Monday, April 15, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ፍትሕ በገንዘብ አይገዛ!

በመላ አገሪቱ እጅግ በጣም አስከፊ ከሚባሉ ድርጊቶች መካከል የፍትሕ እጦት ተጠቃሽ ነው፡፡ ፍትሕ የሕግ የበላይነት ስለመስፈኑ ማረጋገጫ ነው፡፡ ፍትሕ የእኩልነት ማረጋገጫ ነው፡፡ ፍትሕ የአንድን ኅብረተሰብ የሞራል ደረጃ ማሳያ ነው፡፡ ፍትሕ የምክንያታዊነትና የዕውነት ማንፀባረቂያ ነው፡፡ በአጠቃላይ ፍትሕ ለሰው ልጆች የተሰጠ የተፈጥሮ ፀጋ ነው፡፡ ይህ የተፈጥሮ ፀጋ እየተገፈፈ ፍትሕ እንደ ሸቀጥ በገንዘብ ሲተመን ያሳፍራል፡፡ እንደ አገር ያሳቅቃል፡፡

አስከፊዎቹ የፊውዳልና የወታደራዊ አገዛዞች ከሕዝብ ጫንቃ ላይ ተስፈንጥረው ከተጣሉ ከበርካታ ዓመታት በኋላ፣ ሕዝቡን ፍትሕ እንደ ውኃ ሲጠማው ማየት ያሳፍራል፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ ከማንም ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆኖ ፍትሕ ለዜጎች መዳረስ ሲገባው፣ በጀብደኞችና በሥርዓተ አልበኞች ምክንያት ፍትሕ ሲዳፈን እየታየ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ሰፍኖ ዜጎች በሕግ ፊት እኩል የመዳኘት መብት እንዳላቸው ሕገ መንግሥቱ በማያሻማ ሁኔታ አስቀምጦታል፡፡ ነገር ግን ፍትሕ የተስፋ ዳቦ ሆኗል፡፡ ሕዝብን ትናንት ከበደልና ከጭቆና ነፃ ልናወጣ ነው የታገልነው ያሉት ሳይቀሩ ፍትሕ እየነፈጉት ናቸው፡፡ ፍትሕ በገንዘብ ሲቸበቸብ እየታየ ነው፡፡ ይኼም ያሸማቅቃል፡፡

በ1966 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የፈነዳው አብዮት መሠረታዊ ዓላማ ለሕዝቡ ማኅበራዊ ፍትሕ ለማስፈን ቢሆንም፣ በወታደራዊው ኃይል ተጠልፎ አገሪቱ ለ17 ዓመታት ደም ፈሶባታል፡፡ ፍትሕ የጠየቁ በጥይት ረግፈዋል፡፡ አገርም የደም እንባ አንብታለች፡፡ ከዚያም በኋላ ኢሕአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ የሽግግር መንግሥት መሥርቶ፣ ሕገ መንግሥቱን በማርቀቅና በማፀደቅ ላለፉት 24 ዓመታት አገሪቱን እየመራ ነው፡፡ ነገር ግን እስካሁን ድረስ የፍትሕ ጥያቄ ምላሽ አላገኘም፡፡ አሁንም በአደባባይ የፍትሕ ችግር በትልቁ ብሶት እየቀረበበት ነው፡፡ አገሪቱ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ የሚለውን ስያሜ አንግባ ፍትሕ ግን የማይጨበጥ ጉም ሆኗል፡፡ ጉልበትና ገንዘብ ያላቸው ብቻ የሚያገኙት ዕቃ ሆኗል፡፡ እንደ ሸቀጥ ተቆጥሯል፡፡

በቅርቡ ኢሕአዴግም ሆነ አባል ድርጅቶቹ በተለይም ሕወሓት ባደረጉት ጉባዔ ፍትሕ ትልቁ ጥያቄ ሆኖ ቀርቧል፡፡ በአገሪቱ ምድር ፍትሕ ማስፈን የሚገባቸውና የሚጠበቅባቸው ጭራሽ ፍትሕ አደናቃፊ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ የፍትሕ ጥያቄ በመላ አገሪቱ ከዳር እስከ ዳር እያስተጋባ ነው፡፡ ዜጎች ፍትሕን በገንዘብ እንድንገዛ እየተገደድን ነው እያሉ ነው፡፡ በፍትሕ እጦት ሳቢያ ዜጎች ያለኃጢያታቸው ይታሰራሉ፡፡ ንብረታቸውን ያጣሉ፡፡ ቤተሰባቸው ይበተናል፡፡ በአገራቸው ተስፋ እየቆረጡ ይሰደዳሉ፡፡ የፍትሕ እጦት በተባባሰ ቁጥር ሕዝቡ ብሶቱ ጣራ ይነካል፡፡ ወንጀሎች ይባባሳሉ፡፡ ለአመፅና ላልተፈለጉ ግጭቶች ይዳርጋሉ፡፡ በመጨረሻም ማንም ሊመልሰው የማይችል ቀውስ ይፈጠራል፡፡

አንድ ዜጋ በገዛ አገሩ አንገቱን ቀና አድርጎ በነፃነት መራመድ የሚችለው መብቱ ሲከበርለትና እሱም የሚፈለግበትን ግዴታውን ሲወጣ ነው፡፡ ይህ ግዴታውን የሚወጣ ዜጋ ፍትሕ ሲነፈግና መብቱ ሲጣስ ግን ዜግነቱን ይጠራጠራል፡፡ ስለልማት፣ ስለዕድገትና ብልፅግና ቢወራ አይሰማም፡፡ በገዛ አገሩ በመረጠበት ቦታ የመዘዋወር፣ የመኖር፣ ሀብት የማፍራትና የመሳሰሉትን ተግባራት የሚያደናቅፉ በበዙበት ወቅት እንዴት ሆኖ ነው ስለፍትሕ መነጋገር የሚቻለው? ዜጎችን ዘርና ማንነታቸውን እየቆጠሩ የሚያፈናቅሉና ያፈሩትን ሀብት የሚዘርፉ ቀውሶች ሲያንገላቱዋቸው ዝም እየተባለ እንዴት ፍትሕ አለ ይባላል? ጉልበተኞች የተማመኑትን ተከልለው እንዳሻቸው እየፈነጩ ፍትሕን በገንዘብ እየሸቀጡበት ነው፡፡ ዜጎችንም እያስለቀሱ ነው፡፡

ገንዘብ ያላቸው በጥቅም የተገዙ ዓቃቢያነ ሕጎችን፣ ዳኞችን፣ ፖሊሶችንና የመሳሰሉትን የፍትሕ አካላት በመያዝ፣ የማይገባቸውን ጥቅም ያጋብሳሉ፡፡ ንፁኃንን ያስወነጅላሉ፡፡ የሰው ንብረት ይዘርፋሉ፡፡ መንግሥትና ሕግ ባሉበት አገር ውስጥ እንደ ልባቸው ይፈነጫሉ፡፡ በጥቅም የታወሩ የፍትሕ አካላትም ለሕገወጦች ተባባሪ እየሆኑ የፍትሕ ሥርዓቱን ጥቀርሻ ያለብሱታል፡፡ አንዳችም ዓይነት እሴት ሳይጨምሩ ሕገወጦች በሙስና እየከበሩ ያሉት ፍትሕ እንደ ሸቀጥ በገንዘብ እየተገዛ በመሆኑ ነው፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ ነፃነትና ገለልተኝነት እየተጣሰ ፍትሕ መጫወቻ ሲሆን ያማል፡፡ ያንገበግባል፡፡

ራሳቸውን ከሕግ በላይ ያደረጉ በቡድን የተደራጁ ኃይሎች ፍትሕን ጠልፈው የከንቱ ዓላማቸው ማስፈጸሚያ ሲያደርጉ፣ ለሕዝብ ታግለን ደማችንን አፍስሰናል የሚሉ ወገኖች የት ናቸው? ሥርዓተ አልበኞች ፍትሕን በገንዘብ እየሸቀጡ ሕዝቡን የደም እንባ ሲያስለቅሱ ለማኅበራዊ ፍትሕ ታግለናል የሚሉት ምን እያደረጉ ነው? አገርን የመምራትና ሕዝብን የማስተዳደር ሥልጣን ያላቸውስ ምን ይሠራሉ? ትናንት ትግል ላይ ሆነው ዛፍ ጥላ ሥር በፍትሐዊ መንገድ ይዳኙ ነበር የተባሉትስ ታጋዮች የት ናቸው? ከመፈክርና ከአዳራሽ ዲስኩር ያላለፈው ፍትሕን የማስፈን ጉዳይ እስከ መቼ ይድበሰበሳል? ለእነዚህ ጥያቄዎች ሕዝብ ቀጥተኛ መልስ ይፈልጋል፡፡ ሕዝብ ፍትሕ ተሸጦበት የፍትሕ ያለህ እያለ ነው፡፡

በጉልበተኞች ንብረታቸውን የተቀሙ ዜጎች ፍትሕ ሲጠይቁ ተነፍገው ሲያለቅሱ፣ ያለጥፋታቸው ተከሰው በእስር የሚማቅቁ ዜጎች እሪ ሲሉ፣ እስር ቤት ለዓመታት ተዘግቶባቸው ፍርድ ቤት አልቀረብንም የሚሉ ዜጎች ሲጮሁ፣ አገር ሰላም ብለው የወጡ ዜጎች በጉልበተኞች በጭካኔ ሲገደሉ፣ ወዘተ ሰሚ የለም፡፡ በሌላ በኩል አንዱ በተሰጠህ ጊዜ ውስጥ ባለመገንባትህ ካርታህ መከነ ተብሎ ወዲያው ይዞታውን ሲቀማ፣ ሌላው ለዓመታት አጥሮ ተኝቶበት ጠያቂ የለውም፡፡ አንዱ የጠየቀው መሬት ወይም የባንክ ብድር በቀናት ውስጥ ተቀላጥፎ ያለምንም ውጣ ውረድ እቤቱ ድረስ ሲመጣለት፣ ሌላው ለዓመታት ወረፋ ጠብቅ ተብሎ ጊዜውንና ያለችውን ጥሪት ጨርሶ እንዲደኸይ ይደረጋል፡፡ ለዓመታት ፍትሕ ፍለጋ ሲንከራተት ቆይቶ በግፍ ተፈርዶበት ሕይወቱ የሚያልፈውን ዜጋ ቤት ይቁጠረው፡፡ አቤት ሲባል ሰሚ የለም፡፡ ፍትሕን በገንዘብ የሚያናግሩ ሙሰኞች እየደለቡ፣ ንፁኃን ዜጎች ግን አሳራቸውን ይበላሉ፡፡ በጣም ያናድዳል፡፡

የፍትሕ ሥርዓቱ ከአስፈጻሚው አካል ከሚደርስበት ጫና በተጨማሪ፣ በሕገወጦች አማካይነት የሚፈጸምበት ውንብድና ሕዝብን እያስለቀሰ ነው፡፡ በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ የመሸጉ ሕገወጦችና ጉዳይ አስፈጻሚ የሚባሉ ደላሎች ፍትሕን በአደባባይ እየቸረቸሩት ነው፡፡ የድርጅት አባልነትን ላልተገባ ድርጊት የሚጠቀሙበት ፍትሕን የገንዘብ ባሪያ እያደረጉት ነው፡፡ መንግሥት ይህንን አደገኛ ድርጊት ማስቆም ካልቻለ አደጋ አለ፡፡ በፍትሕ መዛባት ምክንያት አንድ ሰው ሲጎዳ፣ ከእሱ በተጨማሪ በዙሪያው ያሉ የቅርብ ሰዎችም ሰለባ ይሆናሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ማኅበረሰቡ ውስጥ በስፋት ሲሰራጭ አገር ትቃወሳለች፡፡ ሥርዓተ አልበኝነት ይነግሳል፡፡ ከዚያም አመፅ ይከተላል፡፡

ፍትሕ ለሁሉም እኩል ተደራሽ እንዲሆን የሚፈለግ ከሆነ ቅድሚያ ለሕግ የበላይነት ይሰጥ፡፡ ሕገወጥነት ላይ ዕርምጃ ይወሰድ፡፡ በየቦታው በቡድን የተሳሰሩ ሕገወጥ ኃይሎች ሰንሰለት ይበጣጠስ፡፡ አገር ወዳድና ንፁኃን ዜጎች በፅናት እንዲታገሉ አመቺና አስተማማኝ ሁኔታዎች ይፈጠሩ፡፡ ከመፈክር የማያልፉ ባዶ ፉከራዎች በቃችሁ ይባሉ፡፡ በሕገወጥ መንገድ የደለቡ ሙሰኞች፣ ተባባሪዎች፣ አድርባዮችና ተላላኪዎቻቸው ይበተኑ፡፡ ሀቀኞች የበላይነቱን ይያዙ፡፡ በፍትሕ ላይ የበላይነት ይዞ አገሪቱን መቀመቅ እየከተታት ያለው አስከፊ ተግባር በአስቸኳይ ይቁም፡፡ ፍትሕ እንዲነግሥ ከተፈለገ ፍትሕ በገንዘብ አይገዛ!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

ስለዘር ፖለቲካ

በሀብታሙ ኃይለ ጊዮርጊስ  ‹‹በቅሎዎች ዝርያችን ከአህያ ነው እያሉ ይመፃደቃሉ›› የጀርመኖች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...

የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዳይዳፈን ጥንቃቄ ይደረግ!

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር አሁንም ጤና አልባ ሆኖ የተለመደው ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ወዲህ ሊሻሻል ያልቻለው የፖለቲካ ምኅዳር ሰሞኑን አዲስ...