Tuesday, December 6, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  የተመረጡ ፅሑፎች

  አትየኝ አልይህ ምን ይሉት ፈሊጥ ነው?

  ሰላም! ሰላም! የተወደዳችሁና የተመረጣችሁ ውድ ወዳጆቼ እንደምን ቆያችሁልኝ፡፡ እኔማ ይኸው ባሻዬ እንደሚሉት፣ ‹‹የቆምነው በእግሮቻችን አይደለም፣ በእግዜሩ ምሕረት አንጂ፤›› ብለው ነበር፡፡ ልክ ብለዋል ባሻዬ፡፡ ሺሕ ዓመት ኑሩልን፡፡ በየሠፈር በየቀዬው እርስዎን የመሰለ የአገር ሽማግሌ ያብዛልን ከማለት ውጪ ምን እጨምርበታለሁ? እርስዎን የመሳሰሉ ለእርቅ የቆረጡ፣ ልጆቻቸውን የሚቆጡ የሚመክሩ ምርጥ ምርጥ ሽማግሌዎች ያብዛልን፡፡ የቆምነው በእግሮቻችን አይደለም ከሚለው የባሻዬ ሐሳብ ላይ የምጨምረው ነገር ቢኖር፣ የቆምኩት በባሻዬ ምክርም ጭምር ነው፡፡ እኔስ በሠፈሬ ምን የመሰሉ ሦስት መንግሥታትን የተመለከቱ መካሪ ችሮኛል፡፡ አንቺ አገር እንደኔው መካሪ አያሳጣሽ፡፡ ከዚህ የተሻለ ምርቃት ምን አለ?

  የባሻዬ ልጅ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በአንድ ሚዲያ ላይ ቀርቦ በሰጠው አስተያየት ምክንያት፣ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ እየተሰነዘረ ያለው ነገር እጅግ አስገርሞታል፡፡ በተለይ ኃይሌ ለኢትዮጵያ ያመጣውን ክብርና ማዕረግ ነክ ነገሮች ሲጻፉ ተመልክቶ እርሱም፣ ‹‹…እንዲያው አንዳንዱን ሰው ምን ነክቶታል?›› በማለት ምላሽ ሊሰጥ ነበር፡፡ ዳሩ ግን ነገርዬው ውኃን መውቀጥ ነው በማለት ተወው እንጂ፡፡ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ኃይሌ የኢትዮጵያ ባለውታ ነው፡፡ ለበርካታ ጊዜያቶች አስመክቶናል፡፡ አስደስቶናል፡፡ አሁንም እያደረገ ያለው ነገር እሰየው የሚያሰኝ ነው…›› በማለት ለኃይሌ ጥብቅና ቆሞ ይከራከርለታል፡፡

  በእርግጥ ባሻዬም ቢሆኑ ግን ለኃይሌ ያላቸው ፍቅር እጅግ የላቀ ነው፡፡ ዳሩ ግን የኢትዮጵያን ሕዝብ 60 ሚሊዮን ብሎ መጥራቱና ከዚያም ሲያልፍ ኢትዮጵያን ለመምራት አላንስም ዓይነት አስተያየት በመስጠቱ የተሰማቸውን ቅሬታ ሲያሰሙ አድምጬያቸዋለሁ፡፡ ‹‹ማንም ሰው ተነስቶ የፈለገውን የመሆን ምኞቱን ሊያራምድ ይችላል፡፡ ዳሩ ግን ኢትዮጵያን የምታህል ታላቅ አገር መምራትን ስናስብ ትንሽ ብናስተውል መልካም ነው…›› ባይ ናቸው፡፡ እንዲያውም ባሻዬ መሪዎች ይወለዳሉ ብለው ከሚያምኑት ወገን ናቸው፡፡

  እኔማ ቀጣዩዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ውዷ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ ብትሆንልኝ ደስታዬ ነው፡፡ እርሷ መልካም ሴት እንደሆነች ጠንቅቄ አውቃለሁ! ባሻዬ ይህን አስተሳሰቤን አይወዱትም፡፡ ለጨዋታ እንኳን ሳነሳው፣ ‹‹ብዙ ያልገባህ ነገር አለ…›› ብለው ይቆጣሉ፡፡ እኔም እንዲያወሩ እገፋፋቸዋለሁ፡፡ ‹‹አየህ ኢትዮጵያ ታላቅ ናት! ታላቅነቷን ለማሳነስ የመጣ የትኛውም የውስጥም ሆነ የውጭ ጠላት አፍሮና ተዋርዶ በአንድ መንገድ መጥቶ በሰባት መንገድ እንደተበተነ አትዘንጋ፤›› ይላሉ፡፡ ባሻዬ ስለኢትዮጵያ ክፉ ሲነሳ አይወዱም፣ በምሬት ይንገሸገሻሉ፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ የእኛ ናት፡፡ የሌላ የማንም አይደለችም፡፡ ማንም እየተነሳ እኔ አንቺን ለመምራት አላንስም ሊላት አይገባም፤›› ብለው ይቆጣሉ፡፡

  እንግዲህ ባሻዬን እንዲህ እንዲንጨረጨሩ ያደረጋቸው ነገር ቢኖር ኃይሌ ኢትዮጵያን የመምራት ዝንባሌ በውስጤ ፀንሻለሁ ማለቱን ሰምተው እየተብሰለሰሉ ባሉበት ወቅት፣ ሌላ ተጨማሪ የማንጠግቦሽን ጉዳይ አንስቼባቸው ነው፡፡ ጆርጅ ዊሃ ከእግር ኳስ ተጫዋችነት ተነስቶ ፕሬዚዳንት ለመሆን ቻለ የሚል ወሬ ከልጃቸው ሰምተው ሲቃጠሉ ነበር፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ አስቂኝ ነው፡፡ እንዲህም ሲሉ አድምጫቸዋለሁ፡፡ ‹‹እንዴት ሆኖ ነው አንድ ኳስ ሲያንከባለል ዘመኑን የፈጀ ሰው አገር ልምራ ብሎ ሲመጣ መሪነት የሚሰጠው?›› ብለው በላይቤሪያ ሕዝብ ይማረራሉ፡፡ በዚህም አያበቁም ወደ አገራችን ተመልሰው፣ ‹‹አትሌት ኃይሌ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ውስጥ የተሰጠውን ኃላፊነት ተወጥቶ በርካታ አትሌቶችን ካፈራልንና የቀድሞ ክብራችንን ከጠበቀልን፣ ከዚህ በላይ ኢትዮጵያ ምንም አትጠብቅበትም…›› ሲሉ ነበር፡፡ ቀጠሉ ባሻዬ፣ ‹‹ጉድ እኮ ነው በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሆን ጠዋት ጠዋት ተነስታችሁ ሱሉልታ ደርሳችሁ ካልመጣችሁ የቀበሌ መታወቂያችሁ አይታደስም ሊለን ነው?›› ሲሉ ሳቄ አመለጠኝ፡፡

  መቼም የሽማግሌ ትችት ከባድ ነው፡፡ ከኃይሌ አናት ላይ አልወርድ ብለዋል፡፡ እንዲያው አሁን ማን ይሙት ወደ ሥልጣኑ ቢመጣ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥቡ ተቀይሮ የኦሎምፒክ ሚኒማ ያሟላ ብቻ በሆነ ነበር፡፡ ይኼኔ ራሴን መቆጣጠር አልቻልኩም ክትክት ብዬ ሳቅኩላቸው፡፡ እኔ ግን ከባሻዬ ሐሳብ ጋር በፍፁም አልስማማም፡፡ ምክንያቱም እኔም ብሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ምራን ብሎ ከመረጠኝ ደህና አድርጌ የመምራት አቅም አለኝ ብዬ አምናለሁ፡፡ ማንጠግቦሽ እንደመከረችኝ ከሆነ የራስ መተማመኔን ዕለት ከዕለት ማሳደግ አለብኝ፡፡ ስለሆነም ማን ያውቃል በሚቀጥለው ምርጫ ላይ ከበርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እንደምፋጠጥ ሙሉ እምነቴ ነው፡፡

  ልዩ ምልክቴ ምን ቢሆን ይሻለኛል? አብዛኛዎቹ ምልክቶች ተይዘው አልቀዋል እነ ንብ፣ ቀፎ፣ ማረሻ፣ ዶማ፣ ጀበና፣ ማንኪያ… ተይዘው አልቀዋል፡፡ ልዩ ምልክቴ ማንኪያ ነው ያለው ተወዳዳሪ እኔን ከመረጣችሁኝ የስኳር ተራራ በየቀበሌያችሁ እሠራላችኋለሁ የሚል የምርጫ ቅስቃሰ እንደሚያደርግ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ ታዲያ የእኔ የደላላው የአምበርብር ምንተስኖት የምርጫ ምልክት ምንድነው? አያድርገግብኝና ወደፊት በጣም ሀብታም ሆኜ ፓርላማ ከገባሁና ከመረጣችሁኝ፣ የቤት ካርታ ነው ምልክቴ፡፡

  ወዳጆቼ ሰሞኑን እየገባልኝ ያለውን ‘ዝግ’ መግለጥ አልችልም፡፡ በተለይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሸጥ መለወጥን ከልክሎ ቢሆን ኖሮ ምን ይውጠኝ ነበር፡፡ ዳሩ ግን ከወትሮው በተለየ ሁኔታ የእኛ ሰው መሸጥና መለወጥን ሥራዬ ብሎ ተያይዞታል፡፡ ቤት ነሽ፣ መኪና ነሽ፣ መሬት፣ የንግድ ሱቅ፣ አክሲዮን… ኧረ የቱን ዘርዝሬ የቱን እተወዋለሁ? ብቻ የዝግ ዓይነት እየጎረፉልኝ ነው፡፡ ሐበሻ ስንት ጥሪቱን አሟጦ የሠራውን ቤት እየቸበቸበው ነው፡፡ እኔማ ሥራ ባይሆንብኝ ኖሮ ኧረ ተው አትሽጡ፣ እንደዚያ ዋጋ ከፍላችሁ የሠራችሁትን ቤት እንደ ዋዛ ባትሸጡት ይሻላል ብዬ ብመክራቸው ደስ ባለኝ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እኔ ደላላ ነኝ፡፡ በተቻለኝ አቅም ሰው ያለውን ሁሉ እንዲሸጥ በማሳመን ላይ የተመሠረተ የገቢ ምንጭ ነው ያለኝ፡፡ ስለዚህ የሚገዛ ከተገኘ ከሁለት ዓይን አንዱን ሸጠው ብዬ የማሳመን ኃላፊነት ነው ጫንቃዬ ላይ የተሸከምኩት፡፡ አሁን ግን ምክንያቱን በውል ያልተረዳሁት ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ከልመና ያልተናነሰ ቤታቸውንና ንብረታቸውን እንድሸጥላቸው እየተማፀኑኝ ነው፡፡

  ታዲያ እኔስ ምኔ ሞኝ እንደ ጉድ እያደራሁት ነው፡፡ ለመሸጥ ደግሞ ማን ብሎኝ እቸበችበዋለሁ፡፡ በዚሁ አጋጣሚ የባሻዬ ልጅ አንድ ለጊዜው ስሙ የማይጠቀስ የአፍሪካ አገር ደላላ ያመጣውን ማስታወቂያ ነግሮኝ ነበር፡፡ ያ ጉደኛ ደላላ፣ ‹‹የሚሸጥ መኪና፣ ቤት፣ እንዲሁም የተለያዩ ንብረቶችን መሸጥ ለምትፈልጉ ከዚህ በታች በምታገኙት አድራሻችን ልታገኙን ትችላላችሁ፡፡ ሳይውል ሳያድር ሸጠን ገንዘብዎን በእጅዎ እናስገባልዎታለን፡፡ በበርካታ ደንበኞቻችን ጥያቄ መሠረት ደግሞ በቅርቡ ኩላሊትና የመሳሰሉትን የሰውነት ክፍሎች ወደ ውጭ አገር ኤክስፖርት ማድረግ ስለምንጀምር፣ በቀን ከሁለት ሊትር ያላነሰ ውኃ በመጠጣት የኩላሊታችሁን ጤንነት እንድትጠብቁ፣ እንዲሁም ኦርጋኒክ የሆኑ ምግቦችን በመመገብ የውስጥ ጤንነታችሁን እንድትጠብቁ በአክብሮት እንገልጻለን፤›› ይላል፡፡ ኧረ ጎበዝ ስምንተኛው ሺሕ ደረሰ እንዴ? የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ዋናው የውስጥ ጤንነት ነው፡፡ ፊትማ ማሳያ ‘ዲስፕሌይ’ ነው፤›› ያለኝን አስታውሳለሁ፡፡ በዚህ ያበደ ዘመን ምን ይባላል ታዲያ?

  ይህችን አባባል ለብዙ ነገር እጠቀምባታለሁ፡፡ ‹‹ዋናው የውስጥ ጤንነት ነው፡፡ ውስጣችን ጥሩ ከሆነ ሁለመናችን ሰላም ይሆናል፡፡ አለበለዚያ ግን ዝም ብሎ ቀለም ብቻ ነው የምንሆነው…›› እያልኩ ለጓደኞቼ በቢራ ሰዓታችን ላይ ሳብራራላቸው፣ እንደኔ ያለ ምጡቅ ደላላ ምድር ላይ ሌላ መፈጠሩን ይጠራጠራሉ፡፡ በእርግጥ ይህ ጥርጣሬ እኔ ውስጥም አይጠፋም፡፡ እኔን የሚመስል ደላላ ከምድር ጫፍ እስከጫፍ ቢፈለግ ይገኝ ይሆን? ምክንያቱም የባሻዬ ልጅ አንዲት ዕውቀት ነብስያዬ ላይ ሲዘራብኝ ምንም ሳልቀንስ፣ ይልቁንም አብዝቼና አብራርቼ ለወዳጆቼ አደርሳለሁ፡፡ ይህንን የሰሙ ሁሉ ይደመማሉ፡፡ ደላላ መሆን አልነበረብህም እያሉ ያላሰብኩትን ያሳስቡኛል፡፡ ብቻ የባሻዬ ልጅ እንዳለው ዋናው ውስጥ ሰላም ሲሆን ነው፡፡ የሚለውን አባባል ደላሎች በሌላ እንደሚተረጉሙብኝ አይጠፉኝም፡፡ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ግን ያወራሁት ስለውስጥ ጤንነት ነው፡፡

  እያንዳንዱን ነገር ወደ ፖለቲካ መቀየር የሚወደው ወዳጄ እኔ የተናገርኩትን ነገር ወስዶ የራሱን ነገር ጨማምሮ እንዲህ እያለ ሲያወራ ሰምቼው ገረመኝ፡፡ ‹‹ዋናው የውስጥ ሰላም ነው፡፡ እንጂማ የቱንም ያህል ሕንፃ ቢሠራ፣ የቱንም ያህል ልማት ተገኘ ቢባል፣ ባለ ሦስት ዲጂት የኢኮኖሚ ለውጥ መጣ ቢባል እንኳን፣ የውስጥ ሰላም ከሌለ በጭንጫ ላይ እንደ በቀለ ዛፍ ነው እያለ…›› ሲያብራራ ሰምቼው ስቄለታለሁ፡፡ ‹‹አሁንም ቢሆን የውስጥ ጤንነታችን ላይ እንሥራ፡፡ ውስጣችንን እያመመን ውጪያችን ቢሽቆጠቆጥ የትም የማይደርስ አርቲፊሻል ውበት ነው…›› እያለ ሲዘባርቅ ሰምቼው በኋላ ደላላው አምበርብር ምንተስኖት ነው ይህንን ሐሳብ ያራመደው እንዳይል ሰግቼ ካጠገባቸው ጠፋሁ፡፡ ከእርሱ ተለይቼ ስራመድ ከግጥም አልፎ እያንጎራጎረ ነበር፡፡ ምን ብሎ አትሉኝም? የዘሪቱን ዘፈን በራሱ ግጥም ቀይሮ፣ ‹‹ፖለቲካው አርቲፊሻል›› ነዋ፡፡

  ባሻዬ ሞያሌ ሄጄ ለቅሶ መድረስ አለብኝ ብለው ከልጃቸው ጋር ሲከራከሩ ነው የዋሉት፡፡ ልጃቸው በዚህ ጊዜ እንኳንስ ሞያሌ፣ ቤተ ክርስቲያን ሲሳለሙ ሲወጡ በሰላም መግባታቸውን አሥር ጊዜ ደውሎ ካላረጋገጠ አይሆንለትም፡፡ በተለይ ከሽምግልናቸው የተነሳ አንድ ደንባራ ሾፌር ቢወጣባቸውስ እያለ ይጨነቃል፡፡ እሱ ብቻም አይደለም የት ደርሰው የት ይቀራሉ? ጀምረን የማንጨርሰውን ነገር እያነሳን ስንጥል ዓለም ጥሎን መንጎዱን ሳስብ በጣም ይደንቀኛል፡፡ አንዳንዴ የሕይወትን ውጣ ውረድ እያሰብኩ እንደ ዋዛ የነጎደውን ዕድሜዬን ጉዳይ ሳሰላስል ልጅነቴ ይናፍቀኛል፡፡ ያ በንፅህና የተሞላ ልብና በግልጽነት የተዋበ አዕምሮ ዝጎ የገንዘብ፣ የዝና፣ የሥልጣን ጥማት አውሬ ያደረገውን የሰው ልጅ ከንቱነት ሳስብ ውስጤ ይከፋል፡፡ ከሁሉም ከሁሉም ግን ከተሳሰብንና ከእኔ ይልቅ የአንተ ይቅደም የሚል ቅን ልቦና ውስጣችን ቢኖር ኖሮ እንኳንስ ለመጋደል፣ ለመኳረፍ ጊዜ ይኖረን ነበር ወይ? ወይ ነዶ? ግና አሁን አትየኝ አልይህ እየበዛ ስለሆነ ረገብ ብንልስ? መልካም ሰንበት!

  Latest Posts

  - Advertisement -

  ወቅታዊ ፅሑፎች

  ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት