ከተባለ ሥራ እየተከታተልን ነው ማለት ፕሮፓጋንዳ ብቻ ነው፡፡

የኢፌዴሪ ፓርላማ የቁጥጥር ሥርዓትን ያጠናክር ሲባል መገለጫው ብዙ ነው፡፡ ለምሳሌ በመላው አገሪቱ ያሉ የመንግሥት ሚዲያዎች ተጠሪነታቸው ለምክር ቤቶቹ ነው፡፡ እንደ ኢቢሲ፣ ኢትዮጵያ ፕሬስና ሬዲዮ ያሉ የፌዴራል መንግሥት ተቋማት የሚመሩትም በመገናኛ ብዙኃን ማስታወቂያ፣ ባህልና ቱሪዝም ቋሚ ኮሚቴ ብሎም በፓርላማው ነው፡፡ እነዚህ የመገናኛ ተቋማት ግን አሁን ዋነኛ የአድርባይነት ምንጭ በመሆናቸው ተዕፅኖ መፍጠርም ሆነ ተዓማኒነትን መጎናጸፍ አልቻሉም ተብሎ በመንግሥት በራሱ ጩኸት ተጀምሯል፡፡ የአመራር አቅምና የአመለካከት ውስንነቱም አንቆ እንደያዛቸው በማሳያዎች ተመላክቷል፡፡ ታዲያ ፓርላማው ምን ዕርምጃ ወሰደ!?

እንደ አገር በመልካም አስተዳደር ዕጦት የሚማረረው ዜጋና የተንገሸገሸው ባለሀብት ቁጥርም ቢሆን ትንሽ የሚባል አይደለም፡፡ ይህ ችግር ጐልቶ እየታየ ያለው ደግሞ በክልልም ሆነ በፌዴራሉ የአስፈጻሚውና የሕግ ተርጓሚው መዋቅሮች ነው፡፡ እነዚህን መዋቅሮች ከምክር ቤት አባላት ጨምሮ የሙያተኞችን አቅም በመጠቀም፣ ሕዝብ የሚማረርበትን የበሽታ ሰንኮፍ መንቀል ይኖርበታል፡፡ ይህ ሲሆን ነው የሥልጣን ሁሉ የበላይ የሚባለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገቢው ሕገ መንግሥታዊ ቦታ መያዙ የሚረጋገጠው፡፡

በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ውስጥ ቁልፍ ድርሻ እንዳላቸው የሚታመነው እንባ ጠባቂ፣ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ምርጫ ቦርድና ዋና ኦዲተርን የመሰሉ ተቋማት ተጠሪነታቸው ለምክር ቤቱ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እነዚህ መሥሪያ ቤቶች በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውም ሆነ በመልካም አስተዳደር ዕጦትና ጉድለት የሚታዩ ክፍተቶችን ማረም ላይ የሚታይባቸው ውስንነት አለ፡፡ ሌላው ቀርቶ ከሕገ መንግሥታዊ አስተሳሰብ ውጪ በሆነ መንገድ በየክልሉ በማንነታቸው ብቻ እየተባረሩ፣ ንብረታቸው እየወደመና እየተገደሉ ያሉ ዜጐችን ሁኔታ ሲያጋልጡ አለመደመጡ የውድቀቱ ማሳያ ነው፡፡

በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ብዛት ያላቸው ማረሚያ ቤቶች አሉ፡፡ ግን ምን ያህል ለተጠርጣሪዎችና ለታራሚዎች ምቹ ናቸው? ከእስረኛ አያያዝ ጋር የሚነሳ የድብደባም ሆነ የመንገላታት ቅሬታ የለም? ለሕዝብና ለጐብኚዎች ክፍት የማይደረጉ ማረሚያ ቤቶች የሚያስተላልፉት መልዕክትስ ምንድነው? መባል አለበት፡፡

አገራችን ለሁሉም ዜጐች የእኩልነትና የነፃነት የኩራት ምንጭ እንድትሆን በማድረግ በኩል ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በላይ ሥልጣን ያለው አካል የለም፡፡ ዜጐች በፖለቲካዊ እምነታቸው፣ በሃይማኖታዊ አስተሳሰባቸው ምክንያት እንዲደገፉ መደረግ የለበትም፡፡ በአንድ ወቅት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች በምክር ቤቱ በነበሩ ጊዜ የሚያነሷቸው የፖለቲካ ምኅዳር መጥበብ፣ የሚዲያ ነፃነት መገፈፍ፣ የመሰብሰብና የመደራጀት መብት መኮሰስ ጉዳይ ለአሁኑ ፓርላማም ጭንቀትና ሥጋት ሆነው ሊታዩ ይገባል፡፡ የአባላቱ ተጠሪነት ለሕግ፣ ለአገርና ለህሊና ነውና፡፡

በአጠቃላይ በኢሕአዴግና በአጋር ፓርቲዎች የበላይነት የተመሠረተው አዲሱ ፓርላማ መስከረም 24 ቀን ሰኞ በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ተከፍቷል፡፡ በዚህ ወቅት እንደታየውም አፈ ጉባዔና ምክትል አፈ ጉባዔው ለተጨማሪ አምስት ዓመታት በድጋሚ ተመርጠዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሹመትን በድጋሚ ከማፅደቁ ባሻገር፣ በማግሥቱ የካቢኔ አባላቱንም ሰይሟል፡፡ በቀዳሚው ዕለት ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ባቀረቡት ይፋዊ ዓመታዊ መንግሥት የትኩረት አቅጣጫዎቹን አመላክቷል፡፡

አሁን ከዚህ በኋላ የሚፈለገው ጉዳይ ከያዝነው ጊዜ ጀምሮ ወደ ተግባር መግባት ነው፡፡ ምክር ቤቱ በመረጃ አያያዝ፣ ለሕዝብ ተደራሽ በማድረግ፣ በአባላቱ የነቃ ተሳትፎ ከመፋዘዝ ወጥቶ በአዲስ መንፈስ ሊንቀሳቀስ ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ በአውራ ፓርቲ ፓርላማ ስም የተዳከመ ማኅበር ወደመሆን ከመውረድ አይድንም፡፡   

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

  

       

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...