Friday, March 31, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ክራውን ሆቴል በክራውን ፕላዛ ላይ ያቀረበው የሰበር አቤቱታ ያስቀርባል ተባለ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ክራውን ሆቴል የቅድሚያ መብት እንዳለው በመግለጽ ሲክስ ኮንቲኔንትስ ሆቴልስ ኢንክ ያቀረበውን ‹‹CROWNE PLAZA›› የሚለውን የንግድ ምልክት መመዝገቡ፣ መሠረታዊ የሕግ ጥሰት መሆኑን በመግለጽ ክራውን ሆቴል ያቀረበው የሰበር አቤታቱ ያስቀርባል ተባለ፡፡

ሲክስ ኮንቲኔንትስ ሆቴልስ ኢንክ ‹‹CROWNE PLAZA›› የሚለውን የንግድ ምልክት ጽሕፈት ቤቱ እንዲመዘግብለት ያቀረበውን ጥያቄ ጽሕፈት ቤቱ የካቲት 18 ቀን 2005 ዓ.ም. ‹‹ክራውን ሆቴል›› ከሚለው ስያሜ ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ አይመዘገብም ብሎ ውድቅ ማድረጉን ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡

 የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ውድቅ ያደረገውን ጥያቄ በመቀበል፣ ሚያዝያ 28 ቀን 2006 ዓ.ም. የሲክስ ኮንቲኔንትስ ሆቴልስ ኢንክ የጠየቀው የንግድ ምልክት ምዝገባ እንዲቀጥል ውሳኔ መስጠቱ፣ አዋጅ ቁጥር 501/98ን (የንግድ ምልክት ምዝገባና ጥበቃ አዋጅ)  የሚቃረን መሆኑን ክራውን ሆቴል በይግባኝ አቤቱታው ተጠቁሟል፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 12 መሠረት፣ ‹‹ንግድ ምልክት ማለት የአንድ ሰው ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ከሌሎች ሰዎች ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ለመለየት የሚያስችል የሚታይ ምሥል›› መሆኑን ክራውን ሆቴል በአቤቱታው ገልጾ ምልክቱ ቃላቶችን፣ ዲዛይኖችን፣ ፊደሎችን፣ ቁጥሮችን፣ ቀለሞችን ወይም ዕቃዎችን ወይም የመያዣዎቻቸውን ቅርፅ ወይም የእነዚያኑ ቅንጅት ሊይዝ እንደሚችል አብራርቷል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 2 (10) ላይም ቀዳሚ መብት እንዳለውም አክሏል፡፡

ጽሕፈት ቤቱም በአዋጁ መሠረት የሲክስ ኮንቲኔንትስ ሆቴልስ ኢንክን ጥያቄ ውድቅ ያደረገ ቢሆንም መልሶ መመዝገቡን ተቃውሟል፡፡

የጽሕፈት ቤቱን ውሳኔ በይግባኝ የተመለከተው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የንግድ ምልክቶቹ እንደማይመሳሰሉ ገልጾ፣ የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ሲክስ ኮንቲኔንትስ ሆቴል ኢንክ ከኢንቨስትመንት አንፃር ሊያበረክት የሚችለው ከፍተኛ አስተዋጽኦ መሆኑን እንደገለጸ መመልከቱን፣ ‹‹ያስቀርባል›› ያለው ሦስት ዳኞች የሚሰየሙበት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ሰነድ ያስረዳል፡፡

የሥር ፍርድ ቤት ሐምሌ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ጽሕፈት ቤቱ ‹‹የሆቴሎቹ ተጠቃሚዎች የማገናዘብ አቅም፣ የትምህርትና የኢኮኖሚ ደረጃቸው ሲታይ ተጠቃሚዎችን ያሳስታሉ ተብሎ ስለማይገመት ሁለቱም የያዙትን የንግድ ምልክት ይዘው ይቀጥሉ፤›› ብሎ የሰጠውን ውሳኔ እንዲፀና ያደረገበት አግባብ፣ ከአዋጅ ቁጥር 501/198 መግቢያ አንፃር ለመመርመር ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ አዟል፡፡

አዋጁ በመግቢያው እንደገለጸው፣ የንግድ ምልክት ምዝገባና ጥበቃ አዋጅ ዕቃ በማምረትና በማከፋፈል ወይም አገልግሎት በመስጠት የንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎችን መልካም ስምና ዝና ለመጠበቅ፣ እንዲሁም በተመሳሳይ ዕቃዎችና አገልግሎቶች መካከል መመሳከርን ለማስወገድ ማስፈለጉንና ሌሎችንም ይገልጻል፡፡

ሰበር ሰሚ ችሎት ለመስከረም 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ተለዋጭ ትዕዛዝ እስኪሰጥ ድረስ የሥር ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ታግዶ እንዲቆይ አዟል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች