Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክ ያወጣው የውጭ አቅራቢዎች የዱቤ ሽያጭ መመርያ ተቃውሞ ገጠመው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በመስከረም 2010 ዓ.ም. መጨረሻ ያወጣው የውጭ አቅራቢዎች የዱቤ ሽያጭ (ሰፕላየርስ ክሬዲት) መመርያ፣ አገር በቀል ፋብሪካዎችን ያገለለና ለውጭ ኩባንያዎች ያደላ ነው በማለት የብረት ፋብሪካዎች ማኅበር ተቃውሞ አቀረበ፡፡

      የኢትዮጵያ መሠረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያወጣውን መመርያ ቁጥር FXD/47/2017 በመቃወም ቀዳሚ ሆኗል፡፡

      ማኅበሩ ሐሙስ መጋቢት 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ለሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት በጻፈው ደብዳቤ፣ ‹‹የውጭ አቅራቢዎች ዱቤ ሽያጭ (ሰፕላየርስ ክሬዲት) መመርያ ቁጥር FXD47/2017 አገር በቀል አምራቾችን ያገለለ በመሆኑ፣ ለከፍተኛ ኢፍትሐዊ የንግድ ውድድር የሚዳርግ ነው፤›› ብሏል፡፡

      ማኅበሩ በደብዳቤው እንደገለጸው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እ.ኤ.አ. ከኦክቶበር 3 ቀን 2017 ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ ያወጣው የውጭ አገር ብድርና የዱቤ ሽያጭ አቅርቦት መመርያ አንቀጽ 4 ላይ እንደተደነገገው፣ ኤክስፖርት አድራጊዎችንና የውጭ አገር ኩባንያዎችን ብቻ በተናጠል ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥርዓት ዘርግቷል፡፡

      በብረታ ብረት ዘርፍ በተደረገው የዳሰሳ ጥናት የውጭ አቅራቢዎች የዱቤ ሽያጭ መመርያ፣ በአገር በቀል አምራቾች ላይ ከተጋረጡ ከፍተኛ ወቅታዊ አደጋዎች ተርታ ይመደባል ሲል ማኅበሩ አስታውቋል፡፡

      የውጭ ምንዛሪ ችግር በዘላቂነት የሚፈታው የኤክስፖርት አቅም ሲገነባ ቢሆንም፣ የውጭ አቅራቢዎች የዱቤ ሽያጭ አሠራር በውጭ ምንዛሪ እጥረት የሚሰቃዩ አገሮች በጊዜያዊ መፍትሔነት የሚጠቀሙበት አሠራር መሆኑ ይታወቃል፡፡

      ሰባ አራት ከፍተኛና መካከለኛ የብረታ ብረት ፋብሪካዎችን በአባልነት ያቀፈው ማኅበሩ እንደገለጸው፣ በሥሩ ያሉት ፋብሪካዎች በአገሪቱ በተከሰተው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ባለመኖሩ ሙሉ አቅማቸውን ቀርቶ ሩቡን እንኳ ማምረት ተስኗቸዋል፡፡

      ‹‹ፋብሪካዎቹ ከአቅም በታች ለማምረት ተገደው በመዳከር ላይ ይገኛሉ፤›› በማለት የገለጸው የማኅበሩ ደብዳቤ፣ ‹‹ይህንንም የጥሬ ዕቃ ዕጦት በጊዜያዊነት መፍትሔ ለመስጠት ጥረት ከማድረግ ጎን ለጎን፣ መንግሥት የረዥም ጊዜ ስትራቴጂካዊ መፍትሔዎች ለማፈላለግ በሚያደርጋቸው ጥረቶች ንቁ ተሳትፎ እያደረግን ነው፤›› በማለት ማኅበሩ ይገልጻል፡፡

      ይሁንና የኤክስፖርት ማበረታቻና የገቢ ምርቶችን የመተካት ጥረትን መመርያው በተገቢው መጠን አመጣጥኖ ያላስተናገደ ከመሆኑም በላይ፣ ለአገር ውስጥ ገበያ የሚያመርቱ የውጭ አገር ኩባንያዎችን በልዩ ሁኔታ ድጋፍ በመስጠት፣ የአገር ውስጥ አምራቾችን ከጨዋታ ውጪ ሊያደርግ የሚችልበት ሁኔታ መፈጠሩን ማኅበሩ ገልጿል፡፡

      ‹‹መንግሥት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ የአገሪቱ የኢንዱስትሪ ልማት ዋና ምሶሶ የአገር ውስጥ ባለሀብቱ መሆኑን በግልጽ ቢያስቀምጥም፣ ይህ መመርያ ግን በተቃራኒው የቆመ ነው፤›› በማለት ማኅበሩ ብሔራዊ ባንክን ተችቶ፣ ‹‹ከዚህ በተጨማሪ ከውጭ አገር የመጡ ኩባንያዎች ሊኖራቸው ከሚችለው የተሻለ የዓለም አቀፍ የንግድ ትውውቅና ግንኙነት አንፃር፣ የአቅራቢዎች ዱቤ ሽያጭ ድጋፍን ለመጠቀም የሚኖራቸው ዕድል ሰፊ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ በአንድ በኩል የሚያስከትለው ተፅዕኖ ከግምት ውስጥ ያልገባበት መመርያ መሆኑን ማኅበሩ ገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ብሔራዊ ባንክ ተመሳሳይ ምርት የሚያመርቱ አገር በቀል አምራቾች ጥሬ ዕቃ የሚያገኙበት ዕድል ጎን ለጎን ሊያስብበት የሚገባ ጉዳይ ቢሆንም፣ መመርያው ይህን ጉዳይ ቦታ አልሰጠውም በማለት ማኅበሩ ገልጿል፡፡

‹‹የውጭ አቅራቢዎች የዱቤ ሽያጭ መመርያ የውጭ አገር ኩባንያዎች የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሪ ለአበዳሪ የሚመልሱበት የብድር አከፋፈል ሥርዓት ከአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ሆኖ ሳለ፣ አገር በቀል ኩባንያዎችን በማግለል ለውጭ አገር ኩባንያዎች ብቻ በተናጠል መፈቀዱ ፍትሐዊነት የጎደለው ነው፤›› ብሏል፡፡ ‹‹ከውጭ ምንዛሪ እጥረት አንፃር ሲታይ በተመሳሳይ ሥራ የተሰማሩ አገር በቀል ኩባንያዎች በአጭር ጊዜ ፍትሐዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር በማድረግ፣ ገና በለጋ ዕድሜ የሚገኙትን አገር በቀል ኩባንያዎች ከውድድር ውጪ ሊያደርግ ይችላል፤›› በማለት ማኅበሩ ሥጋቱን አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ መሠረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ሙሉጌታ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ዘርፍ ከነዳጅ ቀጥሎ ትልቁ የውጭ ምንዛሪ የሚጠቀም ነው፡፡

‹‹ነገር ግን ለዘርፉ የውጭ ምንዛሪ የቀረበው ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ነው፡፡ ፋብሪካዎች በጥሬ ዕቃ አለመኖር ሥራ በማቆምና ባለማቆም መካከል እየዋለሉ የሚገኙ ቢሆንም፣ ብሔራዊ ባንክ አድሎአዊ መመርያ ማውጣቱ ግን አደገኛና እጅግ ጎጂ ነው፡፡ መንግሥት ጉዳዩን በአጽንኦት ሊመለከት ይገባል፤›› በማለት አቶ ሰለሞን የችግሩን መጠን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች