Friday, March 31, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የቡና ኮንፈረንስ 1,500 ያህል ተሳታፊዎች ይጠበቃሉ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከኬንያ፣ ከኮትዲቫዋር፣ ከጣሊያንና ከኮሎምቢያ ጋር ተወዳድራ በማሸነፍ፣ አራተኛውን የዓለም አቀፍ ቡና ኮንፈረንስ እንድታዘጋጅ የተመረጠችው ኢትዮጵያ፣ ኮንፈረንሱን ከየካቲት 27 እስከ መጋቢት 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ ታካሂዳለች፡፡ ከ1,500 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ ይጠበቃል፡፡

ንግድ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር በጋራ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ የዓለም ቡና ኮንፈረንስ በየአራትና አምስት ዓመታት ይካሄዳል፡፡ የመጀመሪያው ኮንፈረንስ እንግሊዝ፣ ሁለተኛው ብራዚል፣ ሦስተኛው ደግሞ ጓቲማላ ተደርጓል፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ላለፉት ስድስት ዓመታት ሳይካሄድ የቆውን አራተኛውን ኮንፈረንስ ታስተናግዳለች፡፡

በንግድ ሚኒስቴር የውጭ ንግድ ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ሙሉጌታ እንደተናገሩት፣ መቀመጫውን ለንደን ካደረገው ዓለም አቀፍ የቡና ኮንፈረንስ ድርጅት (ICO) ጥሪ ካደረገላቸው አምስት አገሮች ውስጥ አንዷ ነበረች፡፡ ድርጅቱ ለማወዳደሪያ ካቀረባቸው በቡና ዙሪያ በቀረቡ የመወዳደሪያ ነጥቦች፣ ከፍተኛውን ውጤት በማግኘት በመመረጧ ኮንፈረንሱን ለማካሄድ እንቅስቃሴ መጀመሯን አስረድተዋል፡፡

የኮንፈረንሱ ዓላማ በቡና ምርት ግብይት፣ በፋይናንስና የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር በማድረግ፣ ለዘርፉ ተዋናዮች ተጠቃሚነትና ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር መሆኑን አቶ አሰፋ አስረድተዋል፡፡

በኮንፈረንሱ ላይ ከአገር ውስጥና ከውጭ 1,500 ያህል ተሳታፊዎች እንደሚገኙ ግምት መኖሩን ቢናገሩም፣ የትኞቹ ድርጅቶችና የትኞቹ ቡና አብቃይ አገሮች፣ በአጠቃላይ ተሳታፊዎቹ ‹‹በዘርፉ የተሰማሩት›› ከማለት ባለፈ በዝርዝር እንደማይታወቁ ገልጸዋል፡፡

የተሳካ ኮንፈረንስ ማካሄድና በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደውን 116ኛው የዓለም አቀፍ የቡና ካውንስል ስብሰባን በብቃት እንደምትወጣ ማሳየት፣ ተሳታፊ አፍሪካ አገሮች መሪዎችን በመጋበዝ የአፍሪካ አንድነትን ማሳየት በኮንፈረንሱ ሊሳኩ ከሚገቡ ግቦች መካከል መሆናቸውን የገለጹት አቶ አሰፋ፣ ለአገር ገጽታ ግንባታም ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

‹‹ኮፊ ካልቸር ዳይቨርሲቲ ኤንድ ኮንሰምፕሽን›› በሚል መሪ ቃል (ገና በድርጅቱ አልፀደቀም) ኮንፈረንሱ እንደሚካሄድ የገለጹት ጄኔራል ዳይሬክተሩ፣ ገና በድርጅቱ የሚፀድቁና ለፓናል ውይይት መነሻ የሚሆኑ ጥናታዊ ጽሑፎች ርዕሶች መመረጣቸውን ገልጸዋል፡፡

ለኮንፈረንሱ የሚመጡ ተሳታፊዎች በኢትዮጵያ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን እንደሚጐበኙ፣ ከ100 በላይ ተሳታፊዎች የሚታደሙበት ደረጃውን የጠበቀ የቡና ኤግዚቢሽን እንደሚካሄድ ጠቁመው፣ ለዚህ ሁሉ የሚሆነው ወጪ ከመንግሥትና ከፕሮሞሽን እንደሚሸፈን ገልጸዋል፡፡ እስከ 28 ሚሊዮን ብር ሊያስወጣ እንደሚችልም አክለዋል፡፡ ኮንፈረንሱ ሊካሄድ ወራት የቀሩት ቢሆንም፣ የዝግጅቱ ዋና ተዋናይ ዓብይ ኮሚቴ፣ ንዑስ ኮሚቴዎችና አዘጋጆች ገና አለመቋቋማቸውን፣ ኮንፈረንሱ የሚካሄደው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የመሰብሰቢያ ማዕከል ቢሆንም፣ ገና አለመፅደቁን ተናግረዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ቡና ላኪ ማኅበር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ጌታቸው አድማሱ ተገኝተዋል፡፡  

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች