Friday, March 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊእነ አቶ መላኩ ፈንታ የአጣሪ ጉባዔውን ውሳኔ በመቃወም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ይግባኝ...

እነ አቶ መላኩ ፈንታ የአጣሪ ጉባዔውን ውሳኔ በመቃወም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ይግባኝ አሉ

ቀን:

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የቀድሞውን የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 622/2001ን የሚተካውን አዲሱን የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 እነሱ የተከሰሱበትን የወንጀል ድርጊት እንደማያስቀር በመግለጽ፣ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በአብላጫ ድምፅ የሰጠውን ውሳኔ የተቃወሙት እነ አቶ መላኩ ፈንታ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲያርምላቸው የይግባኝ አቤቱታ አቀረቡ፡፡

የይግባኝ አቤቱታውን ያቀረቡት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት በመዝገብ ቁጥር 141352 እና 141356 ጉዳያቸው በመታየት ላይ የሚገኙት፣ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ መላኩ ፈንታ፣ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ገብረ ዋህድ ወልደ ጊዮርጊስና የኦዲት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የነበሩት አቶ በላቸው በየነ ናቸው፡፡

የተከሰሱበትን የወንጀል ድርጊት ቀሪ የሚያደርገው አዲሱ አዋጅ በሥራ ላይ መዋሉንና በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22(2) በተደነገገው መሠረት እነሱን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰው፣ ጉዳያቸውን በማየት ላይ ለሚገኘው ፍርድ ቤት ክሳቸው እንዲያቋርጥላቸው መጠየቃቸውን አስታውሰዋል፡፡

ነገር ግን አዲሱ አዋጅ አንቀጽ 182፣ ‹‹በቀድሞው ሕግ የተጀመሩ ጉዳዮች በነበሩበት ይቀጥላሉ፤›› በማለቱ፣ ጉዳዩን እያየው ያለው ፍርድ ቤት አዲሱ አዋጅ እነሱ የተከሰሱበትን ወንጀል ቀሪ የሚያደርግ መሆኑን አምኖ፣ አንቀጽ 182 ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22(2) ጋር የሚቃረን በመሆኑ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ለትርጉም የላከው ቢሆንም ጉባዔው በአብላጫ ድምፅ ‹‹አይቃረንም፣ አይጋጭም›› ብሎ የሰጠው ውሳኔ አግባብ አለመሆኑንና የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 25 (ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል ነው) የሚለውን ድንጋጌን የሚጥስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አጣሪ ጉባዔው የጉምሩክ አዲሱ አዋጅ መታየት ያለበት ከወጣበት ዓላማ አኳያ እንጂ፣ በቀድሞ አዋጅ ለተቀጡ ወይም ለተከሰሱ ይጠቅማል ወይም አይጠቅምም ከሚለው ቀጥተኛ መነሻ መታየት እንደሌለበት የገለጸውን የውሳኔ ሐሳብ፣ ‹‹የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ የጣሰ አባባል፤›› ብለውታል፡፡

የጉባዔው አባባል ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22(2) ድንጋጌ ጋር እንዴት እንደሚጋጭ ያስረዱት አመልካቾቹ፣ ‹‹አዋጆች የተለየ ዓላማ ይዘው ከወጡ ወይም ተከሳሾችን እንዲጠቅሙ ወይም እንዲጐዱ ተደርገው ከወጡ›› ተብሎ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ላይ ተለይቶ የተቀመጠ ነገር ሳይኖርና ጉባዔው በቀጥታ ከድንጋጌው ጋር ማየት ሲገባው፣ በማይገባ መልኩ ተርጉሞ ‹‹የአዋጁ አንቀጽ 182 እና የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22(2) አይጋጩም›› ብሎ መወሰኑ ስህተት መሆኑን ጠቁመው እንዲታረም ጠይቀዋል፡፡

መሸጋገሪያ ድንጋጌው (አንቀጽ 182) ‹‹በሌሎች ሕጐች የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ›› የሚለው የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 5(3) ድንጋጌን ማለትም ‹‹የተሻረ ሕግ በነበረበት ጊዜ የተፈጸመ ወንጀል ሲኖርና በዚህ ሕግ ግን እንደ ወንጀል ያልተቆጠረ ሲሆን፣ ሊያስከስስም ሆነ ሊያስቀጣ አይችልም፤›› የሚለውን እንደማይመለከት ጉባዔው በውሳኔው መግለጹን ተቃውመዋል፡፡

አቤቱታ አቅራቢዎቹ በይግባኝ አቤቱታቸው እንደገለጹት፣ የቀድሞው አዋጅ በአዲሱ አዋጅ ተተክቷል፡፡ በአዲሱ አዋጅ አንቀጽ 181(1) የቀድሞው አዋጅ ሙሉ በሙሉ መተካቱ ተገልጿል፡፡

ከቀድሞውና ከአዲሱ አዋጆች ውጪ ሌላ አዋጅ ሳይኖር አጣሪ ጉባዔው ‹‹ከሌሎች ከጉምሩክ ሕግ ጋር የተያያዙ ሕጐች እንጂ›› ብሎ ትርጉም መስጠቱ፣ የሌሉ ሕጐች (ያልተጻፉ ሕጐችን) እንዳሉ አስመስሎ መሆኑንና ይህ ሕግ ደግሞ ስህተት በመሆኑ፣ አባባሉ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22(2) ጋር እንደሚጋጭ ገልጸው እንዲታረም ጠይቀዋል፡፡

አጣሪ ጉባዔው በፍርድ ቤት ሥራ በመግባት ጉዳዩ በቀድሞ አዋጅ እንዲታይ መወሰኑ አግባብ አለመሆኑን የገለጹት አመልካቾች፣ ፍርድ ቤቱ ለትርጉም የላከው አዲሱ አዋጅ ለተከሳሾቹ (ለእነሱ) እንደሚጠቅም አምኖ፣ አንቀጽ 182 ግን ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22(2) ጋር ስለሚጣረስ ትርጉም እንዲሰጥበት ቢሆንም፣ ጉባዔው ‹‹ይቃረናል ወይም አይቃረንም›› ብሎ ከመወሰን አልፎ፣ በኋለኛው ሕግ መታየት እንዲቀጥል መወሰኑ በፍርድ ቤቱ ሥራ ጣልቃ መግባት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የኋለኛ ሕግ ለተከሳሹ ጠቃሚ ሆኖ ሳለ፣ እንዳይፈጸም መከልከል የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ ተፈጻሚነት የሚያሳጣና የተከሳሾችን (ይግባኝ ባዮችን) ሕገ መንግሥታዊ መብት የሚጥስ መሆኑን በመጠቆም እንዲታረምላቸው ጠይቀዋል፡፡

አጣሪ ጉባዔው የመሸጋገሪያው ድንጋጌ (አንቀጽ 182) ሌሎች ከጉምሩክ ጋር የተያያዙ ሕጐችን ተፈጻሚነት ጠብቆ፣ የሕጐች ሁሉ የበላይ የሆነውን የሕገ መንግሥት ድንጋጌና የሕገ መንግሥት መሠረት ያለውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 5(3) ላይ የተቀመጠውን መርህ ተፈጻሚነት ሊያስቀር እንደማይችል ገልጸዋል፡፡ የሕገ መንግሥቱን ተፈጻሚነት በሚያስቀር መልኩ አጣሪ ጉባዔው የሰጠው ትርጉምና ትርጉሙን መነሻ በማድረግ የተሰጠውን ሥልጣን በማለፍ፣ በፍርድ ቤት ሥልጣን ውስጥ በመግባት አቤቱታ አቅራቢዎቹ በአዲሱ አዋጅ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ የሚያስችል ውሳኔ መስጠት፣ ሕገ መንግሥቱ የሰጣቸውን መብት የሚጥስ መሆኑን በመግለጽ ውሳኔው አግባብነት የሌለው እንዲባልና እንዲታረም ጠይቀዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...