Thursday, March 23, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮ ከሶ ካስቀጣቸው ድርጅቶችና ግለሰቦች 270 ሚሊዮን ብር ገቢ ሰበሰብኩ አለ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮ በ2007 በጀት ዓመት በሕዝብና በመንግሥት ጥቅም ላይ ጉዳት ያደረሱ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን ከሶ በማስቀጣት፣ ከ270 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ ተክሌ ዲዱ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ቢሮው በበጀት ዓመቱ 2,558 ጉዳዮችን ለማየት ያቀደ ቢሆንም የቀረቡለት ጉዳዮች 2,458 ናቸው፡፡ በአብዛኛው የቀረቡት ጉዳዮች ድርጅቶችና ግለሰቦች የመንግሥት ቤቶችና መሬቶችን በሐሰተኛ ሰነድ የግል ሀብት ማድረግ፣ እንዲሁም በራሳቸው መሬት ላይ ሕጋዊ የግንባታ ፈቃድ ሳይዙ ግንባታ ፈጽመው መገኘት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ በመሆኑም ክስ ተመሥርቶባቸው ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑትን በማስቀጣት ገቢው እንደተገኘ አስረድተዋል፡፡

የግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባዔ በበኩሉ ከ200 ያላነሱ ጉዳዮችን ለማየት አቅዶ በቀረቡለት 90 ይግባኞች ላይ ውሳኔ መስጠቱን አቶ ተክሌ ገልጸው፣ ከዚህም አስተዳደሩ ከ24 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡ በኪራይ ሰብሳቢነት የተፈረጁና የተጣራባቸው 153 ሰዎችን ማባረሩንም አክለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮ በሥሩ የሚገኙ የደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤት፣ ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ፣ ማኅበራዊ ፍርድ ቤት፣ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ፣ ግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባዔ፣ ቦታ ማስለቀቅና የካሳ ጉዳዮች ጉባዔ መሥሪያ ቤቶች እንደሚገኙ ኃላፊው ገልጸው፣ በበጀት ዓመቱ የፈጸሟቸውን ተግባራትንም አስረድተዋል፡፡

የመሬት ወረራ በተለየ ሁኔታ የተካሄደባቸው ክፍላተ ከተሞች ኮልፌ ቀራኒዮ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ቦሌና የካ ሲሆኑ፣ የደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤት በመከታተል ዕርምጃ መውሰዱን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

ጽሕፈት ቤቱ ሕገወጥ የጎዳና ላይ ንግድን (የሚነግዱና የሚሳተፉ)፣ ሕገወጥ ግንባታና መሬት ወረራን፣ ሕገወጥ የእንስሳት ዕርድን በዋናነት እንደሚቆጣጠር የጠቆሙት የቢሮ ኃላፊው፣ በበጀት ዓመቱ 45,962 ሕገወጥ  የጎዳና ላይ ነጋዴዎችን፣ 11,669 ሕገወጥ ወራሪዎችና ሕገወጥ ገንቢዎችን፣ 231 ሕገወጥ አራጆችና በመንገድ ደኅንነት ላይ ጉዳት ባደረሱ 8,371 ግለሰቦች ላይ ዕርምጃ መውሰዱን ገልጸዋል፡፡ አዋጭ ንግድ በሚባሉት ሺሻና ጫት በትምህርት ቤቶች አካባቢ በሚነግዱ 3,261 በሚሆኑ ላይ ዕርምጃ መውሰዱንም አክለዋል፡፡ ሕገወጥ ዕርዶች በቦሌና በጉለሌ ሸጎሌ አካባቢ በብዛት እንደሚፈጸሙም ጠቁመዋል፡፡

ከተገልጋዮችና ከአገልጋዩ ጋር የተያያዘ የመልካም አስተዳደር ችግር የሚታይበት በወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ መሆኑን ያስረዱት (የቢሮ ኃላፊው)፣ እስከ 2001 ዓ.ም. ድረስ ለ1,935 ሰዎች በአንድ ማዕከል አገልግሎቱ ይሰጠ እንደነበር አስታውሰው፣ በአገር አቀፍ አንድ ዓይነት መታወቂያ ለመስጠት የሚያስችል አሠራር ተዘርግቶ በ81 ወረዳዎች አዲስ ሶፍትዌር ተዘጋጅቶ ምዝገባ መጀመሩን፣ በቀጣይ በሁሉም ወረዳዎች (በ116ቱም እንደሚዳረስ) አስረድተዋል፡፡ ‹‹አንድ ሰው ሁለትና ከዚያም በላይ መታወቂያና የተለያዩ ማስረጃዎች የሚይዝበትና የኪራይ ሰብሳቢነት አሠራር የሚቀርበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፤›› በማለት አክለዋል፡፡

የፍትሕ ቢሮው የተለያዩ ሕጎችን፣ ደንቦችንና መመርያዎችን አርቅቆ ለካቢኔው በማቅረብ ከማፅደቁም በተጨማሪ በ2008 ዓ.ም. ለካቢኔው ቀርበው ከሚፀድቁት ረቂቅ ሕጎች ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን ረቂቅ፣ የኢንዱስትሪ ቢሮ ማቋቋሚያ አዋጅ፣ የትምህርት ጥራት ኤጀንሲ ደንብና በድምሩ 30 የሚደርሱ ረቂቅ አዋጆችና ደንቦች መዘጋጀታቸውን አቶ ተክሌ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች