Friday, June 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሰማንያ ዓመት የሩቅ ወዳጆች

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ጃፓንና ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከጀመሩ ከሰማንያ ዓመት በላይ ቢያስቆጥሩም ግንኙነታቸው የዕድሜውን ያህል በኢኮኖሚ፣ በኢንቨስትመንትና በንግድ መስክ ብዙ የተጓዘ አይደለም፡፡ መንግሥት ከእስያ ቻይናና ህንድን፣ ከአውሮፓ እነ ቱርክን ያመጣለት የኢንቨስትመንት ፖሊሲና ማበረታቻ እንደ ጃፓን ያሉትን ሊስብለት አልቻለም፡፡ እርግጥ ጃፓኖች ከሌሎች የአንደኛው ዓለም አገሮች የሚለይ ጠባይ እንዳላቸው ቢናገሩም፣ ኢንቨስት ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን ወደ አፍሪካ በጠቅላላው የመጡት በጣም በጥቂቱ ነው፡፡

በኢትዮጵያና በጃፓን መካከል ለነበረው ግንኙነት የዘውድ ዘመን ትልቅ ዕድል ፈጥሮ እንደነበር ይነገራል፡፡ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት የሚገኘው የጃፓናውያን ባህላዊ ቤትና አጸድ ለዚህ ግንኙነት ይጠቀሳል፡፡ በጃፓን ዲፕሎማት የነበሩ የመንግሥት እንደራሴዎች፣ በጃፓንና በኢትዮጵያ መካከል እ.ኤ.አ. በ1930ዎቹ የተመሠረተው የዲፕሎማሲ ግንኙነት ወደ ቤተሰባዊ ዝምድና ሊያመራ ጫፍ የደረሰበት ወቅት ተከስቶ እንደነበር ሲገልጹ ይደመጣል፡፡ ይኸውም የሁለቱ አገሮች የዘውድ አገዛዞች፣ ለተመሠረተው የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተምሳሌታዊ ምልክት ይሆን ዘንድ በጋብቻ መተሳሰር እንደሚገባ ተስማምተው ድግስ ለመደገስ ሽርጉድ ተጀምሮ ነበር፡፡ ከሁለቱ አገሮች የተውጣጡ ልዑካን አንዱ ወደ ሌላኛው አገር በየጊዜው እየተመላለሱ ያደርጉ የነበረው ዝግጅትም መፋፋም ጀምሮ ነበር፡፡

 ይሁንና ጊዜው እየገፋ በመጣ ቁጥር ማለትም የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሊጀመር ነጋሪት መጎሰም ሲጀመር፣ ጃፓኖች ‹‹ትሪፕል አክሰስ›› የሚል ስያሜ በተሰጠውና በጀርመን አዝማችነት በተመራው የሦስትዮሽ ቡድን ውስጥ ጃፓንና ጣልያን ወገንተኛ ሆነው በመሰለፋቸው ምክንያት የተጀመረው የንጉሣውያኑ ቤተሰቦች የጋብቻ ውጥን በጥንስሱ ሊቀር መቻሉን ቀደምት ዲፕሎማቶች ይዘክሩታል፡፡ ከጦርነቱ ፍጻሜ በኋላ እያፍገመገመ የጀመረው ግንኙነት በደርግ መንግሥት መምጣት ተቋርጦ ቆየ፡፡ በኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ያንሰራራው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በይበልጥ ከጃፓን በሚመጣ ዕርዳታና ቴክኒክ ድጋፎች ላይ አመዝኖ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ጃፓን በምትልካቸው የግብርና ሸቀጦችና ጃፓን ወደ ኢትዮጵያ በምታደርሳቸው የኢንዱስትሪ ውጤቶች ላይ የተመሠረተ የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነት ሥር ቢሰድም፣ በኢንቨስትመንት መስክ የሚታየው ግንኙነት ግን የኢትዮጵያ መንግሥት በሚፈልገው መጠን ሆኖ አልተገኘም፡፡ ይህ ነው የሚባል የጃፓን ኢንቨስትመንት ላለመምጣቱ በኢትዮጵያም በጃፓኖች በኩልም የሚጠቀሱ ምክንያቶች አልታጡም፡፡ ከነሐሴ 25 ጀምሮ ለሦስት ቀናት በሸራተን አዲስ እየተካሄደ የሚገኘውና ረቡዕ ነሐሴ 27 ቀን 2007 ዓ.ም. የሚጠናቀቀው፣ የአፍሪካ ጃፓን የኢንቨስትመንትና የንግድ ፎረም ላይ የመንግሥት ኃላፊዎች ማብራሪያ ላይ ምክንያቶቹ ተጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ በኩል ከሚሰነዘሩ ምክንቶች መካከል የጃፓኖች ኢኮኖሚ እጅግ በመምጠቁና ከፍታው ላይ በመውጣቱ፣ ኢኮኖሚያቸው በከፍተኛ ዕውቀት፣ ካፒታልና ክህሎት ላይ በመመሥረቱ ሳቢያ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ኩባንያዎች አለመታየት አንዱ ምክንያት መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ አስረድተዋል፡፡ ከጃፓን የሚሰደዱ የሰው ጉልበት ላይ የተመሠረቱ ኢንዱስትሪዎች (ሌበር ኢንቴንሲቭ) በአሁኑ ወቅት አለመኖራቸውም ሌላኛው የዶ/ር አርከበ መከራከሪያ ነው፡፡ የጃፓን ጉልበት ተኮር ኢንዱስትሪዎች ከሦስር አሥርታት ቀድመው እንደ ኮሪያና ታይዋን በመሳሰሉት አገሮች ተንሰራፍተው በዚያ ተስፋፍተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሦስተኛው የዶ/ር አርከበ መከራከሪያ አፍሪካ እንደ አኅጉር፣ ኢትዮጵያም እንደ አገር ለውጭ ኢንቨስተሮች ምቹ መሆናቸው በዓለም መስተጋባት የጀመረው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ነው፡፡ ‹‹አፍሪካ እየተነሳች ነው›› ወይም ‹‹አፍሪካ ራይዚንግ›› የሚሉ መፈክሮች መደመጥ ከጀመሩ ጥቂት ዓመታት ብቻ አስቆጥረዋል ያሉት ዶ/ር አርከበ፣ ይህ አገላለጽ ከመስተጋባቱ ቀድሞ ግን የውጭ ኢንቨስተሮችን ለመቀበል የሚያስችሉ አመቺ ሁኔታዎች አለመፈጠራቸውና የውጭው ዓለም ለአፍሪካም ለኢትዮጵያም የሰጠው አዎንታዊ ምስል፣ የውጭ ኢንቨስትመንት በተለይ ደግሞ የጃፓኖች ኢንቨስትመንት እዚህ ግባ የሚባል እንዳይሆን አስተዋጽኦ ማድረጉን ይስማሙበታል፡፡

የጃፓን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) ምክትል ፕሬዚዳንት ሂሮሺ ካቶ በበኩላቸው፣ የጃፓን ኢንቨስትመንት በአፍሪካ እንደሚፈለገው መጠን ላለመታየቱ ገፊ ከነበሩ ምክንያቶች መካከል የጃፓን ሕዝብ በብዛት ወደ እርጅናው ያደላ በመሆኑ በሌሎች አገሮች ሄዶ ኢንቨስት ለማድረግ ያለው ፍላጎት ዝቅተኛ መሆን ይገኝበታል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1990ዎቹ ተንሰራፍቶ የቆየው ‹‹የጥቁር ጽልመተኝነት›› ወይም ‹‹አፍሮ ፔሲሚዚም›› ዝንባሌም ጫና አሳድሮ መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ አመለካከት እየተለወጠ እንደመጣ የገለጹት ካቶ፣ የአፍሪካ ፖለቲካዊ መረጋጋት፣ የመንግሥታት ከሙሰኛነት እየጸዱ መምጣት በአዎንታዊነት የሚጠቀሱና ለአፍሪካ ኢንቨስትመንት መዳረሻነት አበርክቶ ያላቸው ክስተቶች መሆናቸውን ካቶ ተናግረዋል፡፡

ይህ ቢባልም ግን የጃፓን መንግሥት፣ አገሪቱን በክፉ የሚያስነሱ ኩባንያዎችን በዝምታ እንደማይመለከትም ካቶ ተናግረዋል፡፡ ለተፈጥሮ ሀብቶች ከፍተኛ ጥማት ያላት ጃፓን በዚህ ሳቢያ ኩባንያዎቿ በድሆች አገሮች ውስጥ የሚገኙ ሀብቶችን በማሟጠጥ ለብዝበዛ እንዳይዳርጉ መንግሥታቸው ቁጥጥር እንደሚያደርግ አስታውሰዋል፡፡

በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶ/ር ማርቆስ ተክሌ እንዳስታወቁት ግን ምንም እንኳ ጃፓኖች እስካሁን የሚፈለገውን ያህል የውጭ ኢንቨስትመንት ምንጭ ባይሆኑም ይህንን ለመለወጥ ሲባል የኢንቨስትመንትና የንግድ ስብሰባዎች እየተካሄዱ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡ ጃፓኖች ከሚሰጡት ዕርዳታና የቴክኒክ ድጋፍ በተጨማሪ የረጅም ጊዜ ብድር ለመስጠትም ፍላጎት ማሳየታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በመጪው ዓመት በኬንያ የሚካሄደው ‹‹ቶኪዮ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ለአፍሪካ ልማት ጉባዔ (ቲካድ) እስካሁን በጃፓን ሲካሄድ ቢቆይም ኬንያ በመጪው ዓመት እንድታካሂደው መወሰኑም የጃፓን ዓይኖች ወደ አፍሪካ ለማቅናታቸው ተምሳሌት እየተደረገ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች