Friday, March 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሽብር ተግባር ተጠርጥረው በተከሰሱት የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ላይ ምስክርነት ተሰማ

በሽብር ተግባር ተጠርጥረው በተከሰሱት የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ላይ ምስክርነት ተሰማ

ቀን:

–  የመኢአድ ፕሬዚዳንት በነፃ ተሰናበቱ

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ከተፈረጀው የግንቦት ሰባት ድርጅት ጋር ለመቀላቀል ሲጓዙ በቁጥጥር ሥር ውለዋል ተብለው ክስ የተመሠረተባቸው አራት የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ላይ የምስክርነት ቃል ተሰጠ፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የመሠረተውን የሽብር ድርጊት ወንጀል ክስ እየመረመረ ለሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 14ኛ ወንጀል ችሎት ምስክሩን ያሰማው ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ነው፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የተመሠረተባቸውን ክስ እንደማይቃወሙና ድርጊቱን መፈጸማቸውን በማመናቸው፣ ዓቃቤ ሕግ በክሱ የጠቀሰውን አንድ ምስክር አሰምቷል፡፡

የዓቃቤ ሕግ ምስክር ሆነው የቀረቡት ግለሰብ እሳቸውም የሰማያዊ ፓርቲ አባል እንደነበሩ አስታውቀው፣ የፓርቲው የተለያዩ ክፍሎች አመራሮች የነበሩትን ብርሃኑ ተክለ ያሬድ፣ እየሩሳሌም አስፋውንና ፍቅረ ማርያም አስማማውን የሚያውቋቸው በፓርቲው ውስጥ በነበሩበት ጊዜ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ተከሳሽ ብርሃኑና እየሩሳሌም የካቲት 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ሰላማዊ ትግሉ እንደማያዋጣ ተነጋግረው ግንቦት ሰባትን ለመቀላቀል ወደ ኤርትራ ለመሄድ ሲንቀሳቀሱ ምስክሩም አብረው ባህር ዳር ድረስ መሄዳቸውን ተናግረዋል፡፡

ባህር ዳር እንደደረሱ እሳቸው (ምስክሩ) ሐሳባቸውን በመቀየር ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን ያስረዱ ሲሆን፣ ተከሳሽ ብርሃኑ ‹‹ለምን ትመለሳለህ? ቢያንስ ጎንደር የምናገኘው ሰው ስላለ እሱን ካገኘህ በኋላ ትመለሳለህ፤›› ቢላቸውም ሳይስማሙ ቀርተው መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹በወቅቱ ስሜታዊ ሆኜ መወሰኔ አግባብ እንዳልሆነ ስለተረዳሁ ነው፤›› በማለት ‹‹ለምን ሐሳብህን ቀየርክ?›› ለሚለው መስቀለኛ ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ምስክር ለመሆን መገደድ አለመገደዳቸውን፣ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው፣ ታስረው እንደነበርና ግንቦት ሰባት ነፃ አውጪ ወይም አሸባሪ ድርጅት መሆኑን እንዲያስረዱ በተከሳሾቹ ሲጠየቁ ዓቃቤ ሕግ ተቃውሟል፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀን ድርጅት መጠየቁ አግባብ አለመሆኑን ዓቃቤ ሕግ በማስረዳቱ፣ ፍርድ ቤቱም የተከሳሾቹ ጥያቄ እንዲታለፍ በይኗል፡፡ ምስክሩ በአራተኛ ተከሳሽ ደሴ ካህሳይ ላይ የምስክርነት ቃል አልሰጡም፡፡

ፍርድ ቤቱ ብይን ለመስጠት ለመስከረም 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ አይኤስን ለመቃወም መንግሥት ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ጠርቶት በነበረው ሰላማዊ ሠልፍ ላይ የተፈጠረውን ብጥብጥ በማደራጀትና በመምራት ተጠርጥረው ክስ ተመሥርቶባቸው የነበሩት የመኢአድ (የቀድሞ) ሊቀመንበር  አቶ ማሙሸት አማረ በነፃ ተለቀዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ የመሠረተባቸውን ክስ ሲመረምር የከረመው የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት አቶ ማሙሸትን በነፃ ያሰናበታቸው፣ ሰላማዊ ሠልፉ በተደረገበት ዕለት እሳቸው ከምርጫ ቦርድ ጋር በነበረባቸው ክርክር ፍርድ ቤት መዋላቸውን የሚያስረዳ ሰነድ በማቅረባቸው ነው፡፡ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበባቸው ምስክሮች የሰጡት የምስክርነት ቃል የተጠና መሆኑን በመቃወም ጠበቃቸው ለፍርድ ቤት በማስረዳታቸውና ምስክሮቹም የተለያየና የማይገናኝ የምስክርነት ቃል መስጠታቸው ለአቶ ማሙሸት በነፃ መሰናበት ምክንያት ሆኗል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...