Friday, June 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የጃፓንና የአፍሪካ ባለሥልጣናት የሚሳተፉበት የኢንቨስትመንት ፎረም ይካሄዳል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከጃፓን የመንግሥትና የግል ተቋማት የተውጣጡና ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ 80 የጃፓን ልዑካንን ጨምሮ፣ ከ300 በላይ ባለሥልጣናትና ተሳታፊዎች የሚታደሙበት የአፍሪካ ጃፓን የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም ለሦስት ቀናት በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው፡፡

ከነሐሴ 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት በሸራተን አዲስ የሚካሄደው ፎረም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ከጂቡቲ፣ ከታንዛንያ፣ ከጋና፣ ከደቡብ አፍሪካ የሚመጡ ሚኒስትሮች ሲኖሩ፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ኃላፊዎችም ይታደማሉ፡፡ የጃፓኑ ኒኪ ቢዝነስ ሳምንታዊ መጽሔት (በዓለም አቀፍ የስቶክ ገበያዎች ላይ ታዋቂ የሆነው የኒኪ ግሩፕ አባል ኩባንያ ነው) ከአፍሪካን ቢዝነስ መጽሔት ጋር በትብብር ባዘጋጁት በዚህ የቢዝነስና የኢንቨስትመንት ፎረም ለመሳተፍ ከሚመጡት የጃፓን ባለሥልጣናት መካከል ሚኒስትሮች ተካተዋል፡፡

ሪፖርተር ከአፍሪካን ቢዝነስ መጽሔት ባገኘው መረጃ መሠረት፣ የጃፓን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) ምክትል ፕሬዚዳንት ሒሮሺ ካቶ ከሚጠበቁት መካከል ይገኙበታል፡፡ በአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምሥራቅና በአፍሪካ የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሞሪዩኪ ኤይዳን ጨምሮ የጃፓን ከፍተኛ ተቋማት ኃላፊዎች በፎረሙ ከሚጠበቁት መካከል ይገኙበታል፡፡ በአምስቱ ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድና በኢንዱስትሪ መስኮች ላይ መንግሥትን በማማከር የሚታወቁት ፕሮፌሰር ኬኒቺ ኦህኖም ተሳታፊ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ፕሮፌሰር ኦህኖ በጃፓን ናሽናል ግራጁዌት ኢንስቲትዩት ፎር ፖሊሲ ስተዲስ ተቋም በፕሮፌሰርነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

ከኒኪ ቢዝነስ በተገኘው መረጃ መሠረት በፋይናንስ፣ በአግሪ ቢዝነስ፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በኃይልና በቴክኖሎጂ መስኮች ላይ ውይይት ይደረጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ፎረሙ የአፍሪካና የጃፓን ኢንቨስተሮች የንግድ ኔትወርክ የሚፈጥሩበት፣ ስለመልካም አጋጣሚዎች የሚመክሩበትና በሁለቱ መካከል ስላለው ምቹ ሁኔታ የሚመክሩበት እንደሚሆን ታውቋል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ የመጣው የጃፓን የፋይናንስና የምርምር ተቋማት፣ የጃፓን ኩባንያዎች በአፍሪካ አገሮች ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ የሚችሉባቸውን መስኮች የመመርመርና ፋይናንስ የማቅረብ አማራጮችን የማየት ዓላማ ያለው ጉብኝት በማድረግ ይታወቃሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥታዊ የጃፓን የፋይናንስ ተቋማት የረጅም ጊዜ ብድር በመስጠት ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ ለማድረግ የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎች በማጥናት ላይ እንደሚገኙም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ለአብነትም በኢትዮጵያ የስምጥ ሸለቆ ከእንፋሎት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ያስችላል የተባለውን የአሉቶ ላንጋኖ ጂኦተርማል ፕሮጀክት ፋይናንስ ለማድረግ የጃፓን መንግሥት በጥናት ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለፕሮጀክቱ አዋጭነት በጃፓን መንግሥት ፈንድ ጥናት በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች