Tuesday, March 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በውቤ በረሃ የሚገኙ ነጋዴዎች የንግድ ቦታቸውን በግዳጅ ልንነጠቅ ነው አሉ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5፣ በተለምዶ ውቤ በረሃ በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን (አራዳ ጊዮርጊስ) አዲሱ የባቡር ተርሚናል እስከ አፍንጮ በር የሚገኙ ነጋዴዎች፣ ምትክ የንግድ ቦታ ሳይሰጣቸው የንግድ ቤቶቻቸውን በግዳጅ ለማፍረስ ወረው እያሸገ መሆኑን ገለጹ፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር እኩል ሊባል የሚችል ዕድሜ ያስቆጠሩ ንግድ ቤቶች በአንድ ሳምንት ማስጠንቀቂያ ማፍረስ ተገቢ አለመሆኑን የሚናገሩት ነጋዴዎቹ፣ አስተዳደሩ የገባላቸውን ቃል በማጠፍ፣ ‹‹ተለዋጭ ቦታ የምሰጣችሁ አሁን ያላችሁበትን የንግድ ቦታ አፅድቼ ስጨርስ ነው›› ማለቱ፣ ከሕግም ሆነ ከመንግሥት ፖሊሲ አንፃር የዜጐችን መብት የማያስከብር በመሆኑ አግባብነት የለውም ብለዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ነጋዴዎቹን ከዓመት በፊት ሰብስቦ በአክሲዮን እንዲደራጁና እያንዳንዳቸው 25,000 ብር በማዋጣት በባንክ እንዲያስቀምጡ፣ እንዲሁም በየወሩ ከ2000 ብር በላይ ገቢ እንዲያደርጉ ያቀረበውን ሐሳብ መቀበላቸውንና ተግባራዊ ማድረጋቸውን የሚናገሩት ነጋዴዎቹ፣ በንግድ ቦታቸው ላይ ግንባታ ተካሂዶ እያንዳንዳቸው 25 ካሬ ሜትር ቦታ እንደሚሰጣቸው የተነገራቸው ሁሉ ታጥፎ፣ በቀናት ውስጥ ለቀው እንዲወጡ መወሰኑ እንዳስደነገጣቸው ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ከወሰነ በኋላ የገባውን ቃል ተላልፎ በአስቸኳይ እንዲለቁ የሚያደርግ ከሆነ፣ ለሌሎች የልማት ተነሺ ነጋዴዎች የተሰጠው ዕድል ለእነሱም መነፈግ ስለሌለበት፣ ተለዋጭ የኮንዶሚኒየም የንግድ ቦታዎች እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

ቤተሰቦቻቸውንና ቀደምት ነጋዴዎችን በመተካት ሥራቸውን በንግድ ላይ በማድረግ ልጆቻቸውን የሚያስተምሩት፣ የሚመግቡትና ራሳቸውንም እያኖሩ የሚገኙት በያዙት ንግድ ቤት እየነገዱ በሚያገኙት ገቢ መሆኑን የሚናገሩት ነጋዴዎቹ፣ በሕገወጥ መንገድ በ‹‹አፍራሽ ግብረ ኃይል›› አማካይነት ወደ ጎዳና ተገፍተው ከመጣላቸው በፊት መንግሥት ሊደርስላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ዕድሜ ጠገብ የንግድ ቤቶች ከሆኑት መካከል የታዋቂው ክራር ተጫዋች ከተማ መኰንን ቤት የነበረው አሁን ብሔራዊ ሆቴል በቅጽል ስሟ ‹‹ጭራ ቀረሽ›› በሚል መጠሪያ የምትታወቀው የዘነበች ታደሰ የነበረውና አሁን ግሪን ባርና ሬስቶራንት፣ መዲና በመባል የሚታወቀው አሁን ያሲን ሱፐር ማርኬት፣ ድምፃዊት አበበች ደራራ የነበረችበት አሁን ሰላም ልኳንዳ፣ ዘመናት ያስቆጠረው አባ ገዳ ማተሚያ ቤት፣ አርቲስት አሰለፈች አላምረው ትሠራበት የነበረው ሆቴል፣ ኤፍሬም ግሮሰሪና ሌሎችም ታዋቂ የንግድ ቤቶች የሚፈርሱ መሆናቸውንም ነጋዴዎቹ ገልጸዋል፡፡

መንግሥት ለልማት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን እነሱም የሚደግፉት ተግባር እንደሆነ የገለጹት ነጋዴዎቹ፣ ከሁሉም በፊት የዜጐች መብትና ክብር መቅደም ስላለበት፣ እንዲሁም መንግሥት ዜጐቹን የመንከባከብና እንደየሥራ ዘርፋቸው ማሰማራት የሚጠበቅበት በመሆኑ ምትክ ቦታ ሰጥቶ እንዲታደጋቸው ጠይቀዋል፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ የቀድሞ ቀበሌ 03/09 (ወረዳ 5) አስተዳደር፣ በደል ሊፈጽምባቸው መሆኑን እየገለጹ ስለሚገኙት የውቤ በረሃ ነጋዴዎች ጉዳይ ለማነጋገር ሪፖርተር ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

በተመሳሳይ ከአራዳ ክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደርና ከተማ ማደስ ጽሕፈት ቤቶችም በተመሳሳይ ምላሽ ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች