– ከ7,422 በላይ ነዋሪዎችን ማፈናቀላቸው ተገልጿል
– ከ273 በላይ መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸው ተጠቁሟል
በጋምቤላ ክልል በማጃንግ ዞን በተለይ በመንገሽና በሶደሬ ወረዳዎች በሚገኙ የተለያዩ ቀበሌዎች፣ ከተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ወደ ክልሉ በመሄድ ለበርካታ ዓመታት በሕጋዊ መንገድ ይኖሩ የነበሩ ከ126 በላይ የተለያዩ ብሔር ተወላጆችን፣ ጭካኔ በተመላበት ሁኔታ በግፍ በመግደል የተጠረጠሩ 45 የክልሉ ተወላጆች ክስ ተመሠረተባቸው፡፡
ተከሳሾቹ በዞኑና በወረዳዎቹ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው መሆኑን ከሳሽ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የመሠረተባቸው ክስ የሚያስረዳ ሲሆን፣ የግድያ ወንጀሉ እንዲፈጸም በዋናነት ካነሳሱትና ካቀነባበሩት መካከል በዞኑ የመንገሽ ወረዳ ዬሪ ቀበሌ ሊቀመንበር ኤፍሬም ኮንችል ቲማንጌ፣ የዞኑ የፀጥታ ኃላፊ ቄስ ገብርኤል ለካኒ ዑማን፣ የጐደሬ ወረዳ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት ኃላፊና አፈ ጉባዔ ኮምቱ ናቲ፣ የገላሽ ቀበሌ ሊቀመንበር አሽን ኮካስ ዩጋከን፣ የክልሉ ምክር ቤት የመሬት አጠቃቀም ኃላፊ ዳዊት ከወሪ ትንጐሽ፣ የሸኔ ቀበሌ ሊቀመንበር ተወካይ ሠራዊት ፋሪስ፣ የመሀሽ ወረዳ ሚሊሻ ፈርዖን ጃርኩሜ፣ የጎደሬ ወረዳ የፀጥታ ጉዳዮች ኃላፊ ኮሲያን ጉሌንና የመንገሽ ወረዳ ፖሊስ ምክትል ኢንስፔክተር ሚልክያስ ኮቲል መሆናቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡
ተከሳሾቹ በ2006 ዓ.ም. በተለያዩ ወራትና ቀናት በመሰብሰብ፣ ከተለያዩ ክልሎች በጋምቤላ ክልል ማጃንግ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ሥር በሚገኙ ቀበሌዎች ሠፍረው ለበርካታ ዓመታት በመኖር ላይ የሚገኙት እነሱ ‹‹ደገኞች›› ብለው የሚጠሯቸው የተለያዩ ብሔር ተወላጆች፣ የያዙትን እርሻና የቡና ተክል መሬት ለማጃንግ ብሔር ተወላጆች እንዲያካፍሉ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡
የማያካፍሉ ከሆነ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ እንደሚደረግ፣ የመሬት ልኬት የሚደረገው ለማጂንግ ተወላጆች ብቻ እንደሚሆንም መስማማታቸውን ክሱ ያክላል፡፡
ተከሳሾቹ ሕጋዊ ነዋሪዎቹን ሰብስበው የያዙትን እርሻም ሆነ ያለሙትን የቡና ተክል ለተወላጆቹ የማያካፍሉ ከሆነ እንደሚወሰድባቸው ከነገሯቸው በኋላ፣ ለተሰብሳቢዎች ያሳወቁትን መመርያ በማጃንግ ዞን ሥር ለሚገኙ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ማስተላለፋቸውን ክሱ ያብራራል፡፡
ሕገ መንግሥቱ ያጐናፀፋቸውን መብት ተጠቅመው ወደ ክልሉ በመሄድ ለበርካታ ዓመታት ሲኖሩ የለፉበትንና ያፈሩትን ንብረታቸውንም ሆነ ይዞታቸውን ለማንም እንደማይሰጡና እንደማያካፍሉ ነዋሪዎቹ ሲናገሩ፣ የማጃንግ ተወላጅ የሆኑ የፖሊስና የሚሊሻ ታጣቂዎች የክልሉ ብሔር ተወላጆችን በማደራጀትና በማስታጠቅ፣ ጥቃት እንዲፈጽሙ ትዕዛዝ መስጠታቸውን በክሱ ተገልጿል፡፡
የአካባቢው ተወላጆች በተሰጣቸው ትዕዛዝ መሠረት ወደ ግጭቱ ሲገቡ፣ ተከሳሾቹም በቀጥታ በመሳተፍ ከሐምሌ 17 ቀን 2006 ዓ.ም. እስከ ግንቦት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በሌላ ብሔር ተወላጆችና በክልሉ ተወላጆች መካከል ደም አፋሳሽ ግጭት መቀስቀሳቸውን ክሱ ያብራራል፡፡
ተከሳሾቹ አመራር በመስጠትና የእርስ በርስ ግጭቱ እንዲስፋፋ በማድረግ ከ126 በላይ ከተለያዩ ክልሎች ወደ ክልሉ የሄዱ የተለያዩ ብሔር ተወላጆች መሞታቸውን፣ ከ7,422 በላይ ነዋሪዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውንና ከ273 በላይ መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አካቷል፡፡
ሕፃናት አንገታቸው ተቀልቶ፣ እናቶች ጡታቸው ተቆርጦና ወንዶች በጥይት ተደብድበው ከሞቱ በኋላ አስከሬናቸው በስለት ተቆራርጦና ጫካ ውስጥ ተጥሎ በአውሬ እንዲበላ፣ የተረፈውንም አስከሬን የመከላከያ ሠራዊት ደርሶ ባለበት እንዲቀበር መደረጉን ክሱ በዝርዝር ያስረዳል፡፡
በ45ቱ ተጠርጣሪ ተከሳሾች ላይ 46 ክሶች የቀረቡ ሲሆን፣ በጅምላና በተናጠል የፈጸሙትን የወንጀል ዝርዝር ዓቃቤ ሕግ በ50 ገጾች ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት አቅርቧል፡፡ ፍርድ ቤቱም ለተከሳሾቹ ክሱን በማንበብ መቃወሚያ ካላቸው መቃወሚያቸውን ለመቀበል ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡