ከኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት መጠኑ ያልታወቀ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ዘርፎ ለመሰወር የሞከረው የድርጀቱ ሠራተኛ በቁጥጥር ሥር ዋለ፡፡
በኤርፖርቶች ድርጅት የሰው ኃይል አስተዳደር መምርያ የፔሮል ሠራተኛ መሆኑ የተገለጸው ተጠርጣሪ አቶ ጌታቸው ደበበ ድርጊቱን ፈጽሞ የተሰወረው ጳጉሜን 5 ቀን 2007 ዓ.ም. እንደነበር፣ የኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ ወንድም ተክሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ተጠርጣሪው መቼ በቁጥጥር ሥር እንደዋለ፣ ምን ያህል ገንዘብ እንደወሰደና ተጨማሪ ተጠርጣሪዎች ስለመኖራቸው እንዲያስረዱ የተጠየቁት አቶ ወንድም፣ ‹‹ጉዳዩ በምርመራ ሒደት ላይ ያለ በመሆኑ ዝርዝሩን መናገር አልችልም፡፡ ድርጊቱ ግን ተፈጽሟል፡፡ ከዚህ በላይ መናገር አልችልም፤›› በማለት ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት ግን ተጠርጣሪው በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ይዞ ለጊዜው ተሰውሮ ነበር፡፡ የገንዘቡ መጠን እንዳይታወቅ የኤርፖርቶች ድርጅት ኃላፊዎች ጉዳዩን በሚስጥር መያዛቸውንና የፋይናንስ ክፍሉ በጥብቅ ጥበቃ ላይ መክረሙንም አክለዋል፡፡
ተጠርጣሪው ድርጊቱን ብቻውን እንዳልፈጸመው ጥርጣሬ እንዳላቸው የገለጹት ምንጮች፣ በቁጥጥር ሥር ሲውል በእጁ ላይ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ሳይገኝ እንዳልቀረም ተናግረዋል፡፡ አቶ ወንድም ተጠርጣሪው የወሰደውን ገንዘብ ሳያጠፋ ሙሉ በሙሉ መያዙን ጠቁመዋል፡፡