Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየንፋስ ስልክ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ዲንና የግዢ ዕቅድ ኃላፊ በሙስና ተጠርጥረው ተከሰሱ

የንፋስ ስልክ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ዲንና የግዢ ዕቅድ ኃላፊ በሙስና ተጠርጥረው ተከሰሱ

ቀን:

– መንግሥትን ከ1.2 ሚሊዮን ብር በላይ ማሳጣታቸው ተጠቁሟል

የንፋስ ስልክ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ኮሌጅ ዲንና የግዢ ዕቅድ ዝግጅት አፈጻጸም ደጋፊ የሥራ ሒደት መሪን ጨምሮ፣ ስምንት ሰዎች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ነሐሴ 28 ቀን 2007 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የኮሌጁ ዲን አቶ ጋይሞ ተሻለ፣ የግዢ ዕቅድና አፈጻጸም የሥራ ሒደት መሪ አቶ ሙሉጌታ አርዓያ፣ የጠቅላላ አገልግሎት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ደስታ፣ የጥራት ኦዲት ብዙነሽ አወቀ፣ የተሽከርካሪ ሥምሪት ኦፊሰር አቶ ኤፍሬም ከተማ፣ የአሠልጣኞች ሥልጠና ባለሙያ አቶ ሽመልስ ድልነሴ፣ ሲኒየር ግዢ ኦፊሰር አቶ ሰለሞን አሻግሬና በግል ሥራ የተሰማሩት አቶ አንተነህ ታረቀኝ ናቸው፡፡ ክሱን የመሠረተው የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሲሆን፣ የሚመረምረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ነው፡፡

ከሦስተኛ እስከ ስድስተኛ ያሉት ተከሳሾች የጨረታ ኮሚቴ አባል ሆነው ሲሠሩ፣ ‘ራውንድ ባር ዋየር ማግኔቲክ ሴንሰር’ ለመግዛት የወጣን ጨረታ፣ አቶ አንተነህን ለመጥቀም በማሰብ ብቸኛ ተጫራች መሆኑን ሲያውቁ ሰርዘው ድጋሚ ጨረታ ማውጣት ሲገባቸው አሸናፊ በማድረግ፣ ዲኑና የግዢ ኃላፊው በማፅደቃቸው መንግሥት 61,875 ብር እንዲያጣ ስላደረጉት በፈጸሙት የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን መምራት የሙስና ወንጀል መከሰሳቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡

ዲኑና ከፍተኛ የግዢ ኦፊሰሩ ደግሞ ኮሌጁ ባወጣው የተለያዩ ዕቃዎች ግዢ፣ አስተዳደሩ ያወጣውን የግዢ መመርያ በመተላለፍ ኮሚቴው ‹‹የዕቃዎቹ መጫረቻ ዋጋ የተጋነነ በመሆኑ አስቀድሞ ጥናት ይደረግባቸው›› የሚል ሐሳብ አቅርቦላቸው እያለ፣ ለሁለተኛ ተከሳሽ ‹‹ጥናት ተካሂዶባቸው ግዢው ይፈጸም›› በማለት ኤቲ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከሚባለው ድርጅት ግዢው እንዲፈጸም ማድረጋቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ በመሆኑም ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣት 1,262,354 ብር ግዢ ተፈጽሟል፡፡ በአጠቃላይ ሁሉም ተከሳሾች በፈጸሙት የአታላይነትና የመንግሥት ሥራን በማያመች አኳኋን መምራት የሙስና ወንጀል መከሰሳቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

ፍርድ ቤቱ ለተከሳሾቹ ክሱን ካነበበላቸው በኋላ የዋስትና መብታቸውን ጠብቆላቸዋል፡፡ በመሆኑም አንደኛና ሰባተኛ ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በአንድ መቶ ሺሕ ብር፣ ሁለተኛና ሦስተኛ ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በ20,000 ብር፣ አምስተኛና ስምንተኛ ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በ10,000 ብር ዋስ እንዲለቀቁ በማዘዝ መቃወሚያ ካላቸው ለመስማት ለኅዳር 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...