Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅ የዲግራ መርሃ ግብር ሊጀምር ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

–   የበረራ መስተንግዶና የቱሪዝም ባለሙያዎችን ለሁለተኛ ጊዜ አስመረቀ

የናሽናል አየር መንገድ እህት ኩባንያ የሆነው ናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅ ለሁለተኛ ጊዜ በበረራ መስተንግዶ፣ በሆቴልና ቱሪዝም ሙያ ያሰለጠናቸውን 191 ተማሪዎች አስመረቀ፡፡ በዲግሪ መርሃ ግብር ማሠልጠን ሊጀምር ነው፡፡

ኮሌጁ ነሐሴ 23 ቀን 2007 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት አዳራሽ ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል በበረራ መስተንግዶ 47፣ በቲኬቲንግና ሪዘርቬሽን 110፣ በኤርፖርት ኦፕሬሽን ሰባት እንዲሁም በካርጎ ኦፕሬሽን ሦስት ሠልጣኞች ናቸው፡፡

ናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅ ከዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበርና ከእንግሊዙ  ኮሜርሺያል ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ያሠለጠናቸውን ተመራቂዎች ከንድፈ ሐሳብ ትምህርት በተጨማሪ የኮሌጁ እህት ኩባንያ በሆነው ናሽናል አየር መንገድ የሥልጠና አውሮፕላኖች አማካኝነት በተግባር የታገዘ ልምምድ መስጠቱን የኮሌጁ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

የኮሌጁ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ካፒቴን አበራ ለሚ ተመራቂዎቹ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የግል አየር መንገዶች በዘርፉ ያሉባቸውን ከፍተኛ የሠለጠነ የባለሙያ እጥረት ለማስወገድና የበለጠ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ ተመራቂዎቹ በአቪዬሽን ሳይንስ የሥልጠና መስኮች ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ውጭ ለሁለተኛ ጊዜ በግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሠለጠኑ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ የመጣውን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ዕድገት ለመደገፍና በዘርፉ አገሪቱ ያላትን አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት በማጠናከር በኩል ተመራቂዎቹ ሚና እንደሚጫወቱም ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በአቪዬሽን መስክ በአፍሪካ ያላትን የመሪነት ሚና አጠናክሮ ለማስቀጠል በመስኩ ባለሙያዎችን በብዛትና በጥራት ለማፍራት የግል ተቋማት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ተቋሙ ተማሪዎች በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ለማሠልጠንና የአካዳሚክ ደረጃቸውን ለማሳደግ በቅርቡ ከሦስት የቻይና ሼንያንግ ኤሮስፔስ ዩኒቨርሲቲ ጋር ባደረገው የመግባቢያ ስምምነት መሠረት ሥልጠናውን ለመጀመር በዝግጅት ላይ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ሼንያንግ ዩኒቨርሲቲ እ.ኤ.አ. በ1952 የተመሠረተና ከ80 ሺሕ በላይ ተማሪዎችን ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ በማስተማር ስም ያካበተ እንደሆነ ናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅ ያሰራጨው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ናሽናል ኮሌጅ ከዚህ ቀደም 141 ተማሪዎችን ማስመረቁ ይታወሳል፡፡

ከውጭ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር የተደረገው ስምምነት የአውሮፕላን አብራሪዎችንና ቴክኒሻኖችን በቅድመና ድኅረ ምረቃ የትምህርት ዘርፎች በጋራ ለማሠልጠንና ሠልጣኞች በኮሌጁ ያገኙትን የንድፈ ሐሳብ ትምህርት በተግባር እንዲማሩ የሚያደርግ ነው፡፡

ከቻይና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር የተጀመረው ትብብር ኢትዮጵያውያንን ወደ ቻይና መላክ ብቻ ሳይሆን የአቪዬሽን የሥልጠና መሣሪያዎችና ቴክኖሎጂዎችን በማስገባት በአገር ውስጥ ሥልጠናውን ለማካሄድ ለተያዘው ዕቅድ የላቀ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሏል፡፡

ከተቋቋመ አራት ዓመታትን ያስቆጠረው ናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅ፣ ከተቋቋመ ጀምሮ በበረራ መስተንግዶ፣ በቲኬቲንግና ሪዘርቬሽን፣ በካርጎ ኦፕሬሽን፣ ኤርፖርት ኦፕሬሽን እንዲሁም በሆቴልና ቱሪዝም መስክ ሥልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

ኮሌጁ ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የዕውቅና ፈቃድ እንደተሰጠው የኮሌጁ መረጃ ይጠቁማል፡፡

ኮሌጁ በአፍሪካ በአቪዬሽን፣ በቲኬቲንግና ሪዘርቬሽን የሥልጠና መስኮች በበርካታ ወጣቶች ደረጃውን የጠበቀ ጥራት ያለው ዓለም አቀፍ ሥልጠና በመስጠቱ ከዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር የ2015 “Africa’s top performing IATA Authorized training Center” የሚል ሽልማት መቀበሉን የኮሌጁ ዲን አቶ ገዛኸኝ ብሩ አስታውሰዋል፡፡

በቅርቡም ኮሌጁ በበረራ ስምሪት፣ በአውሮፕላን ጥገናና በሌሎች የሥልጠና ዘርፎች ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዕውቅና ለማግኘት ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ አስታውቋል፡፡ በቀጣዩ ዓመት በሆቴልና ቱሪዝም የትምህርት መስኮች በዲግሪ መርሐ ግብር እንዲሁም በጉምሩክ ሥነ ሥርዓት አፈጻጸም፣ በበረራ አስተላለፊነትና ኦፕሬሽን የሥልጠና መስኮች ተማሪዎችን ለመቀበል መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች