Wednesday, April 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በንግድ ተቋማት ላይ ዕርምጃ ቢወሰድም የዋጋ ግሽበት ተባብሶ ቀጥሏል

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ወራት ያለምንም በቂ ምክንያት የዋጋ ጭማሪ አድርገዋል ያላቸውን በርካታ የንግድ ተቋማት ቢያሽግም፣ በምግብና ምግብ ነክ ባልሆኑ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ግሽበት ተባብሶ ቀጥሏል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ከ2009 እስከ 2011 ዓ.ም. ድረስ ተግባራዊ እንዲደረግ ያዘጋጀውና በካቢኔ የፀደቀው የመካከለኛ ጊዜ የወጪ ማዕቀፍ ዕቅድ፣ በ2010 ዓ.ም. የዋጋ ግሽበቱ በነጠላ አኃዝ (ስምንት በመቶ) እንደሚሆን ተንብዮ ነበር፡፡

ነገር ግን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ያወጣው የየካቲት ወር የዋጋ ግሽበት 15.6 በመቶ መሆኑን በመመልከቱ፣ የአዲስ አበባ የዋጋ ግሽበት ተመሳሳይ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በተጠናቀቀው የካቲት ወር በርበሬ በኪሎ እስከ 150 ብር፣ ጤፍ እስከ 33 ብር፣ የሽሮ እህል እስከ 40 ብር፣ ዘይት በሊትር (የኑግ) እስከ 80 ብር፣ ድፍን ምስር እስከ 40 ብር ድረስ ለግብይት ሲቀርቡ የስኳርና የስንዴ ዱቄት በገበያ ውስጥ እጥረት እንደተፈጠረ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ኤጀንሲው ባወጣው መረጃ የየካቲት ወር የዋጋ ግሽበት በጥር ወር ከነበረው የ2.5 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ በተለይ በጥራጥሬ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በርበሬና በቅመማ ቅመም ምርቶች ባልተለመደ ሁኔታ በተጠናቀቀው ወር የ50 በመቶ የዋጋ ጭማሪ መታየቱ ተገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ምግብ ነክ ባልሆኑ ሸቀጦች፣ የኮንስትራክሽን ዕቃዎች፣ አልባሳትና መጫሚያዎች፣ የቤት ውስጥ መገልገያ ዕቃዎች፣ የሆቴል ምግቦች፣ የጤና ወጪዎች በዋጋ ንረው መገኘታቸው ተመልክቷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዳምጠው አበበ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ ባለፉት ስድስት ወራት ያለምክንያት ዋጋ የጨመሩ 4,022 ንግድ ሱቆች ታሽገዋል፡፡ ሰባት ሺሕ ሱቆች የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ 8,250 ሱቆች ደግሞ የቃል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

ነገር ግን የዋጋ ግሽበቱ በመጋቢት ወርም እንዲሁ የቀጠለ ሲሆን፣ አካሄዱ ሸማቾችን አስደንግጧል፡፡ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ሸማቾች እንደሚሉት፣ የዋጋ ግሽበቱ በሳምንትና በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከእጥፍ በላይ ጨምሯል፡፡ አሁን ባለው ገበያ አንዴ የወጣ ዋጋ የማይመለስ በመሆኑ፣ አዝማሚያውም የመጨመር ብቻ ስለሆነ ገበያው አስፈሪ እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡

ነጋዴዎችም በፖለቲካው አለመረጋጋት ምክንያት ቀድሞ እንደነበረው ምርት እየገባ አለመሆኑን፣ የገባውም ምርት በተለያዩ ምክንያቶች ዋጋው መጨመሩን ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ለውጥ በመደረጉና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት የለም ማለት በሚቻል ደረጃ ላይ በመሆኑ፣ በገበያ ውስጥ የኢንዱስትሪ ምርቶች የዋጋ ግሽበት ተፈጥሯል፡፡ መንግሥት ሱቆችን መዝጋትን ብቻ አማራጭ አድርጎ መውሰዱ ችግሩን ከማባባስ ውጪ፣ መፍትሔ ይሆናል ብለው እንደማያምኑ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ነጋዴዎች ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች