Sunday, March 3, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን ተመሠረተ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የተለያዩ አሠሪዎች ፌዴሬሽኖችን በማሰባሰብ የኢትዮጵያ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን የተሰኘው ተቋም በይፋ መመሥረቱን አደራጅ ኮሚቴው ማክሰኞ፣ መጋቢት 3 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ አሠሪዎች ፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች አሠሪዎች ፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ ከተሞች ውኃና ፍሳሽ አገልግሎት አሠሪዎች ፌዴሬሽን፣ የአማራ ክልል አሠሪዎች ፌዴሬሽን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አሠሪዎች ፌዴሬሽንን በማካተት የተዋቀረው አደራጅ ኮሚቴ፣ ላለፉት ዘጠኝ ወራት የማኅበራቱን ፌዴሬሽኖች ሲያወያይ ቆይቶ አዲሱን የአሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን ለማቋቋም እንደበቃ ከተሰጠው ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ፍትሕ ወልደ ሰንበት፣ ኮንፌዴሬሽኑን መመሥረት ለምን አስፈለገ በሚል ርዕስ ባቀረቡት ገለጻ፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት በአገራችን በርካታ አሠሪዎች ከአሠሪ ወደ ማኅበር፣ ከማኅበር ወደ ፌዴሬሽን እያደጉ በመምጣታቸውና በዚያው ልክም በአሠሪና ሠራተኛ መካከል ያለው ግንኙነት አገሪቱን ሊመጥን በሚችል መልኩ ወደ ኮንፌዴሬሽን ደረጃ ማደግ ስላስፈለገው፤›› ኮንፌደሬሽኑ መመሥረቱን ገልጸዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ለመንግሥትም፣ ለአሠሪውም ሆነ ለሠራተኛው በተደራጀ መልኩ ጥያቄዎችን ከማቅረብና በግልጽነት ሁሉን አሳታፊ በሆነ መልኩ በአንድ ላይ ተሰብስቦ መደራደርና መነጋገር የሚቻልበትን መንገድ ለመፍጠር እንደሚያስችል ስለታመነበት ኮንፌዴሬሽኑ እንዲመሠረት መደረጉን አብራርተዋል፡፡ በተጨማሪም አሠሪውም መብትና ግዴታውን በትክክል እንዲወጣ የሚያግዘው መሆኑ በመታመኑና በሌሎችም በርካታ ምክንያቶች ተደግፎና ‹‹ብዙ ሥራ ለብዙዎች መፍጠር›› የሚል ዓላማ ተካቶበት፣ ኮንፌዴሬሽኑን መመሥረት እንዳስፈለገ አቶ ፍትሕ ገልጸዋል፡፡

ከአሠሪዎች ፌዴሬሽን ጋር አለመግባባቶች እንደነበሩና ችግሩ ምን እንደሆነ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ የኢትዮጵያ ጥቃቅንና አነስተኛ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ኃይሌ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹እኛን ያደራጀን ራሱ ፌዴሬሽኑ ነው፡፡ ኋላ ላይ እኛ ወደ ኮንፌዴሬሽን ማደግ ስለነበረብን የአብረን እንሥራ ጥያቄ በተደጋጋሚ ብናቀርብም ምላሽ ሳይሰጥ ቆይቷል፡፡ እኛ ለመደራጀት በምንንቀሳቀስበት ወቅት ግን አንዳንድ ችግሮች ፈጥሮብን ነበር፡፡ እነሱ እስከ ዛሬ ለጥያቄያችን ምላሽ ባይሰጡም፣ ኮንፌዴሬሽኑን ለመመሥረት ምንም ስለማያግደን፣ መንግሥትም ስለሚደግፈን አባሎቻችንን አሳምነን ለዛሬው ምሥረታ በቅተናል፤›› ብለዋል፡፡

ፌዴሬሽኖቹ እስካሁን ለአባሎቻቸው ምን ሲያከናውኑ እንደቆዩም ተጠይዋል፡፡ አሠሪዎቹ ማኅበራት በርካታ ሥራዎችን አከናውነዋል ካሉ በኋላ፣ ‹‹እኛን በሚመለከት ከ2,500 በላይ ማኅበራት ሲኖሩን፣ በቅርቡ ከአዲስ አበባ ጥቃቅንና አነስተኛ ቢሮ ከ250 በላይ ከተደራጁ ሥራ ፈጣሪዎች ላይ በተወሰደው የማሸግ ዕርምጃ አሠሪ ፌዴሬሽኑ ሁሉንም ባለድርሻዎች በማደራደር ችግሩ እንዲፈታና የታሸጉትም ተከፍተው ሥራ እንዲጀምሩ አስችሏል፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡

ወደፊትም እንዲህ ዓይነቱ ዕርምጃ ያለ ኮንፌደሬሽኑ ዕውቅና እንዳይወሰድ ስምምነት ላይ ስለመደረሱም ተናግረዋል፡፡ ሆኖም በመንግሥት የሚወሰደው ዕርምጃ አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ እየታየ በመሆኑ፣ በኮንፌዴሬሽኑ በኩል ሕግን በተከተለ መንገድ የመጨረሻ መፍትሔ ለማስቀመጥ እንደሚሠራ አቶ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡

ኮንፌዴሬሽኑ ይመለከተዋል ካላቸው አካላት ጋር ውይይት በማዘጋጀት ችግሩን ለመፍታትና ሊሠራ ስላሰባቸው ሥራዎች ብሎም በኢንቨስትመንት በኩል አገሪቱ ያሏትን ምቹ ሁኔታዎች የሚያሳይ ዓውደ ራዕይን ጨምሮ የጥናታዊ ጽሑፎችን በማዘጋጀት የኮንፌዴሬሽኑን ምሥረታ ለማብሰር እየተዘጋጀ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች