Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናመንግሥት ለጃፓን አምራቾች የኢንዱስትሪ ፓርክ ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታወቀ

መንግሥት ለጃፓን አምራቾች የኢንዱስትሪ ፓርክ ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታወቀ

ቀን:

– ጃፓን ለትልልቅ ፕሮጀክቶች የሚውል ብድር ለመስጠት ፍላጎት አላት

የጃፓን ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ያቀደው መንግሥት በርካታ አምራቾችን ወደ አገር ውስጥ ለማምጣት ያስችላል ያለውንና ለጃፓኖች ፍላጎት እንዲስማማ ተደርጎ የሚከለል ኢንዱስትሪ ፓርክ ለመስጠት ማቀዱን ይፋ አደረገ፡፡ 

የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አማካሪ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ ለጋዜጠኞች ይፋ እንዳደረጉት፣ በመጪዎቹ 12 ወራት ውስጥ ዕውን እንደሚሆን የሚጠበቅ የኢንዱስትሪ ፓርክ ለጃፓኖች ለማዘጋጀት መንግሥት ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ምንም እንኳ ኢንዱስትሪ ፓርኩ እንዲዘጋጅ መንግሥት መወሰኑ ቢገለጽም ፓርኩ የት እንደሚገነባ፣ እንዴትና በምን ያህል ስፋት ይገነባል ለሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ አልተገኘም፡፡

- Advertisement -

መንግሥት በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ እንደሚገነቡ ካቀዳቸው አምስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያልተካተተው አዲሱ የጃፓኖች ኢንዱስትሪ ፓርክ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥናቱ አልቆ ሥራ እንደሚጀምር ከኢትዮጵያ ወገን ይገለጽ እንጂ ለጃፓኖች እንግዳ መሆኑ ታውቋል፡፡

ከጃፓን ኤምባሲ መረዳት እንደተቻለውም በኢትዮጵያ መንግሥት በሐሳብ ደረጃ ያለ እንጂ ይህ ነው የሚባል የጃፓን ኢንቨስተር ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሌለ መረጃው ይጠቁማል፡፡ ይህም ቢባል ግን በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶ/ር ማርቆስ ተክሌ ለሪፖርተር በሰጡት መግለጫ፣ ኢንዱስትሪ ፓርኩ የት ሊገነባ እንደሚችል ዝርዝር ጥናቶች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ ብለው፣ ጥናቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ አልቆ ተግባራዊ እንደሚደረግ አምባሳደሩ አስታውቀዋል፡፡ 

በሌላ በኩል የጃፓን መንግሥት በኢትዮጵያ ለሚካሄዱ የተለያዩ ፕሮጀክቶች የረጅም ጊዜ ብድር ለማቅረብ ፍላጎት እንዳለው አምባሳደር ማርቆስ አስታውቀዋል፡፡ በጃፓን መንግሥት የፋይናንስ ድጋፍ ከሚደረግባቸው መካከል የአልቶ ላንጋኖ ጂኦተርማል ፕሮጀክት ይጠቀሳል፡፡ የጃፓን መንግሥት ይህንን ፕሮጀክት ለመደገፍ ዝግጁ ቢሆንም፣ የጥናት ጊዜውና ቁፋሮው ከታሰበው በላይ መጓተቱን አምባሳደር ማርቆስ ገልጸዋል፡፡ ይህም ሆኖ የጃፓንን የፋይናንስ ምንጮች በአግባቡ ለመጠቀም በኢትዮጵያ በኩል የሚታየው ዝግጅት አነስተኛ መሆኑንም አምባሳደሩ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹እነሱ ብድር እንሰጣለን ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቶቻችን ዝግጁ አልሆኑም፡፡ ለምሳሌ አልቶ ላንጋኖ እየተሠራና እየተቆፈረ ረጅም ጊዜ ፈጀ፡፡ እርግጥ ጂኦተርማል የመጀመሪያችን ስለሆነ ነው፡፡ እነሱ ግን ፋይናንስ ሊያደርጉት ወስነዋል፤›› ብለዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ‹‹ኳሊቲ ኢንፍራስትራክቸር ኢኒሺዬቲቭ›› የተባለው አዲሱ የጃፓን አቅጣጫ ጥራት ያላቸው የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ የሚያስችል አዲስ ፕሮግራም በጃፓኖች መተግበር መጀመሩም ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የጃፓንን ብድር ለማግኘት ካላስቻሏት ሌሎች ምክንያቶች መካከል አገሪቱ ከፍተኛ ዕዳ ክምችት አገሮች ዝርዝር ውስጥ መካተት እንደነበር አምባሳደር ማርቆስ ጠቁመው፣ ኢትዮጵያ ከእነዚህ አገሮች ዝርዝር ውስጥ ከወጣች አራት ዓመታት መቆጠራቸውንና ጃፓኖችም ይህንን በመመልከት ለማበደር ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ የጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) ምክትል ፕሬዚዳንት ሂሮዪሺ ካቶ በበኩላቸው ምንም እንኳ አገራቸው ለኢትዮጵያ ብድር መስጠትን አቋርጣ ብትቆይም በአሁኑ ወቅት ለማበደር ፍላጎት እንዳላት ጠቁመዋል፡፡ ይህም ሆኖ ጃፓን ብድር ከምትሰጥባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ የብድር ዕዳ የመሸከም አቅም ክምችት ከኢኮኖሚ አኳያ ያላቸውን ተዛምዶ ፈትሻ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በጃፓን መንግሥት ዕርዳታ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተገነቡ መሠረተ ልማቶች መካከል ዓባይ በረሃ ላይ የተገነባው የህዳሴው ድልድይን ጨምሮ ከአዲስ አበባ ደብረ ማርቆስ ድረስ የተዘረጋው የአስፓልት መንገድ፣ የአዋሽ ድልድይ፣ በሁለት ዓመት ውስጥ ለ53 ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የተሰጡ ነፃ የትምህርት ዕድሎችን ጨምሮ የካይዘን አሠራር ሥርዓት ጃፓን ኢትዮጵያን ለመርዳት የምታደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች እንደሚያሳዩ አምባሳደር ማርቆስ ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል በዓመት የሚላከውን 30 ሺሕ ቶን ቡና ጨምሮ፣ ሰሊጥ፣ አበባና የቆዳ ውጤቶች ወደ ጃፓን ገበያ እየተላኩ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

ጃፓኖች በአምራች ኢንዱስትሪ ረገድ ወደ ኢትዮጵያ አልመጡም ያሉት አምባሳደሩ ለመምጣት እየተዘጋጁ ያሉ ኩባንያዎች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡ ጃፓን ሠራሽ የኔትወርክ ቴክኖሎጂዎችን ለዜድቲኢ በማቅረብ ኢትዮጵያ ውስጥ ምርቶቹ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያደርገውና ኤንኢሲ የተባለው የጃፓን ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ፍላጎት ካላቸው ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ኮዮ ሆልሲንግስ የተባለውና የሶላር ምርቶችን የሚያመርተው ኩባንያም ኢትዮጵያ ውስጥ አቅም ያለውና አብሮት የሚሠራ ታማኝ አገር በቀል ኩባንያ ካገኘ በሴኔጋል እንደከፈተው የሶላር ውጤቶች ማምረቻ ፋብሪካ ለመክፈት ፍላጎት እንዳለው የኩባንያው ተወካዮች ለሪፖርተር አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር የመግባቢያ ስምምነት ያደረገው ቶሺባ የተባለው ኩባንያ በቀጥታ ከመንግሥት ጋር ስምምነት ካደረጉና እንቅስቃሴ ከጀመሩ ጥቂት ኩባንያዎች መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡ አምባሳደር ማርቆስ እንደጠቀሱት ቶሺባ ኩባንያ ለኤሌክትሪክ ሠራተኞች ሥልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...