Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹መንግሥት ለመማር ዝግጁ ቢሆንም እስካሁን ግን ተገቢውን ትምህርት አልተማረም››

ፕሮፌሰር ኬኒቺ ኦህኖ፣ ጃፓናዊው የመንግሥት አማካሪ

እሳቸውም ባለቤታቸውም ጃፓናውያን ፕሮፌሰሮች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናትን ማማከር የጀመሩት ከስምንት ዓመት በፊት ነበር፡፡ ፕሮፌሰር ኬኒቺ ኦህኖ የኢኮኖሚክስ ምሁር ሲሆኑ፣ በዓመት ሁለት ጊዜ በየስድስት ወሩ በጃፓን ባለሙያዎችና በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት መካከል በሚደረገው የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ብሔራዊ ምክክር ላይ በመገኘት ሐሳቦቻቸውን ማካፈል ከጀመሩ ሰንብተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ከሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊና ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላቸው፡፡ ከአሥር ጊዜ በላይ ከአቶ ኃይለ ማርያም ጋር ተገናኝተው የተነጋገሩት ፕሮፌሰር ኦህኖ፣ መንግሥት በዕድትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ያሰፈራቸው ግቦች የተለጠጡ ብቻ ሳይሆኑ ምናባዊና የማይጨበጡ እንሆኑ በመግለጽ ሲተቹ ይታወቃሉ፡፡ የዛሬ አንድ ዓመት ገደማ ከሪፖርተር ጋር በተለይ ባደረጉት ቆይታ የመጀመሪያው ዕቅድ በብዙ ጎኑ ተለጣጭና ተስፈኛ ብቻም ሳይሆን፣ እሳቸውና አጋሮቻቸው ያቀርቧቸው የነበሩ ሙያዊ አስተያየቶች ቸል የተባሉበት እንደነበር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ በበርካታ ጎኖቹ የሚተቸው ያለፈው የአምስት ዓመት የኢኮኖሚ ዕቅድ፣ አገሪቱ ስትተገብራቸው የቆዩትን የማኔጅመንት ሥርዓቶች አለማካተቱን ለሪፖርተር የገለጹት፣ ሰሞኑን በተካሄደው የአፍሪካ ጃፓን የቢዝነስና የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ በተገኙበት ወቅት ነበር፡፡ ከመንግሥት ቁንጮ ባለሥልጣናት ጋር በግልጽ እንደሚወያዩ የሚናገሩት ፕሮፌሰር ኦህኖ፣ በአዲሱ የአምስት ዓመት ዕቅድና ባለፈው መካከል ስላሉ ክፍተቶች፣ መንግሥት አምራች ኢንዱስትሪውን መሠረት ለማስያዝ ማድረግ መከተል ሰለሚገባው አካሄድ፣ የብድር ዕዳን ለማቃለል ብቻም ሳይሆን ያልታሰቡ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች እንዳይከሰቱ የአገሪቱ የኢኮኖሚ በግድ ማደግ እንደሚጠበቅበት፣ የዕድገቱ መቀዛቀዝ መዘዝ እንዳለውና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ፕሮፌሰር ኦህኖ ከብርሃኑ ፈቃደ ጋር ባደረጉት ቆይታ አብራርተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ቀደም ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ ስለዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተነጋግረን ነበር፡፡ አብዛኞቹ የዕቅዱ ግቦች አለመሳካታቸው ይታወቃል፡፡ በአጠቃላይ በዕቅዱ ላይ የእርስዎ ዕይታ ምንድነው?

ፕሮፌሰር ኦህኖ፡- የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በሚዘጋጅበት ወቅት አንዳንድ ተግባራዊ ሊደረጉ የታቀዱ ቁጥሮች፣ በተለይ ለአምራች ኢንዱስትሪው የተቀመጡት ከፍተኛ መሆናቸውን ተናግረናል፡፡ ሆኖም የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሰዎች በርካታ ኢንቨስትሮች እየመጡ በመሆናቸው የታቀዱት ግቦች ምክያታዊ መሆናቸውን ገልጸው ነበር፡፡ እንደምታውቀው ኢንቨስተሮች እንዲሁ ኢንቨስት አያደርጉም፡፡ እንደማስበው እጅግ ከፍተኛ የነበሩት አኃዞች ምናልባትም ሲበዛ የተለጠጡ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ያስገረመኝም ነገር አለ፡፡ በርካታ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በተለይ በአምራች ኢንዱስትሪው በኩል መጥቷል፡፡ ለዚህ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ሌሎችም የውጭ ኢንቨስትመንት እንዲመጣ የሠሩ በሙሉ ሊኮሩ ይገባቸዋል፡፡ ይህም ሆኖ ግቦቹ በጣም ከፍተኛ በመሆናቸው ከታቀዱት ውስጥ ያልተሳኩ አሉ፡፡ ይህ በመሆኑ ግን ብዙ ልትጨነቁበት አይገባም እላለሁ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ትክክለኛው አቅጣጫ ላይ ስለምትገኙ ነው፡፡ ብዙ የውጭ ኢንቨስትመንት እየሳባችሁ ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ዞኖችን እያሻሻላችሁና እያበራከታችሁ ነው፡፡ በሎጂስቲክስ፣ በጉምሩክ፣ በታክስና በሒሳብ አሠራር በኩል ያሉ ሳንካዎችን ለመቅረፍ እየሞከራችሁ ነው፡፡ እንደማስበው መንግሥት ስለችግሮቹ በደንብ ይገነዘባል፡፡ ስለዚህም ባልተሳኩት ግቦች ሳቢያ ብዙም ጨከን ያለ አስተያየት መስጠት አልሻም፡፡ ከመነሻው ጀምሮም እነዚህን ግቦች ማሳካት በጣም ከባድ እንደነበር እናውቃለን፡፡ ሳይሳኩላቸውም ቀርተዋል፡፡ ይህ መሆኑ ጥሩ ነው ማለቴ ግን አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዝግጅት ሒደት ላይ ተሳትፎ እንደነበረዎት አውቃለሁ፡፡ ከዕቅዱ ጋር ያለዎት የቅርብ ትውውቅ እንዴት ይገለጻል?

ፕሮፌሰር ኦህኖ፡- አዎን፡፡ በመጀመሪያው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ያልተሳኩ ነገር ግን አስፈላጊ ግብዓቶች እንደሆኑ ያመንባቸውን ነጥቦች በማመላከት ምክራችንን ሰጥተናል፡፡ እኛ እንዳልነው ጠቅላይ ሚኒስትሩም እንደተስማሙት የቀላል አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ በዕቅዱ መሠረት አልተሳካም፡፡ በግቡ መሠረት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተምሳሌትና ቀዳሚ የቀላል አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ባለቤት እንድትሆን ይታሰብ ነበር፡፡ ይህ ጥሩ ግብ በመሆኑም በ2017 ዓ.ም. አገሪቱ በአፍሪካ መሪ የቀላል ኢንዱስትሪ ባለቤት ትሆናለች ተብሏል፡፡ ይህ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ እንዴት እንደተቀመጠ አላውቅም፡፡ ሌላው ለመንግሥት ያቀረብንለት ሐሳብ በምርታማነትና በተወዳዳሪነት ላይ ያተኮሩ በርካታ ነጥቦች በዕቅዱ እንዲካተቱ ነው፡፡ ያለፈው ዕቅድ ስለማኔጅመንት ሥርዓቶች ምንም የሚጠቅሰው ነገር የለም፡፡ ምንም እንኳ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በዕቅዱ ዘመን ሲተገበሩ ቢቆዩም ስለቤንች ማርኪንግ፣ ወይም ስለመሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ ወይም፣ ስለካይዘን የሚጠቅሰው አንድም ነገር የለውም ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን እነዚህ ሥርዓቶች በዕቅዱ ለምን እንዳልተካተቱ ጠይቄያቸው ነበር፡፡ እርግጥ በእያንዳንዱ የዕቅዱ ሰነድ ዝርዝር ጉዳይ ላይ አይገቡም ነበር፡፡ በሁለተኛው ዕቅድ ላይ እነ ካይዘን፣ እነ ምርታማነትና እነ ተወዳዳሪነት እንደሚካተቱ አስባለሁ፡፡ በመጨረሻው የረቂቅ ዕቅዱ ላይ እነዚህ ነገሮች መካተት ብቻ ሳይሆን፣ የመጪው አምስትና አሥር ዓመት ዕቅዶች ሆነው እንደሚቀመጡ ተስፋ አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- በበፊቱ ቆይታችን አጉልተው እንደገለጹት ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ነገሮች መስመር መያዝ ይጀምራሉ፡፡ ካለፈው ዕቅድ አኳያ በተለይ የመንግሥት መዋቅር፣ የአስተዳደር ጉዳዮች፣ ወይም ለኢንዱስትሪው የሚመጥኑ የሰው ኃይል ክህሎቶች ታሳቢ ሲደረጉ ይህ ሊሆን የሚችል ነገር ነው ይላሉ?

ፕሮፌሰር ኦህኖ፡- የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ገና በጅምር ላይ እንደሚገኝ መናገር እችላለሁ፡፡ የአገሪቱን የኢንዱስትሪ ፖሊሲ በከፍተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙት እንደ ሲንጋፖር ካሉት አገሮች ደረጃ አኳያ በማየት አወዳድሬዋለሁ፡፡ ለሲንጋፖር ትልቁን ነጥብ ሰጥቻለሁ፡፡ ‹‹A+›› ይገባቸዋል፡፡ ታይዋን በኢንዱስትሪ ፖሊሲ ረገድ በጣም ጥሩ ነች፡፡ ኮሪያና ጃፓንም ‹‹A›› ይገባቸዋል፡፡ ለማሌዢያ፣ ለታይላንድና ለኢትዮጵያ ‹‹B›› እሰጣቸዋለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ገና እየጀመረ ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ዞኖችን ለማቋቋም የሚደረገው ጥረት ትክክለኛ አቅጣጫ ነው፡፡ ሆኖም ዝርዝር ነገሮች በደንብ መጥራት አለባቸው፡፡ የጨርቃ ጨርቅና የቆዳ ልማት እንዲሁም የካይዘን ኢንስቲትዩቶች አሁን መቋቋማቸው ለወደፊቱ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ነገር ግን የሚጎድሉ ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛው የአገሪቱ የቢዝነስ አሠራር ሁኔታ ነው፡፡ በጣም መጥፎ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የጉምሩክ አሠራርና የታክስ ጉዳዮች፣ እንዲሁም የሒሳብ አሠራር ሥልቱ ከዓለም አቀፍ ስታንዳርድ ጋር የተጣጣመ አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ለመንግሥት ስለዚህ ነገር ገልጫለሁ፡፡ እነሱም ያውቁታል፡፡ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንንና የሎጂስቲክስ ሥርዓቱን ማሻሻል ይፈልጋሉ፡፡ ጥሩ ጥሩ ዓላማዎች አሏቸው፡፡ ሆኖም ይህን ሁሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊያከናውኑት ይችላሉ ወይ ብለህ ከጠየቅህ ግን ሌላ ነገር ነው፡፡

በኢትዮጵያ እንደ ጉድለት የሚታየው ሌላው ችግር የአገር ውስጥ ኢንተርፕራይዞች ወይም የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ማሻሻያ ፖሊሲ አለመኖር ነው፡፡ ለቆዳና ለጨርቃ ጨርቅ ኢንስቲትዩቶች ተመሥርተዋል፡፡ ትክክል ነው፡፡ ሆኖም ለሁሉም አነስተኛና ጥቃቅን ዘርፍ ምንም ነገር የለም፡፡ ማሌዢያ፣ ታይዋን ወይም ጃፓን ብትሄድ ግን ስለጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ፖሊሲ አስፈላጊነት የምናገረው ለምን እንደሆነ ልትገነዘብ ትችላለህ፡፡ በአገሪቱ በጥቃቅንና አስተኛ መስክ በርካታ ሊሠሩ የሚችሉ ነገሮች ቢኖሩም፣ በዚህ ረገድ ለዘርፉ ተስማሚ የሆነ ፖሊሲ አውጥታ ለመተግበር አገሪቱ ዝግጁ አይደለችም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ማዕቀፉና ትርጓሜውን ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ እንዴት ነው ጥቃቅንና አስተኛ ዘርፎች የሚቃኙትና የሚደገፉት የሚለው የፖሊሲ ማዕቀፍ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ማዕቀፍ ምን እንደሚመስል ለእኔ ግልጽ አይደለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በእነዚህ ተቋማት ውስጥ የሚገኘውን የሰው ኃይል ብቃት ማሻሻል ያስፈልጋል፡፡ ያንን እንዴት ማድረግ እንደሚቻል የሚጠቁሙ በርካታ መንገዶች አሉ፡፡ ማበረታቻ፣ ድጎማና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና በመስጠት የሰው ኃይሉን ማሻሻል ይቻላል፡፡ የቴክኒክና የሙያ ትምህርትና ሥልጠና የሚሰጡ ትምህርት ቤቶች እዚህ መኖራቸው ጥሩ ነው፡፡

ሆኖም ኢትዮጵያ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትን ፋይናንስ በማድረግ ረገድ ጥሩ ምሳሌ የምትሆንም አይመስለኝም፡፡ ማሌዢያ ብትሄድ ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ሲባል በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ የተቋቋሙ ባንኮች አሉ፡፡ ይህ ኢትዮጵያ ውስጥ አልተደረገም፡፡ ሌላው የተረሳው ነጥብ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማቱን ከውጭ ገበያ ወይም ከውጭ ኢንቨስተሮች ጋር ማስተሳሰር ነው፡፡ እነዚህን ተቋማት ማዛመድ፣ ማገናኘት፣ እንዲሁም ከኢንዱስትሪ ክላስተር ጋር እንዲጣጣሙ ማድረግ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ፖሊሲዎች ውስጥ የሚካተቱ ሲሆን፣ መንግሥት አንዳንዶቹን ገና ለመጀመር እየሞከረ ነው፡፡ ስለዚህም ነው ገና በጀማሪነቱ ላይ የሚገኝ ነው የምለው፡፡ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ፖሊሲ ወይም የአገር ውስጥ ኢንተርፕራይዞች ማሻሻያ ፖሊሲ ለእኔ በጣም ወሳኙ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ አካል ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ዞን መገንባትና የውጭ ኢንቨስተሮችን መጋበዝ ጠቃሚ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን የአገር ውስጡን የሰው ኃይልና ድርጅቶችን ብቃት ካላሻሻልክ የውጭ ኢንቨስመንትንም ሆነ የኢንዱስትሪ ዞኖችን ጠቀሜታ ሙሉ በሙሉ ለማጣጣም በጣም አስቸጋሪ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት የኢንዱስትሪ ዞኖችን እያስፋፋ ነው ቢባልም፣ እንዲህ ላሉት ፕሮጀክቶች ፋይናንስ ማግኘቱም ከባድ ሆኖበታል፡፡ ይህም የመንግሥት ችግር ሆኖ ሊታይ አይችልም ይላሉ?

ፕሮፌሰር ኦህኖ፡- ፋይናንስ የምንግዜም ችግር በመሆኑ መንግሥት አስፈላጊው ፋይናንስ ባይኖረው አይፈረድበትም፡፡ መንግሥት ከግምጃ ቤቱ በዚህ ዘርፍ ላይ ኢንቨስት የማድረግ ሐሳብ ያለው ይመስለኛል፡፡ ዩሮ ቦንድ የተባለውን የውጭ የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ ያመጡት ከገንዘቡ የተወሰነውን ለኢንዱስትሪ ዞኖች ግንባታ ለማዋል ነው፡፡ የዓለም ባንክ በአዲስ አበባ ቦሌ፣ ለሚና ቅሊንጦ አካባቢ ለሚገነቡት ዞኖች ፋይናንስ አቅርቧል፡፡ የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) ቢጠየቅ ፋይናንስ ለማቅረብ አወንታዊ ነው፡፡ ልክ ቻይኖቹ እንደገነቡት ኢስት ኢንዱስትሪ ዞን፣ ጆርጅ ሹ የሚባለው የታይዋን ኩባንያ ሊገነባ እንዳሰበው ያለ የኢንዱስትሪ ዞን ግንባታ ለግል ኩባንያዎችም መሰጠት አለበት፡፡ ፋይናንሱ ከሌላችሁ ምንም ማለት አይደለም፡፡ ሆኖም ሌሎች ምንጮችን ማፈላለግ ይኖርባችኋል፡፡ በእሽሙር ወይም በጋራ ማልማት፣ አንዳንዴም ኢፊሴላዊ የልማት ትብብር የፋይናንስ ምንጮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አንዳንዴ ዝም ብሎ የኢንዱስትሪ ዞኖችን በመገንባት ብቻ የኢንቨስተሮችን ፍላጎት ማሟላት አይቻልም፡፡ ከግንባታው ስንነሳ የተገነባው የማምረቻ ሼድ ወይ በጣም ረጅም አልያም በጣም ጠባብ ይሆንና ኢንቨስተሮችን እንደታሰበው ላያመጣ ይችላል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ የገንዘብ ብክነት ነው፡፡ የአንድ መስኮት አገልግሎትም በጣም በከፍተኛ የጥራት ደረጃ መሰጠት ይኖርበታል፡፡ የኢንቨስተሩ ፍላጎት ምን እንደሆነ ጠንቅቆ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በጠቅላላው መንግሥት ለመማር ዝግጁ መሆኑን መናገር ይቻላል፡፡ ሆኖም እስካሁን ግን ተገቢውን ትምህርት አልተማረም፡፡ እኛ በጥቂቱ ልንረዳቸው እንችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ብዙ ርቀት መጓዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አሁን ያለው አቅጣጫና ማዕቀፍ መልካም ሊባል የሚችል ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ዞኖችን መገንባት ችለዋል፡፡ ይህንንም እንደ መነሻ ተጠቅመውበታል፡፡ መንግሥት የጉምሩክ፣ የሎጂስቲክስና የሰው ኃይሉ ላይ ማሻሻያዎችን በማድረግ የኢንዱስትሪ ዞኖችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚሠራ ይናገራል፡፡ ይህ ብቻ ባይሆንም ትክክለኛ ስትራቴጂ ነው ማለት እችላለሁ፡፡ እንዲህ ያለውን አካሄድ እደግፋለሁ፡፡   

ሪፖርተር፡- በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ መንግሥት እንዲያተኩርባቸው የሚገቡ በርካታ ነጥቦች አሉ፡፡ ብድር የመሸከም አቅም መታየት ካለባቸው ውስጥ አንዱ ነው ብለው ያስባሉ?

ፕሮፌሰር ኦህኖ፡- ይህንን ለማድረግ የአገሪቱን የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታና ስታትስቲካዊ አኃዞችን ማየት ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- እርግጥ ነው፡፡ ሆኖም የዓለም ባንክ በቅርቡ ይፋ ባደረው ሪፖርት መሠረት የአገሪቱ የብድር ዕዳ መጠን ከኢኮኖሚው (ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ) የ40 በመቶ ድርሻ ይዟል፡፡ በጥቂት ዓመታት ውስጥም ይህ መጠን 60 በመቶ በላይ እንደሚሆን ይተነብያል፡፡

ፕሮፌሰር ኦህኖ፡- የአገሪቱን ዕዳ የመሸከም አቅም ትንታኔ አልሠራሁበትም፡፡ ይህንን ለዓለም የገንዘብ ድርጅትና ለዓለም ባንክ ተንታኞች እተወዋለሁ፡፡ ነገር ግን ዕዳ የመሸከም አቅም በስኬታማ ኢንቨስትመንቶች ይወሰናል፡፡ ኢንቨስትመንቱ ብክነት የሞላበት ከሆነ ዕዳው ዕዳ ብቻ ይሆናል፡፡ ኢንቨስት የሚደረገው ትክክኛ በሆኑ እንደ ሰው ኃይል ባሉት፣ ኢንዱስትሪ ዞን ግንባታ ወይም በመሠረተ ልማት ሥራዎች ላይ ከሆነ ግን መንግሥት በቀጥታ ጥቅም ባያገኝበት እንኳ የግሉ ዘርፍ ከፍተኛ ተጠቃሚ ይሆንበታል፡፡ የውጭ ኢንቨስተሮችም ወደ ኢትዮጵያ አንዲመጡ ያስችላል፡፡ አገሪቱም በዓለም ገበያ ይበልጥ ተወዳዳሪ እንድትሆን ስለሚረዳት ዕዳዋን ለመክፈል ትችላለች፡፡ ይህ ከሆነ ስለዕዳው ብዙም መጨነቅ አያስፈልግም ማለት ነው፡፡ ኢኮኖሚው ማደጉን እስከቀጠለ ድረስ የብድር ዕዳው ከዕድገቱ ጋር ሲነፃፀር የዕዳው መጠን ጥቂት ሆኖ ሊገኝ ይችላል፡፡ ኢኮኖሚው ማደግ ሲያቆም የምትበደረውን ገንዘብ ካላቆምክ ግን ችግር ውስጥ ትገባለህ፡፡ በዚህ ወቅት ዕዳው ከኢኮኖሚው አኳያ አርባ በመቶ ደርሷል መባሉ እኔን ብዙም አያስጨንቀኝም፡፡ እኔ ይበልጥ የምሰጋው የኢኮኖሚ ዕድገቱ ቀጣይነት ላይ ነው፡፡ የአሥር በመቶ ዓመታዊ ዕድገቱ ከቀጠለ በጣም ጥሩ ነገር ነው፡፡ ይህ ግን የሚሆን አይመስለኝም፡፡ ዕድገቱ ሊቀዛቀዝና ሊቀንስ ይችላል ብዬ አስባሁ፡፡ መካከለኛ ገቢ ያለው አገር ብቻም ሳይሆን ከፍተኛው ገቢ ላይ ያለ መካከኛ ኢኮኖሚ (ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከአራት ሺሕ እስከ 12 ሺሕ ዶላር ሲሆን) መሆን እስክትችሉ ድረስ፣ የኢኮኖሚው ዕድገት አሥር በመቶ ገደማ መሆን አለበት፡፡ የኢኮኖሚው ዕድገት ከተቀዛቀዘ ግን ከብድር ዕዳው በተጨማሪ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንዲከሰቱ ዕድል ሊሰጥ ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- የብድር ዕዳውን ጉዳይ ያነሳሁበት ምክንያት የኢኮኖሚው ዕድገት ሊቀዛቀዝ ከሚችሉባቸው ምክንያቶች መካከል የመንግሥት ኢንቨስትመንት ሊቀንስ እንደሚችል ከመታሰቡ ጋር  በተገናኘ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ተፅዕኖ ውስጥ አይከተውም ይላሉ? ከዕቅዱ ማየት እንደሚቻለው ከመቼውም ጊዜ በላይ የተለጠጠ ይመስላል፡፡ በኃይል ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ይታሰባል፡፡ ከወጪ ንግዱ ይገኛል የተባለውም የተለጠጠና ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ነው፡፡

ፕሮፌሰር ኦህኖ፡- መንግሥታት የአምስት ዓመት ዕቅዶቻቸውን ከተገቢው በላይ እንዳይለጥጡ መግታት አልችልም፡፡ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ሌሎች መንግሥታትም ግዙፍ አኃዞች  አሏቸው፡፡ በእስያ የካምቦዲያን የኢንዱስትሪ ግብ ተመልክቻለሁ፡፡ በከፍተኛ ደረጃ የተለጠጠ ተስፈኛ ነው፡፡ በካምቦዲያ የፋይናንስ ሚኒስቴር ሰዎች የተቀመጡት ግቦች ግዙፍና አኃዞቹም ትልቅ ተደርገው ሕዝቡን ማነሳሳት አለባቸው ይላሉ፡፡ ይኼ የፖለቲካና የሥነ ልቦና ዓላማን ያነገበ ነው፡፡ እንደገባኝ ከሆነ ያልተለጠጠና በተስፋ ያልተሞላ የአምስት ዓመት ዕቅድ ማግኘት አልተቻለም፡፡ ነገሮች ግን ሚዛናቸውን መጠበቅ አለባቸው፡፡ እርግጥ ነው ዕቅዶች የተለጠጡ፣ ሕዝቡንና ኢንዱስትሪዎችን የሚያነሳሱ መሆን እንዳለባቸው እስማማለሁ፡፡ በዚያው ልክ ግን ትርጉም የሚሰጡና የማክሮ ኢኮኖሚውን ሚዛን ማስጠበቅ የሚችሉ መሆን አለባቸው፡፡ ዕቅዱ የፖለቲካ ሰነድ እንደመሆኑ መጠን ሚዛኑን እንዴት ማስጠበቅ እንደሚቻል መወሰን ያለባቸው ፖሊሲ አውጪዎቹ ራሳቸው ናቸው፡፡ የአምስት ዓመት የኢኮኖሚ ዕቅዶች በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ምናባዊ እንደሆኑ እናውቃለን፡፡ ሆኖም ሌላው ቢቀር በጥቂቱም  ምክንያታዊና አሳማኝ መሆን አለባቸው፡፡ ነገር ግን ወፍ ዘራሽ አኃዞችንና እጅግ የገዘፉ የኢንቨስትመንት መግለጫዎችን ላስቆም አልችልም፡፡ እንደማስበው እውነታው ራሱ ይይዛቸዋል፡፡ ይህም ቢባል ዕቅዶችን ሲተልሙ ታሳቢ የሚያደርጓቸው ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፈው የአምስት ዓመት ዕቅድ በጥሩ ከሚነሱት መካከል የውጭ ኢንቨስትመንት መጨመር አንዱ ነው ብለዋል፡፡ በሁለተኛው ዕቅድ ውስጥ ምን ይጠብቃሉ? ቀላል አምራች ኢንዱስትሪው የሚገነባ ይመስልዎታል?

ፕሮፌሰር ኦህኖ፡- የቀላል አምራች ኢንዱስትሪው የውጭ ኢንቨስትመንት እየቀጠለና እየጨመረ ሲሄድ ማየት እፈልጋለሁ፡፡ የጨርቃ ጨርቅ ማሽነሪዎች፣ የሎጂስቲክስ ድጋፍ፣ የፍጆታ ዕቃዎች፣ የምግብ ዘይት ምርት መጨመር በጣም ይበረታታል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለው የመጠጥ ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ቀላል አይደለም፡፡ ይህ እንዴት እንደሆነ አልገባኝም፡፡ ኢትዮጵያውያን ቢራ ጠጪዎች መሆን ጀምረው እንደሆነም አልገባኝም፡፡ ነግር ግን ፍላጎቱ እስካለ ድረስ የንግድ መርህ የኢንቨስትመንቱን አስፈላጊነት ያረጋግጣል፡፡ የግሉ ዘርፍ ኢንቨስት የሚያደርገው ገንዘብ የት እንዳለና ሊገኝ እንደሚችል ሲገነዘብ ነው፡፡ በቀላል ኢንዲስትሪው ላይ የሚደረገው ግዙፍ ኢንቨስትመንት እያደገ ሲሄድ ማየት እሻለሁ፡፡ ለግንባታ ያለው ፍላጎት እንደሚቀጥል፣ በብረትና በሲሚንቶ ላይ ኢንቨስት ማድረግ እንደሚያስፈልግ፣ የሸማቹ ፍላጎትም እንደሚጨምር ይጠበቃል፡፡  ስለዚህ መካከለኛና ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያላቸውን ምርቶችና ሌሎች በርካታ ዕቃዎችንም ማምረት መጀመር ተፈጥሯዊ ክስተት ነው ማለት እንችላለን፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ ጃፓን ያሉ አገሮች በመጪው አምስት ዓመት ውስጥ ወደዚህ በመምጣት ኢንቨስት ከሚያደርጉ ያደጉ አገሮች መካከል ይሆናል ብለው ያምናሉ?

ፕሮፌሰር ኦህኖ፡- ጃፓኖች ለመምጣት ቀሰስተኞች ናቸው፡፡ የጊዜ ጉዳይ እንጂ መምጣታቸው ግን አይቀርም፡፡ ወደ ቻይና ኢንቨስት ለማድረግ ስትገባ ጃፓን የመጨረሻዋ አገር ነበረች፡፡ በቬትናም፣ በካምቦዲያ ወይም በማይናማር (በርማ) የነበረው የጃፓን ታሪክ ተመሳሳይ ነው፡፡ በእነዚህ አገሮች ውስጥ ጃፓን ኢንቨስት ለማድረግ ስትገባ ከቀዳሚዎቹ ውስጥ አልነበረችም፡፡ ሲገቡ ጊዜ ቢፈጁም ከገቡ አሥርና ሃያ ዓመት በኋላ ግን በቬትናምና በካምቦዲያ ያለው የጃፓኖች ኢንቨስትመንት ከሌሎች ይልቅ ትልቅ ነው፡፡ ሁሌም ለመግባት ይዘገያሉ እንጂ ከገቡ በኋላ ጃፓኖች በአምራችነት ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ እንዲህ ያለው ሒደት ወደፊት በአፍሪካም ሊደገም ይችላል፡፡ በአሁኑ ወቅት በጣም ጥቂት የጃፓን ኩባንያዎች ናቸው በአፍሪካ አምራች ኢንዱስትሪዎችን እየተከሉ የሚገኙት፡፡ ወደፊት ግን ግዙፍ ኢንቨስትመንታቸው እንደሚሆን የሚጠበቅ ነው፡፡ ወደ ኢትየጵያ መምጣት ከሚፈልጉ አነስተኛና ትልልቅ ከሆኑ በርካታ የጃፓን ኩባንያዎች ጋር ግንኙነት አለኝ፡፡ መምጣት ቢፈልጉም ሥጋት የሆኑባቸው ነገሮች አሉ፡፡ የውጭ ምንዛሪው ሁኔታ ያሳስባቸዋል፡፡ የማምረቻ ቁሳቁሶችን ወደዚህ ማምጣት ስለሚችሉባቸው ሁኔታዎች ሥጋት አላቸው፡፡ አገሪቱ በቂ የተጣራ ውኃ ማቅረብ ስለመቻሏም ማወቅ ይፈልጋሉ፡፡ ሁሉም ነገር መልካም መሆኑን ማረጋገጥ ይፈልጋሉ፡፡ ይህ በመሆኑም ነው ጃፓኖች እስኪመጡ ጊዜ የሚፈጀው፡፡ ከኮሪያዎችም ሆነ ከቻይናዎች እንለያለን፡፡ እነሱ ሪስክ ወስደው (አደጋ ተጋፍጠው) ስኬታማ መሆን እስከቻሉ ድረስ እንዲህ ባለው ሒደት ውስጥ አልፈው ብዙ ገንዘብ ማግኘትን ይመርጣሉ፡፡ ካልተሳካላቸውም ትተው ይሄዳሉ፡፡ እነሱ ሪስክ ወሳጆች ሲሆኑ እኛ ግን እንደነሱ አይደለንም፡፡ በበኩሌ ከአምስት እስከ 20 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ካምቦዲያና ቬትናም ላይ እንደሆነው ሁሉ፣ በኢትዮጵያም የጃፓኖች ኢንቨስትመንት እንደሚመጣ የራሴን ትንበያ አስቀምጫለሁ፡፡ ወደፊት በኢትዮጵያ ትልቅ አምራቾች የሚሆኑት ጃፓኖች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በአፍሪካ-ጃፓን ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ስምዎን በማንሳት ምሥጋና አቅርበውልዎታል፡፡

ፕሮፌሰር ኦህኖ፡- አዎ፣ ወዳጄ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- መልካም ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ሌሎች ባለሥልጣናት እርስዎ ለሚሰነዝሯቸው ሙያዊ ሐሳቦች አቀባበላቸው ምን ይመስላል?

ፕሮፌሰር ኦህኖ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ዋጋ ያለውን ዕውቀት ከማንኛውም ሰው ከመቅሰም ወደኋላ የሚሉ አይደሉም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስም እንዲሁ ነበሩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትክክለኛ ሰዎችን ለማግኘትና ሐሳቦቻቸውን ለመስማት ብዙ ርቀው የሚሄዱ  ናቸው፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር ለአሥር ጊዜ ያህል ተገናኝተናል፡፡ ወደ ጃፓን ለጉብኝት በሄዱ ጊዜም አስጠርተውኝ ከመወያየት አይቦዝኑም፡፡ ስንገናኝ ለሁለት ሰዓት ያህል እንነጋገራለን፡፡ ውይይታችንም አንዳችን ከሌላችን ዕውቀትን ለማግኘት በሚደረግ የጋራ ዕውቀት ልውውጥና አክብሮት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ መጽሐፌን ያነባሉ፡፡ እንደማስበው በጣም ቆፍጣና ተማሪና የአገር መሪ ናቸው፡፡ እንዲህ ያሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ከኢትዮጵያ ውጪ አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ ሟቹ መለስና ኃይለ ማርያም ያላቸውን ዓይነት ሰብዕና ሌሎች መሪዎች ውስጥ ብዙም አታገኘውም፡፡ አንዳንዴ በሚያስግርም ሁኔታ ምክር የሰጠንባቸው ነገሮች ተቀባይነት ማግኘት ብቻም ሳይሆን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምና ከሥራቸው ባሉት ሰዎች ሲተገበሩም እናያለን፡፡ መቶ በመቶ እንኳ ባይሆን የምንሰጣቸውን ምክሮች በአንክሮ ይቀበላሉ፡፡ አንዳንዴ መንግሥታትን አማክረን ሐሳብ የሰጠንባቸው ነገሮች ሲተገበሩ አናይም፡፡ ስለዚህ እንዲህ ካሉ ባለሥልጣናት ጋር መሥራቴ መልካም አገልግሎት እንድሰጥ ስለሚያስችለኝ ለኢትዮጵያ ጠንክሬ እየሠራሁ እገኛለሁ፡፡ እውነት ነው አንዳንድ ጊዜ ከመንግሥት አመለካከቶች ጋር ላንስማማ እንችላለን፡፡ አንዳንዴም እኔው ራሴ ልሳሳት እችላለሁ፡፡ ሆኖም በጋራ መተማመን ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ስላለን ያለንን አለመግባባት አንዳችን ከሌላችን አንደብቅም፡፡ እንደማስበው እንዲህ ያለው የዕውቀት ግንኙነት ጠቃሚ ከመሆኑም በላይ፣ከትልልቅ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ሲሆን ደግሞ የበለጠ የሚደነቅ ነው፡፡ በሌሎች አገሮች እንዲህ ዓይነቱ ግንኙነት ከባድ ሲሆን፣ ከትልልቆቹ ባለሥልጣናት ጋር ለሁለት ሰዓት ቁጭ ብሎ ስለኢኮኖሚክስ ማውራት የማይቻል ነው፡፡ በመንግሥታችሁ ልትኮሩ ይገባችኋል፡፡ እርግጥ በጠቅላላው ሲታይ መንግሥት ደካማ ነው፡፡ የግሉ ዘርፍም በጣም ደካማ ነው፡፡ በአፈጻጸም በኩል ከታየም ጥሩ የምትባሉበት ነገር የለም፡፡ ሆኖም መሪዎቻችሁ ጥሩ አስተሳሰብ ያላቸው ይመስለኛል፡፡ ጃፓን እንደናንተ ያለ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢኖራት ብዬ እመኛለሁ፡፡ ጠቅላይ ሚስትር ሺንዞ አቤን በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም እንቀይራችሁ ነበር (ፈገግ ለማሰኘት የተናገሩት)፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው?›› ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት...

ዘንድሮ ጀርመን በኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ግእዝና አማርኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክና መልክዓ ምድር ጠንቅቆ የተማረው የታላቁን ምሁር ሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ የልደት በዓልን እያከበረች ትገኛለች፡፡ በ1616 ዓ.ም....

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...