Tuesday, March 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኖርዌጂያዊው የሒልተን ሆቴል ዋና ሥራ አስኪያጅ ታስረው በዋስ ተፈቱ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኖርዌጂያዊው የሒልተን ሆቴል ዋና ሥራ አስኪያጅ ነሐሴ 28 ቀን 2007 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ በቂርቆስ ፖሊስ መምርያ ታስረው ከቆዩ ከሰዓታት በኋላ ቃላቸውን ሰጥተው በዋስ ተለቀቁ፡፡

ሚስተር ሀኮን ጋርደር ላርሰን በሆቴሉ በሥራ ላይ እያሉ የፍርድ ቤት የእስር ትዕዛዝ በያዙ ፖሊሶች የተወሰዱት፣ ላለፉት 15 ዓመታት ከሆቴሉ ጋር ይሠራ ከነበረ ኢትዮ ናሽናል ትራቭል ኤንድ ኦርግ (ኢንቶ) ድርጅት ጋር በተፈጠረ አለመግባባት መሆኑም ታውቋል፡፡

ኢንቶ ከሆቴሉ ጋር በተለምዶ የሻትል ሥራ (በሆቴሉ ውስጥ የሚደረገውን ማንኛውንም የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት) ለመሥራት ውል ገብቶ በየዓመቱ ውሉን እያደሰ ለ15 ዓመታት ቆይቷል፡፡ ነገር ግን በጥቅምት ወር 2007 ዓ.ም. ባደሰውና እስከ ታኅሳስ ወር 2008 ዓ.ም. ድረስ በሚቆየው ውል ላይ፣ ከክፍያ ውጪ ለአራት ከፍተኛ የሥራ አመራሮች ዲፓርትመንት (ቶፕ ማኔጅመንትስ) አገልግሎቱን እንዲሰጥ በሆቴሉ ኃላፊዎች መገደዱን፣ የድርጅቱ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አሜሪካዊው ባለሀብት አቶ ከበደ ባሌማ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ተገደው አገልግሎቱን ለመስጠት ለምን እንደፈረሙ ሲጠየቁ፣ ‹‹ላለፉት 15 ዓመታት ስንሠራ በርካታ ደንበኞችን ከማፍራታችንም በተጨማሪ፣ በተጓዳኝ በርካታ ሥራዎችን የሠራንና እየሠራንም ስለሆነ ያንን ዕድል ላለማጣት እንጂ አግባብነቱን አምነንበት አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

ሆቴሉ አስገድዶ ተጨማሪ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረጉን እንደ መብት ወስዶ ሌላ ተጨማሪ ግዴታ ውስጥ እንዲገቡ እያስገደዳቸው መሆኑን የገለጹት አቶ ከበደ፣ ሌሎች በሆቴሉ ውስጥ ካሉ የተለያዩ ድርጅቶች በተለየ ሁኔታ የእነሱ ድርጅት ከሚያገኘው ገቢ ላይ 50 በመቶውን ለሆቴሉ እንዲያስገቡ እየተገደዱ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ሆቴሉ በድጋሚ ወደማይፈልጉትና ከሕግ ውጪ ወደሆነ አሠራር እንዲገቡ ሲያስገድዳቸው ባለመስማማታቸው፣ ወራት የቀሩትን የኮንትራት ውል በመሰረዝ ከአዲካ አስጐብኚና የጉዞ ወኪል ጋር አዲስ ውል መዋዋሉንና ኢንቶ ወደ ሕግ በመሄድ ማሳገዱን አቶ ከበደ ገልጸዋል፡፡

ከ23 በላይ ዘመናዊ ተሽከርካሪዎችን በማቅረብና አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ከበደ፣ 32 ሠራተኞች ያሉትን ድርጅት በማስገደድ ከሥራ ውጪ ለማድረግ እንቅስቃሴው እየጠነከረ በመምጣቱ፣ ለፖሊስ ክስ በማቅረባቸው ሚስተር ላርሰን በሕግ ሊጠየቁ መቻላቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ሚስተር ላርሰን ቂርቆስ ፖሊስ መምርያ ቀርበው ቃላቸው ከሰጡ በኋላ፣ የሒልተን ሆቴል የሰው ሀብት አስተዳደር ኃላፊ ወ/ሮ አዳኑ ታፈሰ ተውሰዋቸው ከእስር መፈታታቸው ተገልጿል፡፡ ሪፖርተር ሚስተር ላርሰን ስለታሰሩበት ዝርዝር ምክንያትና በዋስ ስለተፈቱበት ሁኔታ ከሆቴሉ ማብራሪያ ለማግኘት ያደገው ጥረት አልተሳካም፡፡

ሚስተር ላርሰንን በጉዳዩ ላይ ተጠይቀው፣ ‹‹በሕግ የተያዘ ጉዳይ በመሆኑ ምንም ዓይነት ምላሽ አልሰጥም፤›› ብለዋል፡፡

ኢንቶ በሰኔ ወር 2007 ዓ.ም. ከሆቴሉ የኦፕሬሽን ዳይሬክተር ሚስተር ሻንካር ፓራማሲቫም ጋር በተመሳሳይ ጉዳይ አለመግባባት ላይ ደርሶ፣ ዳይሬክተሩ አንድ ቀን ታስረው መፈታታቸውን፣ ክስ ተመሥርቶባቸው ጉዳዩ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቀጠሮ ላይ መሆኑንና ከአገር እንዳይወጡም መታገዳቸውንም አቶ ከበደ ገልጸዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች