Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅደመራ

ደመራ

ቀን:

     ስንኝ

በሚስቀው እግዜር

በሚያለቅሰው ሰይጣን

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በኒህ መካከል

ሰው የሰው ልጅ ቆሟል

እየተሳቀለ

ባንደኛው ሳቅ ባንደኛው ልቅሶ

ቆዳው እያለቀ

             በዮሐንስ አድማሱ

****

የሰኔው መስቀል በኦፖ ብሔረሰብ

ኦፖዎች ‹‹ናዋስ›› የሚሉት የመስቀል በዓልን የሚያከብሩት በቆሎ እሸት በሚደርስበት ወቅት ሰኔ ወር ላይ ነው፡፡ በዓሉ በሚከበርበት ቀንም የአካባቢው ነዋሪዎች በሙሉ ችቦ ይሠራሉ፡፡ በአካባቢያቸውም በጋራ አንድ ትልቅ ደመራ ይደመራል፡፡ በበዓሉ ቀን እያንዳንዱ ሰው ችቦ ለኩሶ ከቤት ይወጣል፡፡ በአገር ሽማግሌዎችም እየተመሩ በአካባቢው ወደሚገኙ የበቆሎ (ማሽላ) ማሳና ወንዞች ይሄዳሉ፡፡ ‹‹ከሰፈራችን ረሃብ ይውጣልን፤ በሽታ ይውጣልን›› እያሉም በማሳው ውስጥ ከተዘዋወሩ በኋላ የያዙትን ችቦ በሙሉ ወንዝ ውስጥ ይወረውሩታል፡፡ ይህም በሽታውና ረሃቡ እንደተወረወረ ለማሰብ ነው፡፡ ከማሳው ውስጥ የበቆሎ እሸት በመቁረጥ ደመራው ውስጥ በመወርወር እንዲበጠስ ይደረጋል፡፡ የተሰበሰበው ሰው ሁሉ ከዚህ በቆሎ እሸት በመብላትና ቦርዴ በመጠጣት ሲጫወቱና ሲዝናኑ ያመሻሉ፡፡

******

‹‹አባት ያቆየው ለልጅ ይበጀው››

የወይራ ዛፍ ተካዩ የሰባ ዓመት ሞስሊም አረጋዊ (ሽማግሌ ትምህርታዊ አጫዋች ታሪክ) አንድ ሞስሊም ሽማግሌ ጉድጓድ እየቆፈረ የወይራ ዛፍ ይተክል ነበር፡፡ አንድ ንጉሥ በሠረገላ ላይ ተቀምጦ በዚያ የተክል አጠገብ ሲያልፍ ሽማግሌውን የተክል ገበሬ አይቶ ‹‹ዕድሜህ ስንት ነው?›› ብሎ ሲጠይቀው ‹‹ሰባ ዓመት ሆኖኛል›› አለ፡፡ ንጉሡም ‹‹የወይራ ተክል ፍሬ መስጠት የሚጀምረው ከመቶ ዓመት በኋላ ነው፡፡ መቼ ደርሶልህ ልትበላው ነው በከንቱ የምትደክም?›› አለው፡፡

የሽማግሌው ሞስሊም መልስ “አባቶቻችን ተከሉ፡፡ ይኸው እኛ እንበላለን፤ እኛ የምንተክለውን ደግሞ ልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችን ይበላሉ፤” የሚል ነበር፡፡ ንጉሡ በመልሱ ተገርሞ ኻያ ሺሕ ወቄት ወርቅ ሰጥቶት  ሄደ፡፡ ሽማግሌውም ከኋላ ተከትሎ “ንጉሡ ሆይ አንድ ጊዜ ይስሙኝ” በማለት አሰምቶ መናገር ጀመረ፡፡ ንጉሡ “ምንድን ነው የምትል?” ሲለው ሽማግሌው “ይኸውልዎት ንጉሥ ሆይ! የወይራ ዛፍ ፍሬ መስጠት የሚጀምር ከመቶ ዓመት በኋላ ነው፤” ብለውኝ ነበር፡፡

ነገር ግን የእኔ ወይራ ዛፍ መቶ ዓመት ሳይቆይ ይኸው ዛሬውኑ ማፍራት ስለጀመረ ይህን ታምር መግለጥ ፈልጌ ነው ያስቆምኩዎት፣ ይቅርታ  አድርጉልኝ” አለ፡፡ ንጉሡም ይህ ሰው ታምረኛ ነው፡፡ እንደዚህ አንዳንድ አስደናቂ ቃል እየተነገረ ገንዘባችንን ሳያስጨርስ የሚመለስም አይመስልም፣ ሠረገላው ፍጥነት እንዲጨምር አድርግ፤” ብሎ ጉዞውን ቀጠለ ይባላል፡፡

  • መጋቤ አእላፍ መክብብ አጥናው “አምስተኛ ጉባኤ ዕድሜ ቀጥል ትምህርት አዘል የአባቶች ጨዋታ”  (2004)

*******************

ወርቅ ላበደረ …

«እርስዎ ነዎት ያኔ ልጄን ውኃ ሙላት ሲወስደው ዋኝተው ያወጡትና ያተረፉት?»

«አዎ እንዴታ!»

«እና ታዲያ የታለ ኮፍያው?»

  • ምስጋናው አየነው «የቀልዶች ወላፈን» (1997)

*******

ዘይተሃሰበ እና ንጉሡ

በአንድ ወቅት አንድ ንጉሥ ነበረ፡፡ ንጉሡም አንድ ትንሽ ልጅ ሁልጊዜ ወደ እርሱ ቤት እየመጣ ሲጫወት ያየው ነበር፡፡ ንጉሡም ልጁን ወደ አንድ ጠንቋይ ዘንድ ይዞት ሄዶ ጠንቋዩን “ይህ ልጅ ሲያድግ እጣ ፈንታው ምንድነው?” ብሎ ጠየቀው፡፡

ጠንቋዩም “ዙፋንህን ይወርሳል፡፡” ብሎ መለሰለት፡፡ በዚህ ጊዜ ንጉሡ ልጁን በትልቅ ሳጥን ውስጥ ከቶት ባህር ውስጥ ጣለው፡፡

ታዲያ አንድ ባልና ሚስት ልጁን አግኝተውት ወደ ቤታቸው ወሰዱት፡፡ ስሙንም “ዘይ ተሃሰበ” ማለትም (“ያልተጠበቀ”) ብለው ሰየሙት፡፡

ከእለታት አንድ ቀን ንጉሡ አንድን የፀጥታ ችግር ሊፈታ ልጁ ይኖር ወደነበረበት ስፍራ ሄደ፡፡ ንጉሡም እንዳጋጣሚ ልጁ ከሚኖርበት ቤት ያርፍና የንጉሡ ቤተሰብ ምግብ ሲበላ ልጁ የንጉሡንና የአሳዳጊዎቹን እጆች ያስታጥባል፡፡

ንጉሡም የልጁን ታታሪነት በማየት ይወደውና ሰዎቹን የራሳቸው ልጅ እንደሆነ ይጠይቃቸዋል፡፡

እነርሱም “ልጃችን አይደለም፡፡ አሳድገነው ነው፡፡” በማለት እንዴት እንዳገኙት ነገሩት፡፡

በዚህ ጊዜ ንጉሡ በጣም ተገርሞ ልጁን ወደ ቤተ መንግሥቱ እንዲልኩት ለመናቸው፡፡ እነርሱም በሐሳቡ ተስማምተው ሲሰጡት ንጉሡ ግን ለልጁ ወታደሮቹ ልጁ ቤተ መንግሥት እንደደረሰ እንዲገድሉትና በቤተ መንግሥቱ ፊት ለፊት እንዲቀብሩት ያዘዘበትን ደብዳቤ ፅፎ ሰጠው፡፡ ልጁም ወደ ቤተ መንግሥቱ እየሄደ ሳለ አንድ ጭልፊት መጥቶ ደብዳቤውን እንዲሰጠው ጠየቀው፡፡ ልጁም እሺ ብሎ ወረቀቱን ሲሰጠው ጭልፊቱ በምትኩ ሌላ “ልጁ እናንተ ዘንድ በደረሰ ግዜ ሴት ልጄን ዳሩለት፡፡” የሚል ደብዳቤ ሰጠው፡፡

እናም ልጁ ቤተ መንግሥት ደርሶ ወረቀቱን ለልጅቷ ቤተሰቦች ሲሰጥ እነርሱም ልጅቷን ድረውለት አብረው መኖር ጀመሩ፡፡ ንጉሡም ወደ ቤቱ ሲመለስ የሠርጉ ድግስ ስላላለቀ አንድ ትልቅ ድንኳን አየ፡፡

“ይህ ምንድነው?” ብሎም ጠየቀ፡፡

እነርሱም “አንተ ራስህ ልጄን ዳሩለት የሚል ደብዳቤ ልጁን አስይዘህ አላከውም እንዴ? ይህ ታዲያ የሠርጉ ድንኳን ነዋ!” አሉት፡፡

ይህን ሲሰማ ንጉሡ በድንጋጤ ከፈረሱ ላይ ወድቆ ራሱን ሲስት ሳንጃው ጎኑን ወግቶ ገደለው፡፡ ልጁም ዙፋኑን ወረሰ፡፡

  • ተራኪው የማይታወቅ የትግራይ ተረት

 

*****

ሜካፑ ሲታጠብ

እጅ፣ እግር፣ አንገት በተለይም ፊትን ለማስዋብ የተለያዩ ሜካፖችን (የፊት ማስዋቢያ ቅባቶችን) መጠቀም የተለመደ ነው፡፡ ከወጣት እስከ ጉብል ብሎም በዕድሜ የገፉትም በተለይ የፊታቸውን ቆዳ ውበት ለመጠበቅ፣ እርጅናንና የተበላሸ ፊትን ለመሸፈን የተለያዩ ሜካፖችን ይጠቀማሉ፡፡ ይህ ደግሞ በሴቶች ይጎላል፡፡ ታዲያ በሜካፕ ተውቦ የሚያውቁትን ሰው ድንገት ታጥቦ ወይም በሜካፕ የማያውቁትን ድንገት በሜካፕ ቢያዩት በልዩነቱ መደንገጥዎ ወይም መገረምዎ አይቀርም፡፡

ለአልጀሪያዊው ሙሽራ ግን ጉዳዩ ከመደንገጥና ከመገረምም ያለፈ ነው፡፡ ሚስቱን በተጋቡ ማግስት ፍርድ ቤት እስከማቆም ደርሷል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከጋብቻው ቀን በፊት የሚያውቃት ሚስት በሜካፕ የተዋበች ነበረች፡፡ እውነተኛ መልኳን አያውቅም ነበር፡፡ በጋብቻቸው ማግስት የተመለከተው የሚስቱ ገፅታ ግን የተለየ ነበር፡፡ ሜካፑ ሲታጠብ የተገለጠው እውነተኛው ፊቷ ለባሏ አልተመቸውም፡፡ በመሆኑም ከጋብቻ በፊት ፊቷን በሜካፕ በመሸፈን እሷነቷን ደብቃ አታላኛለች በሚል ከሷታል፡፡

ስነልቦናዊ ኪሣራ አድርሳብኛለች ሲልም የ20 ሺሕ ዶላር ካሳ ጠይቋል፡፡

ኢሚሬትስ 24/7 ከሳሽን ጠቅሶ ሰሞኑን እንዳስደመጠው፣ ‹‹ሚስቴ እስከ ሠርጋችን ድረስ በጣም ቆንጆና ሳቢ ነበረች፡፡ ሆኖም በሠርጋችን ማግሥት ፊቷን ታጥባ ሳያት የተለየች ነበረች፡፡ አታላኛለች›› ብሏል፡፡

*****************

ለመከሰስም ለመዳንም ምክንያት የሆነው ምርመራ

ባንኮክን ለመጎብኘት ያቀናችው የ39 ዓመቷ ቻይናዊት ጂያንግ ዡሊያንግ፣ በባንኮክ ሱቫርናቡሚ አየር ማረፊያ ስትደርስ ነበር በሆድቃዋ ውስጥ የተለየ ነገር የታየው፡፡ በሆዷ ውስጥ ያለውን ባዕድ ነገር በኮሎኖስኮፒ (አንጀት መመርመሪያ መሣሪያ) ከታየች በኋላ፣ የሕክምና ባለሙያዎች ከትልቁ አንጀቷ ውስጥ ስድስት ካራት ዳይመንድ አውጥተዋል፡፡ ዳይመንዱ ከትልቁ አንጀቷ ባይወጣ ኖሮ ሙሉ ለሙሉ የምግብ መፈጨት ሥርዓቷን ያበላሸው እንደነበር የሕክምና ባለሙያዎች ሲገልጹ፣ ፖሊስ ደግሞ 278,000 የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ ዳይመንድ በመስረቅ ወንጀል ጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ማዋሉን አሶሽየት ፕሬስ ዘግቧል፡፡

ለመኪና ግጭት ምክንያት የሆነችው ሸረሪት

ሰዎች ጉዳት የሚያደርሱ ይሁኑም አይሁኑም ሳያውቁ የተለያዩ ነፍሳትን በመፍራት ብቻ ይደነባበራሉ፡፡ ራሳቸውን ላልተፈለገ አደጋም ያጋልጣሉ፡፡ በአሜሪካ የተከሰተውም ይኸው ነው፡፡ የኢንዲያናዋ ወይዘሮ አንጀላ ኪፕ የዘጠኝ ዓመት ልጇን ይዛ እያሽከረከረች ነው፡፡ ድንገት ግን ሸረሪት ትከሻዋ ላይ ስትሄድ ታያለች፡፡ ወይዘሮዋ የመኪናውን በር ከፍታ ዘላ ትወርዳለች፡፡ መኪናው እንቅስቃሴውን ቀጥሏል፡፡ ከኋላ የተቀመጠው ልጇ እንቅስቃሴ ላይ የነበረውን መኪና ለማቆም ከኋላ ወንበር ዘሎ ፊት መጣ፡፡ የረገጠው ግን ፍሬኑን ሳይሆን ነዳጅ መስጫውን ነበር፡፡

ዩኤስኤ ቱዴይ እንደዘገበው፣ መኪናው ከተማሪዎች አውቶቡስ ጋር የተጋጨ ሲሆን በመኪናው ላይ ከባድ፣ በታዳጊው ላይ መጠነኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ ፖሊስ እንደገለጸው፣ ኪፕ በወንጀል ላትጠየቅ ትችላለች፡፡

በፍሪጅ 21 የሴት ብልት ክፍሎችን ያስቀመጠው ሰው ተያዘ

የ58 ዓመቱ ዴንማርካዊ በጾታዊ ጥቃት ተከስሶ በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ፍርድ ቤት ሰኞ ዕለት የቀረበው በፍሪጁ ውስጥ 21 የሴት ብልት ክፍሎች በመገኘታቸው እንደሆነ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ ግለሰቡ የተያዘው ባለፈው ሳምንት በሎይምፎንቲን ከተባለ ቦታ ላይ ነው፡፡

በተከሳሹ መኖሪያ ቤት የማደንዘዣ መድኃኒቶችና የቀዶ ሕክምና መሣሪያዎች የተገኙ ሲሆን፣ ግለሰቡ መጀመሪያ ሴቶቹን በማደንዘዝ ሕገወጥ ቀዶ ጥገናውን እንደሚያካሂድ ፖሊስ አስታውቋል፡፡ በዚህ መልኩ በግለሰቡ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ብዙዎቹ ከሌሴቶ ሳይሆኑ እንዳልቀሩ ፖሊስ ገምቷል፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ግለሰቡ ቀደም ሲል ለጋዜጠኛ የሴት ልብት ትልተላ እንደሚያደርግ አምኖ ነበር፡፡ በሕገወጥ የመሣሪያ ንግድ ደግሞ ዴንማርክ ውስጥ ይፈለጋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...