Monday, June 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሜታ ቢራ ፋብሪካ ከሁለት ዓመት በኋላ ሙሉ ለሙሉ የአገር ውስጥ ግብዓት እንደሚጠቀም ገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሦስት ዓመት በፊት በእንግሊዙ ዲያጆ ኩባንያ ከመንግሥት የተገዛው ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ፣ በአሁኑ ወቅት ከ6,000 በላይ ገበሬዎች የሚቀርብለትን ስምንት ሺሕ ቶን የቢራ ገብስ እየተጠቀመ ለጠመቃ ያውላል፡፡ ሆኖም በአሁኑ ወቅት ከገበሬዎች በቅድመ ብድር እያገኘ ያለውን የቢራ ገብስ ሙሉ ለሙሉ ከአገር ውስጥ አምራቾች ለመግዛት ማቀዱን ይፋ አድርጓል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በአርሲ፣ በምዕራብ አርሲ፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ውስጥ ከሚገኙ 6,113 ገበሬዎች ጋር ባደረገው ውል መሠረት ከወለድ ነፃ የ12 ሚሊዮን ብር የግብዓት ብድር በመስጠት ስምንት ሺሕ ቶን ገብስ ሊቀርብለት መቻሉን የገለጹት የኩባንያው የኮርፖሬት ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ በአካል አባተ ናቸው፡፡ አቶ በአካል እንዳስታወቁት፣ ሜታ አቦ ቢራ ‹‹የአገር ውስጥ ግብዓት ለዕድገት›› በማለት መተግበር በጀመረው ፕሮግራም መሠረት፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ለገበሬዎች የምርት ግብዓት አቅርቦት እንዲውል 90 ሚሊዮን ብር ወጪ ያደረገ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 12 ሚሊዮን ብር ለአነስተኛ ገበሬዎች ብድር የዋለ ነው፡፡

ሜታ አቦ ከሦስት ዓመት በፊት ከደቡብ ምዕራብ ሸዋ 800 ገበሬዎች ምርት መረከብ ሲጀምር 150 ቶን ብቻ ማግኘት እንደቻለ የኩባንያው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ሥራ በጀመረ በሁለተኛው ዓመት የምርቱም የገበሬዎቹም ቁጥር ጨምሯል፡፡ ከአንድ ሺሕ ገበሬዎች 1,250 ቶን ምርት ተረክቧል፡፡ በጠቅላላው አራት ሺሕ መሬት በቢራ ገብስ ምርት እየተፈሸነ ለፋብሪካው እየቀረበለት ይገኛል፡፡ ኩባንያው ከሁለት ዓመት በኋላ የተመሠረተበትን 50ኛ ዓመት በማስመልከት ገብስን ጨምሮ ለቢራ የሚያስፈልጉትን ግብዓቶች ሙሉ በሙሉ ከአገር ውስጥ ለመግዛት ሲያቅድ 20 ሺሕ ገበሬዎችን የመሳተፍ ዕቅድ እንደያዘም ገልጿል፡፡

በኦሮሚያ ክልል የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ቅርጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበበ ድሪባ እንዳስታወቁት፣ ገበሬዎች ከገበያ ዋጋ ይልቅ ጭማሪ በማድረግ ለገበሬዎች ክፍያ እየፈጸመ ይገኛል፡፡ በገበሬውና በኩባንያው መካከል ለአንድ የምርት ዘመን የሚቆይ የምርት አቅርቦት ስምምነት እንደሚፈጸም ያብራሩት አቶ አበበ፣ አሥር የገበያ መር የእርሻ ክላስተሮች በኦሮሚያ የተፈጠሩ መሆኑንና አርሲና ምዕራብ አርሲ በተለይ በቢራ ገብስ ላይ ከፍተኛ ሥራ እየሠሩ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡ በጠቅላላው 23 ሺሕ ገበሬዎች በቢራ ገብስ ምርት ላይ ማተኮራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ከሁለት እስከ ሦስት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ከውጭ የሚገባውን የገብስ ቢራም ሆነ ብቅል በአገር ውስጥ ለመተካት በአሮሚያ ክልል መታወቀዱን አቶ አበበ አስታውቀዋል፡፡

ሜታ ቢራ ጥሩ ምርት አምርተዋል ላላቸው ገበሬዎች ማክሰኞ፣ ጳጉሜን 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ዕውቅና በሰጠበት ሥነ ሥርዓት ወቅት፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር መብራህቱ መለስ እንደገለጹት፣ በአገሪቱ የቢራ ገብስ ፍላጎት ከ80 እስከ 100 ሺሕ ቶን በዓመት ቢሆንም፣ በአገሪቱ እየተመረተ ያለው ግን 38 ሺሕ ቶን መሆኑና በብዛት ከውጭ የሚገባ ምርት መቀነስ በአገር ውስጥ መተካት አልተቻለም፡፡ ሆኖም መንግሥት ለምግብ፣ ለመጠጥና ለመድኃኒት ዘርፍ ኢንስቲትዩት ማቋቋሙን፣ በዚህም በግብርናና በኢንዱስትሪ ዘርፎች መካከል ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል የኢንዱስትሪ ፓርክን ለመገንባት መንግሥት 2.5 ቢሊዮን ዶላር የመደበለትን ፕሮጀክት ለመተግበር መዘጋጀቱንም ጠቅሰዋል፡፡

ከሜታ ቢራ ባሻገር ከገበሬዎች ገብስ በመግዛት ከሚጠቀሱት የውጭ ኩባንያዎች መካከል በደሌና ሐረር ቢራ ፋብሪካዎችን የገዛው ሃይኒከንም ተጠቃሽ ነው፡፡ ሃይኒከን መቶ ሺሕ ገበሬዎች ይሳተፉበታል በተባለው አቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ 20 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የገብስ ቢራ ከገበሬዎች ለመግዛት ስምምነት ማድረጉ አይዘነጋም፡፡

ከሦስት ዓመት በፊት በመንግሥት ይዞታ ሥር የነበረውን ሜታ አቦ ቢራ በ225 ሚሊዮን ዶላር መግዛቱ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ የሜታ ቢራ ዓመታዊ የማምረት አቅም 450 ሺሕ ሔክቶ ሊትር ነበር፡፡ አምና የኩባንያው ጠቅላላ የማምረት አቅም አንድ ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር ሊደርስ መቻሉን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በ1950ዎቹ መጨረሻ በ50 ሺሕ ሔክቶ ሊትር ቢራ የመጥመቅ አቅም የተመሠረተው ሜታ አቦ ቢራ፣ በደርግ መንግሥት እስከተወረሰበት ጊዜ ድረስ ሜስ አልፍሬድ ዮርገን ሰን የተባለ የውጭ አማካሪ ኩባንያ በመቅጠር ለሁለት ዓመታት ያህል የቢራ ጠመቃ ጥራቱን ለማሻሻል ሲሠራ መቆየቱንም የሚገልጹ መረጃዎች ይጠቀሳሉ፡፡

በአንፃሩ ሜታ አቦን የገዛው ዲያጆ ኩባንያ፣ የአልኮል፣ የወይንና የቢራ መጠጦችን በማምረት በዓለም የመጠጥ ኢንዱስትሪ ስሙ የሚጠቀስ ኩባንያ ነው፡፡ ጆኒ ዎከር፣ ክራውን ሮያል፣ ጄብ፣ ቡኬነንስ፣ ዊንድሶርና ቡሽሚልስ ውስኪ፣ እስሚርኖፍ፣ ሰሮክ፣ ኬቴል ዋን ቮድካ፣ ቤይሊስ፣ ካፒቴን ሞርጋን፣ ታንክሬይ ከሚባሉት ምርቶች በተጨማሪ ሜታ ቢራና ጊነስ ከኢትዮጵያ የተካተቱ ናቸው፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪም ማልታ የተሰኘውን ከአልኮል ነፃ መጠጥ በማምረትም ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች