Thursday, June 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ጉብኝትና የአጎዋ አቅጣጫዎች

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለፈው ሳምንት ውስጥ ሁለት ዓበይት ክንውኖች ከአሜሪካ ተከናውነዋል፡፡ የቅርብ ክንውን የሆነው ስምንት የኮንግረስ አባላት በአዲስ አበባና በአቅራቢያ ከተሞች ጉብኝት ማድረጋቸው ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ብሎም በአሜሪካ ባለሥልጣናት ከቀረጥና ከኮታ ነፃ ለአፍሪካ በተሰጠው የንግድ ዕድል አጎዋ ተብሎ በሚጠራው የነፃ ገበያ ለመጪዎቹ አሥር ዓመታት መራዘሙና አንድምታዎቹን በሚመለከት ማብራሪያ የተሰጠበት ሌላኛው ክንውን ነው፡፡

ከአሜሪካ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው የስምንቱ የኮንግረስ አባላት ጉብኝት በአሜሪካና በኢትዮጵያ መካከል ባለው የልማት ትብብር ላይ ያጠነጠነ ነው፡፡ በመሆኑም የኮንግረስ ልዑካኑ በአሜሪካ የልማት ድጋፎች የሚተገበሩ ፕሮጀክቶችን ከመጎብኘት በተጨማሪ ከአገር ውስጥ የሲቪል ማኅበረሰብ አባላትና ከአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ጋር መነጋገራቸውን ኤምባሲው አስታውቋል፡፡ ልዑካኑ ጉብኝት ካደረጉባቸው ኩባንያዎች መካከል በፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አነሳሽነት በአፍሪካ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ላይ በሚንቀሳቀሰው የፓወር አፍሪካ ኢኒሺዬቲቭ ድጋፍ የተደረገለት ይገኝበታል፡፡

ከኢትዮጵያ ባሻገር በኬንያና በፊሊፒንስ የሚንቀሳቀሰው ሰንትራንስፈር ኢትዮጵያ የተባለው ኩባንያ፣ በኢትዮጵያ ከዋናው የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ሥርጭት ውጭ ለሆኑና መደበኛ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ለማያገኙ ነዋሪዎች አማራጭ የታዳሽ ኃይል አቅርቦት ለመስጠት እየሠራ ይገኛል፡፡ ይህ ተቋም ከፓወር አፍሪካ የአንድ መቶ ሺሕ ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ማግኘቱም ይታወሳል፡፡ ኩባንያው በተለይ በፀሐይ ኃይል የሚሠሩ የቤት ውስጥና ለንግድ አገልግሎት የሚውሉ የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂዎችን ከማቅረብ ባሻገር የምሕንድስናና የተከላ እንዲሁም የጥገና አገልግሎቶችን የሚሰጥ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር በፀሐይ ኃይል ምርቶችን በመገጣጠም እየሠራ የሚገኝ ሲሆን፣ የኩባንያው ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ዮና ወርቄ ለኮንግረስ አባላቱ ማብራሪያ መስጠታቸው ታውቋል፡፡

ከዚህ ኩባንያ ባሻገር ማማ ፍሬሽ እንጀራም በአሜሪካ ድጋፍ ከሚደረግላቸው አንዱ ኩባንያ ነው፡፡ ይህ የንግድ ተቋም ሪኒው ግሎባል ኢምፓክት ኤንጅል ኔትወርክ ከተባለው የአሜሪካ ተቋም የገንዘብ ድጋፍ በማግኘቱ ማስፋፊያ በማድረግ የማምረት አቅሙን በሦስት እጥፍ ለማሳደግ መቻሉን ለአሜሪካ ልዑካን አሳውቋል፡፡ ማማ ፍሬሽ በዓለም ዕውቅናው እየናኘ የመጣውን እንጀራ በአሜሪካና በአውሮፓ ገበያዎች ለማፋፋት እንደረዳው አብራርቷል፡፡ ከዚህ ባሻገር የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችን የሚያመርተው ፓዮኒር ዘር ማቀነባበሪያ፣ ዱፖንት የተባለው የአሜሪካ ተቋም ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (ዩኤስኤአይዲ) ጋር በአንድነት ሆነው መናገሻ አካባቢ ለሚገኘው የዘር ተቋም ከፍተኛ የበቆሎ ዝርያ ለማውጣት የሚችልበትን እገዛ በማድረጋቸው በኮንግረስ አባላቱ ከተጎበኘ ተቋማት መካከል ሆኗል፡፡ የጤና ኬላ፣ በአዲስ አበባ የሚገኘው ዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም (አይኦኤም) ጉብኝቱ ካካተታቸው መካከል ይገኙባቸዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር በአገሪቱ የልማት እንቅስቃሴ ላይ የግሉ ዘርፍ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ከጎበኙት ልዑካን ባሻገር፣ በቅርቡ በአጎዋ መራዘም ላይ የቪዲዮ መግለጫ መሰጠቱ ይታወሳል፡፡ በአዲስ አበባ፣ በአቡጃ፣ በዳካር፣ በሌጎስ፣ በሊቨርቪል፣ በሎሜ እንዲሁም በሉዋንዳ የሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎች በኩል ለመገናኛ ብዙኃን ከዋሽንግተን በተሰጠው መግለጫ መሠረት፣ በአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትሯ ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ እንዲሁም በአሜሪካ ረዳት የንግድ ተወካይ ፍሎሪ ሊዘር አማካይነት ለአፍሪካ አገሮች የተሰጠው ነፃ የገበያ ዕድል ለመጪዎቹ አሥር ዓመታት መራዘሙንና የሚኖሩት አንድምታዎችን በማስመልከት ገለጻዎች ተሰጥተዋል፡፡ ለአሥር ዓመታት የተራዘመው አጎዋ በአፍሪካ ብልጽግና፣ በገበያዎች ክፍት መደረግ፣ በአካታችና አሳታፊ ልማት፣ በጠንካራ የአካባቢያዊ ትስስሮችና በመልካም አስተዳደር መስኮች ላይ ትኩረት እንደሚሰጥ የገለጹት ግሪንፊልድ፣ የአሜሪካ የንግድ ሰዎች አፍሪካ ውስጥ ኢንቨስት እንዲያደርጉ መተማመንን የሚፈጥር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ረዳት የንግድ ተወካይዋ ፍሎሪ ሊዘር፣ ለመጪዎቹ አሥር ዓመታት በተራዘመው አጎዋ ፕሮግራም የመሳተፍ ዕድል ለማግኘት የሚችሉ 39 አገሮች እንዳሉ ጠቅሰዋል፡፡ ላለፉት አሥራ አምስት ዓመታት የቆየው አጎዋ 4.4 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ዕቃዎችን ወደ አሜሪካ ለመላክ እንዳስቻለ ጠቅሰው፣ የንግድ አቅም ግንባታን ጨምሮ ሌሎች የቴክኒክ ድጋፎች ለአፍሪካ አገሮችና ላኪዎች እየተሰጠ እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡

አዲሱ የአጎዋ ዕድል ምን የተለዩ ይዘቶች እንዳካተተ ለተጠየቁት ሲመልሱ ሊዘር እንዳብራሩት የአሥር ዓመቱ አጎዋ ከጨመራቸው አዳዲስ ይዘቶች መካከል የሌላ አገር የሥሪት ሕጎችን በማሻሻል ከድንበር ውጭ የምርት ሥርዓት የሚኖራቸው ምርቶች ወጪ እንዲካተት መፍቀዱ አንዱ ነው፡፡ በአንድ አገር የተመረተና የሌሎች አገሮች የምርት ግብዓት የተካተተበት ምርት አሜሪካ እንደምትቀበልና ለዚህም ግልጽነት የሰፈነበት አሠራር መዘርጋቷን ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን ባለፉት አሥራ አምስት ዓመታት ሲተገበር የቆየው አጎዋ ለታዳጊ የአፍሪካ አገሮች ምን ፋይዳ ነበረው የሚል ጥያቄም ተነስቷል፡፡ ግሪንፊልድ ለዚህ ጥያቄ የሰጡት ምላሽ ከንግድ አንድምታው ባሻገር ፖለቲካዊ ፋይዳ እንደነበረውም ነው፡፡ በፖለቲካዊ ይዘቱ የአፍሪካ አገሮች የአጎዋ ተጠቃሚ ለመሆን ማሟላት ከሚጠበቅባቸው መካከል የሰብዓዊ መብቶችን፣ የፕሬስ ነፃነትንና የሠራተኞችን መብት እንዲያከብሩ መጠየቅ ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው፡፡ እነዚህ መብቶች በምን ደረጃ በአፍሪካ አገሮች ዘንድ እንደተከበሩ ማብራሪያው ባያካትትም ለአጎዋ አባልነት ግን እንደመሥፈርት መቀመጣቸው ተጠቅሷል፡፡

ከዚህ ይልቅ በነፃ የንግድ ዕድሉም ቢሆን የሚጠበቀውን ያህል ያልተጠቀሙ አገሮች በመኖራቸው ስለዚህስ ምን ይሉ እንደሆነ ባለሥልጣናቱ ተጠይቀው ነበር፡፡ ሊዘርም ሆኑ ግሪንፊልድ እስካሁን ሲተገበር የቆየው አጎዋ በርካታ የንግድ ተቋማትንና አገሮችን ተጠቃሚ ሲያደርግ እንደቆየ ያምናሉ፡፡ ይህም ሆኖ የአፍሪካ የንግድ ተቋማትም ሆኖ መንግሥታት በጋራ የሚሠሩባቸው ተጨማሪ ዓመታት እንዳገኙ አስገንዝበዋል፡፡ ሌሎችም በርካታ አጎዋ ነክ ውይይቶችና ገለጻዎች የተደረጉበት ማብራሪያ የመጪዎቹን አሥር ዓመታት ብሩህነት ለማመላከት ሞክሯል፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ አገሮች በተሰጣቸው የነፃ ገበያ ዕድል እንደሚፈለገው ሳይጠቀሙ ቆይተዋል፡፡ በአሜሪካ ገበያ ትልቅ ድርሻ ይይዛል ተብሎ ትልቅ ግምት የተሰጠው የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው የውጭ ኩባያዎች እስኪቀላቀሉት ድረስ አንቀላፍቶ ቆይቶ ነበር፡፡ ከቱርክም ከህንድም የመጡት ኢንቨስተሮች ጥቂትም ቢሆን ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ያደረጓቸው ጥረቶች የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪውን በሚጠበቀው መጠን ለማራመድ ብቁ መንገድ ይቀራቸዋል፡፡ የቆዳ ዘርፍና የጫማ ምርቶች እንዲሁም የቆዳ አልባሳትና ሌሎች ምርቶች ተስፋ የተጣለባቸው ምርቶች ሲሆኑ የአግሪ ቢዝነስ መስኮችም ለአጎዋ ገበያ ትልቅ ግምት የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት ኢትዮጵያ ባለፉት አሥራ አምስት ዓመታት ውስጥ በአጎዋ በኩል ከላከቻቸው ምርቶች በአማካይ ከ40 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማግኘት አልቻለችም፡፡

የአሜሪካ ከፍተኛ የንግድ ባለሙያና በኢትዮጵያ የአሜሪካ የውጭ ንግድ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ታንያ ኮል ከጥቂት ጊዜ በፊት ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ በአጎዋ በኩል ከምትልካቸው ምርቶች ቦይንግ አውሮፕላንን ጨምሮ በዚህ ዓመት ብቻ ከ1.6 ዶላር በላይ ስታገኝ፣ ኢትዮጵያ ግን ከ225.6 ሚሊዮን ዶላር የዘለለ ገቢ አላገኘችም፡፡ በመሆኑም ምርቶችን በገፍ ማምረትም ሆነ ወደ አሜሪካ መላክ ፈተና ሆኖ ይገኛል፡፡ ለሚቀጥሉት አሥር ዓመታት አጎዋ በመራዘሙ ግን እየተስፋፉ ያሉት የቆዳና የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ትልቅ የገበያ ዕድል እንደሚያገኙ ይጠበቃል፡፡ በአንፃሩ አሜሪካ ከታሪፍና ከኮታ ነፃ የገበያ ዕድል ለእስያ አገሮች ‹‹ትራንስ ፓስፊክ ፓርትነር ሺፕ›› በተሰኘው ማዕቀፍ ውስጥ ተመሳሳይ የነፃ ገበያ ዕድል መስጠቷ ግን በርካታ ጨርቃ ጨርቅ አምራቾችን ሥጋት ውስጥ የጣለና የአፍሪካን የተወዳዳሪነት አቅም የሚፈታተን ተብሎለታል፡፡ የሥጋቱ ምክንያት ደግሞ በእስያ አገሮች ውስጥ የማምረቻ ወጪዎች ከአፍሪካ ይልቅ ዝቅተኛ መሆናቸው ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች