Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊመገናኛ ብዙኃን መልካም አስተዳደርን ዋነኛ አጀንዳ እንዲያደርጉ ተጠየቀ

መገናኛ ብዙኃን መልካም አስተዳደርን ዋነኛ አጀንዳ እንዲያደርጉ ተጠየቀ

ቀን:

በኢትዮጵያ ያሉ የግልም ሆኑ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የመልካም አስተዳደር ዕጦትን ለመቅረፍ፣ ዋነኛ አጀንዳ አድርገው መሥራት እንዳለባቸው ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ከሚዲያና ከኮሙዩኒኬሽን አመራሮች ጋር በመተባበር ‹‹ተፅዕኖ ፈጣሪ ሚዲያ ለመገንባት ያሉ ዕድሎች፣ ፈተናዎችና መፍትሔዎቻቸው›› በሚል መሪ ቃል ከመስከረም 21 ቀን እስክ 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ በጁፒተር ሆቴል ባዘጋጀው የሁለት ቀናት የውይይት መድረክ ላይ እንደተገለጸው፣ የመገናኛ ብዙኃን የመንግሥትን አገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን የዕለት ተዕለት ሥራቸው አካል አድርገው መከታተል አለባቸው፡፡ በአገልግሎት አሰጣጡ ዙሪያ ጉድለቶች ከታዩ ወይም ተገልጋዩ ኅብረተሰብ በሚያደርሰው ጥቆማ ጉድለቶች እንዲታረሙ መጠየቅና ያለመታከት መከታተል እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡

ከተፅዕኖ ፈጣሪ መገናኛ ብዙኃን አንፃር የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባሉባቸው ተጨባጭ እውነታዎች ዙሪያ ‹‹የኢትዮጵያ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ከመልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲ ግንባታ አንፃር›› የሚል ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አክሲዮን ማኅበር ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ብሩክ ከበደ፣ የመንግሥት አሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲኖረው፣ የኅብረተሰቡና የመገናኛ ብዙኃን ክትትል ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

መገናኛ ብዙኃን በምርመራ ዘገባ ላይ ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸው የተናገሩት አቶ ብሩክ ሙስናን፣ ብልሹ አሠራርን፣ የተደራጁ ምዝበራዎችን ጊዜ ወስደው በመመርመር፣ በላቀ ሙያዊ ደረጃ ማጣራትና ማጋለጥ ትኩረቶች መሆን እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡ ሚዲያው ይህንን ሲያደርግ ራሱን በግንባር ቀደምትነት ከኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት ተግባር ነፃ ማውጣት የመጀመሪያው ዕርምጃ መሆን እንዳለበት አስረድተዋል፡፡ የሚዲያው አመራር ከተንጠራራ ፍላጎትና ከአድርባይነት ነፃ መሆን እንዳለበት፣ በተቋሙ ውስጥ ውስጣዊ ዴሞክራሲ እንዲኖር ማድረግ፣ ሁሉም አመራር የዘመናዊ ሚዲያ ዕውቀት ባለቤት እንዲሆን ማድረግ፣ ከየትኛውም አቅጣጫ የሚመጡ ውጫዊ ተፅዕኖዎችን ቀድሞ መገመትና ለመቋቋም ራስን ማዘጋጀት እንደሚገባ አክለዋል፡፡ በዋነኝነት የሚዲያ ተቋሙን ከኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና በንቃት መጠበቅና የውስጥ ንፅህናን በየጊዜው ማረጋገጥ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ጋዜጠኛው ከሁሉም በላይ ውግንናውን በዋነኝነት ለሕዝብ ማድረግ እንዳለበት የጠቆሙት አቶ ብሩክ፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱንና ሕገ መንግሥቱን ማክበርና ማስከበር፣ በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ መሥራት፣ ሙያውን የስውር ፖለቲካ ተልዕኮ ማስፈጸሚያ ከማድረግ ተጠብቆ ሙያዊ ብቃቱን በሁሉም ዘርፍ ማሳደግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

መንግሥት የመረጃ ነፃነትን በሁሉም ዘርፎች ማረጋገጥ፣ የሚዲያ ተቋማትን እንደ ሁነኛ የሕዝብ ድምፅ ማዳመጫ፣ መከታተያና መገንዘቢያ በመውሰድ መደበኛ መከታተያና ማስፈጸሚያ ሥርዓት መዘርጋት እንዳለበት በጥናታዊ ጽሑፋቸው የጠቆሙት አቶ ብሩክ፣ በሚዲያ ለሚቀርቡ የሕዝብ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች፣ ጥቆማዎችና የምርመራ ግኝቶች አፋጣኝ ምላሽ መስጠትና ማሳወቅ እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

የሚዲያ ነፃነት በማናቸውም የመንግሥት አካላትና ባለሥልጣናት የጎንዮሽ ወይም የጀርባ ጉንተላ፣ ማስፈራራትና ዛቻ ተፅዕኖ ሥር እንዳይወድቁ መንግሥት ጥብቅ ሥርዓት መዘርጋት እንዳለበት አቶ ብሩክ ተናግረዋል፡፡ ለሚዲያ አመራሮችና ባለሙያዎች የክህሎትና የአመለካከት ዕድገት ሥልጠና ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንዳለበትም አክለዋል፡፡

የመገናኛ ብዙኃን ከመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ከጥገኛ ባለሀብቶች፣ ከጥገኛ ፖለቲከኞች፣ ከጥገኛ ማኅበራት፣ ከጥገኛ ምሁራን፣ ከደላሎችና ከሌሎችም ተግዳሮቶች እንደሚገጥሙት አቶ ብሩክ በጥናታቸው ዳሰዋል፡፡ የሕዝብ ግንኙነቶች አቅም ማነስ፣ የየተቋማቱ ቴክኖሎጂ የመጠቀም አናሳነትና የመንግሥት የማስፈጸም አቅም አናሳነትም የሚዲያው ተግዳሮቶች መሆናቸውን አክለዋል፡፡

ፖሊስና ፍርድ ቤቶች ‹‹ለምን ተነካን?›› ብለው ሥልጠናቸውን ያላግባብ የመጠቀም ሁኔታ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ በጥናቱ ጠቁመው፣ ‹‹አፈፍ›› እያደረጉ የማሰር ሥልጣናቸውን በጋዜጠኛ ላይ እንዳያደርጉ ወይም እንዳይተገብሩ የተለየ የሕግ ጥበቃ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙኃን የሕዝብና የግል (ለዘብተኛና ጽንፈኛ) በሚል የተከፈሉ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ብሩክ፣ በሁለቱም በኩል ጠንካራና ደካማ ጎኖች እንዳሉ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡

መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ሚናቸውን በብቃት እንዲወጡ እየገለጸና የመንግሥት የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነትና መልካም አስተዳደር ማስፈን ፍላጎት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን በጥናታቸው ያካተቱት አቶ ብሩክ፣ የሕዝቡ የዴሞክራሲ ባህል ዕድገትና ተሳትፎ መጎልበት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

ሕዝቡ ባገኘው አጋጣሚ በነፃነት የመናገርና ሐሳቡን የመግለጽ ባህሉ እየዳበረ መሆኑን፣ የተማረው የኅብረተሰብ ክፍልና አዲሱ ትውልድ የነፃነትና የመብት ጥያቄው ከፍ እያለ መሆኑን፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃንን በማድመጥ ደረጃውን ከፍ እያደረገ ስለሆነ የመገናኛ ብዙኃን ክህሎትና ብቃት ሊታሰብበት እንደሚገባ አቶ ብሩክ አሳስበዋል፡፡ መገናኛ ብዙኃን ተናጋሪ ኅብረተሰብ መፍጠርና ኅብረተሰቡን የራሱ ባለጉዳይ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አክለዋል፡፡ ለኅብረተሰቡ ጥያቄዎች ትኩረት ሰጥቶ ማስተናገድና ምላሽ እንዲያገኝ ማድረግ፣ የመንግሥት ሐሳቦች፣ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ዕቅዶች ላይ ኅብረተሰቡን በነፃነት በማሳተፍ አስተያየታቸውን በማካተት፣ ሙያው የመንግሥት አንደበት ከመሆን መላቀቅ እንዳለበትም በጥናቱ ተካቷል፡፡

አቶ ብሩክ ካቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ ጋር ተመሳሳይነት ያለውና አጠቃላይ የመገናኛ ብዙኃን አሠራር ላይ ያተኮረ ‹‹የተፅዕኖ ፈጣሪ ሚዲያ ምንነትና በኢትዮጵያ ያሉት ዕድሎች፣ ፈተናዎችና መፍትሔዎቻቸው›› የሚል ጥናታዊ ጽሑፍ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ፋካልቲ መምህር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ለውይይት ቀርቧል፡፡ የውይይቱን መድረክ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘርዓይ አስገዶም በንግግር ከፍተዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጌታቸው ረዳ የውይይቱ አስፈጻሚ ነበሩ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...