Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅየወይፈኑ አወራረድ

የወይፈኑ አወራረድ

ቀን:

በዓል በመጣ ቁጥር ለእርድ የሚዘጋጁ ከብቶች፣ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚዘዋወሩት በተለያየ መንገድ ነው፡፡ አንዱ መንገድ በከባድ የጭነት ተሽከርካሪ ማጓጓዝ ነው፡፡ ይህ ፎቶ የፓኪስታን ሰአማ ቲቪ በድረ ገጹ ያወጣው ነው፡፡

************

‹‹ሰላም Vs ጸጥታ››

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ጩኸት እና ረብሻ ስላልታየ፣
ቤትና ንብረት ስላልጋየ፣
አመፅና ኡኡታ ስለሌለ፣
‹‹ሰላም ነው›› ተባለ፡፡
ኧረ ተዉ!
ሕዝቦች በፍርሀት ጸጥ ስላሉ፣
ጸጥታን ሰላም ነው አትበሉ፡፡

  • ዳዊት ፀጋዬ ‹‹አርነት የወጡ ሐሳቦች›› (2003)

*************

እባብ ከሰውየው ተሻለ

በአንድ ወቅት አንድ ድሃ ሰው ወጥመድ የሚሆንለት ጉድጓድ በማዘጋጀት ጉድጓዱን በሣር ሸፍኖ እንስሳትን ያጠምድበት ነበር፡፡ አንድ ቀን ታዲያ ለድኩላ ባዘጋጀው ወጥመድ ውስጥ አንበሳ፣ ነብር፣ ሰው፣ እባብና ተኩላ አንድ በአንድ ጉድጓዱ ውስጥ ወደቁ፡፡

ያጠመደውም ሰው የያዘውን እንስሳ ለማየት ሲመጣ አምስቱን ወጥመዱ ውስጥ ተይዘው አያቸው፡፡ ሰውን ጨምሮ አምስት የተለያዩ እንስሳትን መያዙ አስገረሞታል፡፡

እናም ሁሉም በአንድነት ‹‹ከዚህ ጉድጓድ ውስጥ አውጣንና ውለታህን እንከፍላለን፡፡›› አሉት፡፡

ሰውየውም ‹‹ከበላችሁኝስ?›› ብሎ ሲጠይቃቸው እነርሱም ‹‹በፍፁም አንጎዳህም፡፡ ቃል እንገባልሃለን፡፡›› አሉት፡፡

ሰውየውም በቅድሚያ አንበሳውን ‹‹እኔ በጣም ድሃ ሰው ነኝ፡፡ ከወጥመዱ ብትወጣ ምን ታደርግልኛለህ?›› ብሎ ጠየቀው፡፡ አንበሳውም ‹‹የፈለከውን የቤት እንስሳት ላመጣልህ እችላለሁ፡፡ ሃምታምም ትሆናለህ፡፡›› አለው፡፡

ሰውየውም አንበሳውን ከወጥመዱ አወጣው፡፡

ቀጥሎም ይህንኑ ጥያቄ ነብሩን ጠየቀው፡፡ ነብሩም ‹‹ይህንን ወጥመድ ያዘጋጀኸው ጥሩ ሥጋ ለመብላት ብለህ አይደለም? ስለዚህ እያንዳንዱን ወፍራም በሬ፣ ላም፣ በግና ፍየል አመጣልህና ለቤተሰብህ ከበቂ በላይ ምግብ ይኖርሃል፡፡›› አለው፡፡

ሰውየው ነብሩንም አወጣው፡፡

‹‹አንተስ፣ አያ እባብ?››

‹‹እኔ ደግሞ ከፍተኛ አደጋ ባጋጠመህ ጊዜ አድንሃለሁ፡፡›› ብሎ እባቡ ቃል ገባ፡፡

ነብሩንም አወጣው፡፡

‹‹አንተስ፣ አያ ተኩላ?››

ተኩላውም ‹‹እኔ ምንም ልረዳህ አልችልም፡፡ አንተን ልረዳ የምችልበት አቅም የለኝም፡፡ ሆኖም አንድ ምክር ልሰጥህ እችላለሁ፡፡›› አለው፡፡

ተኩላውንም አወጣው፡፡

ከዚያም በወጥመዱ የተያዘው ሰውዬ ‹‹እኔ ደግሞ እረኛህ ሆኜ ከብቶችህን እጠብቅልሃለሁ፡፡›› ብሎ ‹‹ከብቶች ስላሉህ ከብቶችህን ብቻ ከመጠበቅ ባሻገር ስላንተ ለሌላ ሰው ሳልነግር ምስጢረኛህ እሆናለሁ፡፡›› አለ፡፡

አጥማጁም ‹‹እሺ›› ብሎ ሁሉንም ከወጥመዱ አወጣቸው፡፡ በመጨረሻም ሁሉም ከወጡ በኋላ ተኩላው ሰውየውን ‹‹የእኔ ምክር እነሆ! ሰውየውን ብቻ ተጠንቀቀው፡፡›› ብሎ ወደ ጫካው ሮጦ ሄደ፡፡

ሰውየውም ያጠመደውን እረኛ ይዞ ወደቤቱ ሄደ፡፡ ሌሎቹም ሁሉ የገቡትን ቃል ለመፈፀም ወደየፊናቸው ሄደው ነብሩ ሰውየው ሥጋ እንዲበላ በግና ፍየል ይዞለት መጣ፡፡ ከሁለትና ከሦስት ዓመታት በኋላም አንበሳው የበግ፣ የፍየልና የከብቶች መንጋ አምጥቶ የሰውየውን በረት ሞላው፡፡ ሰውየውም ሃብታም ሆነ፡፡

ታዲያ አንድ ቀን ሦስት ሰዎች በሃብታሙ ሰው በረት አጠገብ ሲያልፉ ምርኮኛው እረኛ ሰዎቹ የሚነጋገሩትን ነገር ይሰማ ነበር፡፡ ከሰዎቹም አንዱ ከብቶቹን ሁሉ እየተመለከተ ‹‹አሃ! ያ ፈረስ በአንበሳ የተሰረቀብኝን የእኔን ፈረስ ይመስላል፡፡›› አለ፡፡

ሌላኛውም ሰው ‹‹ያቺን ላም ደግሞ ተመልከቱ! ከእኔ ላም ጋር በቀለምም ሆነ በመልክ ትመሳሰላለች፡፡ ምናልባትም አንበሳው የእኔንም ላም ወስዷት ይሆናል፡፡›› አለ፡፡

ሦስተኛውም ሰው ‹‹ያንን በሬም ተመልከቱ! የእኔን በሬ ይመስላል፡፡›› አለ፡፡

እረኛውም እያዳመጠ ነበር፡፡ መንገደኞቹ ሰዎች ከብቶቹ የእነርሱ መሆናቸውን አያውቁም ነበር፡፡ ከብቶቻቸው በአንበሳው የተበሉባቸው መስሏቸው ነበር፡፡

ታዲያ አሽከሩ እረኛ ታሪኩን ሁሉ ለሰዎቹ ከመጀመሪያው ከወጥመዱ ጉዳይ አንሥቶ የሆነውን ነገር ሁሉ ነግሯቸው ‹‹ንጉሡ ችሎት ላይ ለምን አትከሱትም? እኔም ምስክር እሆናችኋለሁ፡፡›› ብሎ መከራቸው፡፡

‹‹እንግዲያውማ ምስክር መሆን ከቻልክ መጥተህ ክሰሰውና እናም ውለታህን ከፍለንህ ሃብታም ትሆናለህ፡፡›› አሉት፡፡

በዚህ ዓይነት ሰውየውን በንጉሡ ችሎት ከሰሱት፡፡ በችሎቱም ላይ ‹‹ምስክር አለን፡፡›› አሉ፡፡

ተከሳሹ ሰው ግን ወደ ችሎቱ ቀርቦ ሁሉም እንስሳት የራሱ እንደሆኑና እርሱም ንፁህ መሆኑን ተናገረ፡፡

ንጉሡም ‹‹ከሳሾች ምስክር አለን እያሉ ነው፡፡›› አለ፡፡

ሰውየውም ‹‹እነርሱ እየዋሹ ነው፡፡ ምንም ማስረጃ የላቸውም፡፡›› ብሎ ተከራከረ፡፡

በዚህ ጊዜ አሽከሩ እረኛ በምስክርነት ቀርቦ ሊናገር ሲል ንጉሡ የሃብታሙን ሰው ሃያልነት ስለፈራ ሰውየውን ለመስቀል ምክንያት ሲፈልግ ስለነበረ በሰውየው አናት ላይ ሸምቀቆ ገመድ በማዘጋጀቱ ሰውየው ተስፋው ተሟጦ ነበር፡፡

በዚያች ቅፅበት ከየት መጣ ሳይባል እባቡ መጥቶ ምስክሩ አንድም ቃል ከመናገሩ በፊት ነደፈው፡፡ የተነደፈውም ሰው ራሱን ስቶ ወዲያው ሞተ፡፡

የተከሰሰውም ባለጸጋ ሰው ንጉሡን ‹‹ጃንሆይ ሆይ! ይህ እንግዲህ የእግዚአብሔር ፍርድና የታላቅነቱ መገለጫ ነው፡፡ ሃሰተኛ ምስክር ስለሆነ ሞተ፡፡›› አለ፡፡

ንጉሡም ሰውየው የተናገረው ነገር እውነት ነው ብሎ በነፃ አሰናበተው፡፡

  • በወርቁ ዓለሙ የተተረከ የከፋ ተረት (ከኢትዮጵያ ተረቶች ገጽ)

******

ኑሯችንን በአባባሎች

በኃይሉ ገ/እግዚአብሔር

አንድ፡-የቅጠል ሰፈር ነዋሪዎች የቧንቧ ውሃ ካጡ ሦስት ዓመት ሆናቸው፡፡ ምን እየጠጣችሁ፣ በምን እያበሰላችሁ፣ በምን እየታጠባችሁ ትኖራላችሁ? የሚለውን ጥያቄ ነዋሪዎቹ ሲጠየቁ፣ ‹‹አቅሙ ያለው በሸክም፤ የሌለው በግዢ ከሌላ ሰፈር እያመጣን ነዋ!›› ሲሉ በሃዘን ይመልሳሉ፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅ የመታጠብ ቀን በየዓመቱ ጥቅምት 5 እንደሚከበር ይታወቃል፡፡ በዚህ ቀን የዓለም ሕዝብ አካል የሆኑት የቅጠል ሰፈር ነዋሪዎች፣ ‹‹ባይሆን የዓለም እጅ መታጠብ ቀንን ምክንያት በማድረግ እጃችሁን ታጠቡ!›› ሲባሉ አሉ እንዲህ ሲሉ አንጎራጎሩ አሉ፤ ‹‹ውሃ የለም እንጂ ውሃማ ቢኖር፣
እንኳን እጅ ቀርቶ ይታጠባል እግር!››

ሁለት፡- ችግር ያጎለሰሰው አባወራ የበዓልን ወግ ለቤተሰቦቹ የማሳየትና ከጎረቤቶቹ እኩል የመሆን ሃሳብ በልቡናው አደረ፡፡ ተበድሮም ተለቅቶም እንዳቅሙ ዶሮ ገዛ፡፡

ዶሮዪቱ ከተገዛች ሦስት ቀን ቢሆናትም ወደ ጉሮሮዋ የምትሰደው የእህል ዘር አላገኘችም፡፡ ዓውደ ዓመቱን ምክንያት በማድረግ አባወራው የተሳለ ቢላ ይዞ ወደ እርሷ ሲቀርብ ዶሮዋ ባዘነ የዶሮ አንደበት፣ ‹‹ኧረ ጌቶች ባይሆን ቀምሳ ታረደች ቢባል ምን አለበት? ሳያበሉኝ፣ ሊበሉኝ!?›› አለች አሉ፤ ከዚህ ልቦለድ ከሆነው ታሪክ ቀልጠፍ ያለውን አባባል እንደ ተረት እንውሰድ፤ ‹‹ሳያበሉኝ፣ ሊበሉኝ!?›› አለች ዶሮ፡፡

ሦስት፡- የቀበሌ መዝናኛ ክበብ በራፍ ላይ ቆሟል፤ ለምኖ አዳሪው፡፡ ይህ ነዳይ የቆመው፣ ‹‹ልግባ ወይስ አልግባ? ቀይ ወጥ አዝዤ ልብላ ወይስ አልብላ?›› በማለት እያሰላሰለ አይደለም፡፡ ገንዘብ ከየት አምጥቶ? በፀሐይ ብዛት ውሃ ውሃ ቢለው፣ ‹‹የእግዜሩን ውሃ›› እንዲሰጡት ለመማፀን እንጂ፡፡ እግረ መንገዱን ክበቡ ውስጥ የተከፈተውን ቴሌቪዥን እያየ ነው፡፡ አንድ ብርጭቆ ውሃ እንዲሰጡት ቁሞ የሚጠባበቀው ይህ ለምኖ አዳሪ፣ ‹‹ኢትዮጵያ በዕድገትና በብልፅግና ጎዳና ላይ እንደምትገኝ ተገለፀ!›› የሚል ዜና ሰማ፡፡ በውሃ እጦት ሁለመናው የደረቀው ለምኖ አዳሪ እንዲህ ብሎ ጠየቀ አሉ፤ ‹‹አገራችን በለፀገች? እኔ የት ሄጄ?›› ከዚህች ንግግር እንዲህ የምትል ሸንቃጣ አባባል እንውሰድላት፤ ‹‹አገርህ በለፀገች! ቢሉት እኔ የት ሄጄ?›› አለ ለምኖ አዳሪው፡፡

አራት፡- አቶ ጥጉ አዝነዋል፡፡ ባለፈው ፋሲካ ዶሮ ሊገዙ ፈልገው ገበያ ወጥተው ነበር፡፡ የያዟት ገንዘብ ጥቂት ነበረችና እንዲቀንስላቸው አንዲት እግሯን የተጎዳች አቅመ ደካማ ዶሮ አንስተው ዋጋ ጠየቁ፡፡ መቶ ሃያ ብር ተባሉ፡፡ ‹‹ምነው ጌታዬ!›› አሉ እዝን ብለው፡፡ ነጋዴ ጌታ ከሆነ ቆይቷልና፣ ‹‹ምነው ጌታዬ አንድ እግሯ እኮ አንካሳ ነው!›› አሉ በሚያሳዝን ድምፅ፡፡ ነጋዴው ግን ሳቀ እንጂ አላዘነም፡፡ ‹‹አባባ ዶሮውን የፈለጉት ለዳንስ ነው እንዴ!›› አላቸው አልቀንስም ለማለት፡፡ አቶ ጥጉ እፍር አሉ፡፡ ዶሮዋን ካነሱበት ሳጠራ ላይ ቁጭ አደረጓት፡፡ ይኸው አሁን ለእንቁጣጣሽ ደግሞ ከድመት ከፍ ያለች ከበግ ያነሰች በግ ሊገዙ ገበያ ሄደው ቢጠይቁ አንድ ሺህ ብር ተባሉ፡፡
«ጌታዬ ቀንስልኝ!» አሉ በልመና ዓይነት፡፡ «እሺ ስንት ይገዛሉ?» አላቸው ጅንን ብሎ፡፡
«ስድስት መቶ ብር ሽጥልኝ» ነጋዴው ሳቀ፤ አቶ ጥጉ ግን ተሳቀቁ፡፡ «አባባ በስድስት መቶ ብር እንኳን ሥጋው ድምፁ አያዋጣኝም!» ሲል አሾፈባቸው፡፡ አቶ ጥጉ እንደለመዱት እፍር አሉ፡፡ ጭራ የመሰለ ላት ያላትን ኮሳሳ በግ ከባልንጀሮቿ ጋር ቀላቀሏት እና እንዲህ እያንጎራጎሩ ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡ «እንደ ኢየሩሳሌም እንደ አክሱም ፅዮን፣ ተሳልሜው መጣሁ ዶሮና በጉን፡፡»

አምስት፡- አርፍዶ ቢሮ በመድረሱ አለቃው ሊበሉት ደርሰዋል፡፡ ‹‹ምነው አረፈድክ?›› ከላይ አንስቶ መሬት በሚደባልቅ አስተያየት እያዩት፡፡

‹‹ታክሲ…!››
‹‹ታክሲ ምን?››

‹‹አጥቼ!››

‹‹በጠዋት አትነሳም ነበር!››

‹‹ኧረ በጠዋት ነበር የተነሳሁት!››

‹‹አይ! በጠዋት ከተነሳህ ታክሲ አይጠፋም!››

‹‹ኧረ ይጠፋል!››

‹‹እንዴት? …የፈለግከው የሚሸጥ ነበር እንዴ!?›› ብስጭት በሚጠራው ተራቢ ሳቃቸው እየተርገፈገፉ፡፡ ወጣቱ ተናደደ፤ ‹‹በዚህ ሰዓትም ልመጣ የቻልኩት

ለረዥም ሰዓት ወረፋ ጠብቄ ነው!›› አለ እልህ እየተናነቀው፡፡

‹‹ለምኑ ነው ወረፋ?›› ጉትት ባለ ድምፅ፡፡

‹‹ለታክሲ!››

‹‹ለታክሲ ወረፋ!?›› በመገረም ጮኹ፡፡

‹‹አዎ ወረፋ!››

‹‹…እ …እንዴት ነው ታክሲው ውስጥ ዳቦ ይሸጣል እንዴ!?›› አሁንም በሳቅ ተርገፈገፉ፡፡ የወጣቱ ብስጭት ጣራ ነካ፡፡ በንዴት በሩን በላያቸው ላይ ጠርቅሞት ሊወጣ ምንም አልቀረውም፡፡

ከዚች ቁንፅል ገጠመኝ፣ የወጣቱን አለቃ ንግግር እንደ አባባል እንውሰዳት፤

‹‹ታክሲ ለመሳፈር ወረፋ እየጠበቅኩ ነው ቢለው፤ ‹‹ውስጡ ዳቦ ይሸጣል

ወይ!?›› አለ አሉ ግራ የገባው፡፡

ስድስት፡- አቶ ደንበጃ የተቃዋሚ ፓርቲ በመመሥረትና በማፍረስ፣ በማደስና በማዋሃድ እውቅና ያላቸውና በዚህ ታላቅ የፖለቲካ ሥራም ረዥም ዓመታትን ያሳለፉ ናቸው፡፡

እኚህ ታላቅ ፖለቲከኛ በዚህ ተግባራቸው ዘወትር እንደኮሩ ነው፡፡ ፖለቲካና ፖለቲካ መሰል አገራዊ ጉዳይ በተነሳ ቁጥር፣ ‹‹ያልፈሳሁበት የፖለቲካ ዳገት የለም› አለች አህያ›› ብለው መተረት ይቀናቸዋል፡፡ /ጉድ ነው፤ አህያዋ የየትኛው ፓርቲ አባል ትሆን?/

አንድ ቀን እንደተለመደው አቶ ደንበጃ የተገኙበት ቦታ ሁሉ የማይቀረው ፖለቲካዊ ጉዳይ ተነስቶ ክርክር ተጀመረ፡፡ በዚሁ ዕለትም እንደ ሁልጊዜው መግባባት አልተቻለም፡፡ (ልክ በአንድ ፓርቲ ውስጥ እንዳሉ ሰዎች ያለ አለመግባባት)
ሃሳባቸውን የሚደግፍ በማጣታቸው ክፉኛ የተበሳጩት አቶ ደንበጃ፣ ‹‹ስሙ!›› አሉ፤ ‹‹ስሙ! እኔ እኮ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ጥርሴን የነቀልኩበት ነው!››

ከአቶ ደንበጃ ተሟጋቾች አንዱ በፖለቲካ ጦስ ብዙ መከራ የተቀበለ ነበርና፣ ‹‹አባት የዚህ አገር ፖለቲካን በጥርስዎ ብቻ ከተገላገሉት ተመስገን ነው›› አላቸው ትክዝ ብሎ፡፡ ወደ አባባል ብንቀይረው፣ ‹‹የዚህ አገርን ፖለቲካ ጥርሴን የነቀልኩበት ነው› ቢለው፣ ‹‹በጥርስህ ብቻ ከተገላገልከው ተመስገን ነው›› አለው አሉ ከማዕከላዊ እስር ቤት የወጣ አንድ አሳረኛ፡፡ (ከፌስቡክ ገጹ የተወሰደ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...