Tuesday, February 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መተካካት ብርቅ ሆነ እንዴ?

ሰላም! ሰላም! አዲስ ነገር ናፋቂ ሁላ፣ “ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለም” ቢባል አልሰማ እያለ አስቸግሯል ይሉኛል። እነማን እንደሆኑ አልነግራችሁም። ለነገሩ ልንገራችሁ ብልም ተላላፊና ተጣጣፊው በበዛበት ጊዜ ማን ብዬ እነግራችኋለሁ? የምሬን እኮ ነው! ቆይ እኔ ምለው? አሮጌ አቁማዳችንን እያየ ሰው ፀሐይ ድረስ የሚጓዘው ምን ነክቶት ነው ግን?  በልቤማ (ልባችሁ እስኪጠለፍ ቶሎ ቶሎ ነገር ቋጥሩበት) ‘ከሰሃራ በታች አዲስ ነገር የለም በሏቸው’ ልበላቸው ይሆን እያልኩ ስፈራ ስቸር ከአፌ አመለጠኝ። እንደፈራሁት ይህቺም በአቅሟ ሸውራራ ፖለቲካዊ ፍቺ አላት ተብላ ነው መሰል ሰዎቹ ተመልሰው አልመጡም። ይብላኝ ለነሱ እንጂ እኔስ በውኃ ቀጠነ መቆራረጥን ለምጄዋለሁ። ትቼዋለሁ ስላችሁ።

ብቻ ጡር አልፈራ እያልን እንዳልኩት በውኃ ቀጠነ መቆራረጥ ስናበዛ ነው መሰል ከእናአካቴው ዝናቡም ‘ላሽ’ አለ። ሰማዩን ‘ላሽ’ በልቶት ይሁን፣ ተፈጥሮ ያሳጣችው መንግሥታችን እንደሚያስገነዝበን ‘ኤልኒኖ’ የሚሉት ጎረምሳ ንፋስ ብቻውን አባሮት፣ ብቻ ይኼው የአዲስ አበባን ነዋሪ ያህል ወገን የዕርዳታ ያለህ አለ ተባለ። “እግዚኦ” አሉ ባሻዬ። እዚህ ቆም ላድርጋችሁና አባባ ጃንሆይ ሊናገሩት ይችላሉ ብዬ ያሰብኩትን ልጋብዛችሁማ። ሁሌ ፍሪዳ መገባበዝ ለምዶ የምናብ ጭውውት ልጋብዛችሁ ማለቴ የደበረው ካለ፣ ዛሬም ድርቅ የሚከሰትባት ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚኖር ቆንጠጥ አርጋችሁ አስረዱልኝ። ደግሞ አደራ ቀኝ እጁን ሰጥቶታል ብላችሁ ከቁንጥጫው በላይ እንዳትሄዱ። ስንዝር ሲሰጡት ዕርምጃ የሚመትረው እኮ ነው አንድም ያደረቀን እናንተ?

እናላችሁ ጋዜጠኛው ጥያቄዎቹን ለማቅረብ ተሰናድቶ ተቀምጧል። “ጃንሆይ! አሁንም በእርስዎ የአስተዳደር ዘመን ሲከሰት እንደነበረው በአገራችን ድርቅ ተከስቷል። ዝናብ ከድቶናል። ምን አስተያየት አለዎት?” ሲል ይታያችሁና ካሜራው ወደ አባባ ጃንሆይ ሲዞር . . . ግርማቸው ከቅንድባቸው እንደጀመረ እስከ እግር ጥፍራቸው በላያቸው እየፈሰሰ ይመልሳሉ። “እኛ ድሮም ይህን ልቦናችን ያውቀዋል። አንተ የዝናብ መክዳት ያስገረመህ ትመስላለህ። ክህደትን እስከ ጥግ እንደ እኛ የተጓዘባት የለም። ዘለህ በማትነካው ሰማይ ክህደት አብዝተህ አትገረም። የቆምክበት ምድርም አድጦ የሚጥልህ ቀን አለና መገረምህን ቆጥበው፤” ቢሉት ጋዜጠኛው አቋርጦ፣ “ያው ከእርስዎ የአስተዳደር ዘመን የሚለየው ዛሬ በበልግና በክረምት የዝናብ እጥረት ምክንያት ለተከሰተው ድርቅ ፀሐዩ መንግሥታችን ሙሉ ለሙሉ ዕርዳታ ፍለጋ እጁን አልዘረጋም። ለተጎጂ ወገኖች ከካዝናው የሸፈነው ዕርዳታ ቀላል አይደለም። ምን ይላሉ?” አለ ጋዜጠኛው ጃንሆይን በነገር ወጋ እደያረገ፡፡

ጃንሆይ ሽንቆጣውን ልብ ብለው፣ “ድርቅ ያለ፣ የነበረና ወደፊትም የሚኖር ነው። ቁም ነገሩ እሱ ሳይሆን እግረ እርጥብ መሆኑ ላይ ነው። ፈጣሪ በቃችሁ ስላለ ወሎ ሰበብ ሆና ከሥልጣናችን ወረድን እንጂ፣ በየሄድንበት ከአውሮፕላን ሳንወርድ ጠብታ የማያውቁ ምድሮች በጎርፍ ተጥለቅልቀዋል። ትዕዛዙ አንዴ ከተቆረጠ ግና እንኳን ድርቅ ትንታ አንፈራፍሮ ከማይቀርልህ ጉድጓድህ ያስተኛሃል። ምነው ግን የዛሬው ፀሐዩ መንግሥታችሁ ለዕርዳታው ማዋጣቱ አስገረመህ? እኛ እኮ እልፍ ጊዜ ግብር ያበላን፣ ለወዳጆቻችን ለእንግሊዞች ሳይቀር በመርከብ አስጭነን ስንዴ የላክን ሰዎች ነን፤” ሲሉት ሥርጭቱ ተቋርጦ፣ ‘ፕሮግራሙ የተላለፈው አባል ያልሆነ ቴክኒሻን ገብቶብን ነው’ የሚል ታነባላችሁ። ይኼን ሰምቶ ደግሞ መንግሥት ግብር ካላበላ የሚል አይጠፋማ። እንደ ወረደ እየገለበጥን መሰለኝ ያለመግባባታችን ዕድገት የጨመረው። እንዲያው እኮ!

ይኼውላችሁ ረስቼው። መቼ ዕለት ማን ስልኬን አንደሰጠው አላውቅም፡፡ አንድ ባለፀጋ የመንደራችን ነዋሪ  ደወለልኝ። “አቤት” ልለው ሄድኩ። “ና ላሳይህ” ብሎ እሱ ከሚኖርበት ባለሦስት ፎቅ መኖሪያ ቤቱ ጀርባ አራት በአራት የሆኑ ሁለት ክፍሎች ከእነ መታጠቢያ ክፍላቸው ሠርቷል። መቼም የዘመኑ ሰው አጣጥሞ የሚኖረው ዕድሜ እንዳለውና እንደሌለው ሳያረጋግጥ የቤት ባለቤትነትን ማረጋገጥ ይቀናዋል። ገንዘብና ጉልበቱን መጥምጦ ቤት ሲሠራ ነፍሱን አያውቅም። ባሻዬ ስለቤተ ሠሪው መብዛት እያነሳሁ አንዳንድ ገጠመኘን ሳጫውታቸው፣ ‘ፍካሬ ኢየሱስ’ (ዘወትር ከእጃቸው አይጠፋም ስላችሁ) ተፈጻሚነት እያገኘ እንደሆነ ልብ በል ይሉኛል። “ልጅ አንበርብር ልብ ብለህ አድምጠኝ። በስምተኛው ሺሕ ቤተ ሠሪ ይበዛል። ሠርቶ የሚኖርበት ግን ጥቂት ነው’ ይላል። እኔ ወድጄ መሰለህ የሰማይ ቤቴ ላይ ያደፈጥኩት?” ይሉኛል። እንዲህ ሲሉኝ እሳቸውም ያው ዞረው ዞረው የሚደላደሉበት ርስት ዕጣ ጠባቂ እንደሆኑ ልነግራቸው አስብና መልሼ እተወዋለሁ። የሰማይ ሆነ የምድር ከቤት በላይ ምን አለ? ቤት ሲባል የሚሰማችሁ ባለኮንደሚኒየም መሆን አለባችሁ መቼስ!

  በኪራይ አከራይ ጣጣ ያልተንገበገበ ምኑን ያውቀዋል? የሚያውቀው ያውቀዋል። በቀደም ከባሻዬ ልጅ ጋር ስለዚህ ባለፀጋ ሰውዬ አንስተን፣ “ቤት ቢሠራ አይደክመውም?” ብለው፣ “እኛ አለን አይደል  እንኳን መሥራት መሳል የጠፋብን?” አለኝ። ጥሎብኝ ሳላስጨርስ አለቀውም አይደል? “እንዴት?” ስለው፣ ‹‹አንድ ጩጬ ልጅ በሥነ ጥበብ አስተማሪው፣ ‘ነገ የሚታረም የቤት ሥዕል ሳልና ና’ ይባላል። በሥዕል ደብተሩ ላይ አሽሞንሙኖ ሥሎ ይወስዳል። አስተማሪው ሥዕሉን አተኩሮ እያየ ‘ምንድነው ይኼ? ይኼ እኮ ቁም ሳጥን እንጂ ቤት አይደለም፤’ አለው። ልጁ ምን ቢል ጥሩ ነው? ‘እኛ የምንኖረው እዚህችኛዋ ተከፋች ውስጥ ነው’ አይለው መሰለህ?” ብሎ በሳቅ አፈረሰኝ። ስለዘመኑ ልጆች እንደወረደ የመጻፍና የመሳል ብሒል እያሰብኩ ግርም አለኝ። ልጅነቴ ትዝ አለኝ።

ሥዕል አስተማሪ እንደነበረን ባላስታውስም ወፍ መሳል ይወድ የነበረ አብሮ አደጌን አስታወስኩት። ታዲያ አንድ ቀን ወፍ ማልመድ አለብኝ ብሎ እንዳበደ ተነስቶ አላስቆም አላስቀምጥ ይላል። ለሚያለምዳቸው ወፎች ቤት ልሥራ ብሎ ማገዝ ጀመርኩ። ቁመቱ ሜትር ከሃምሳ የሚሆን ወርደ ጠባብ ሳጥን ነገር አበጀንና የሚችለውን ያህል ውስጡን ጣውላ ረበረብንበት። የሚያስቀው ሥራችን የበሩ ነበር። ለእያንዳንዱ ክፍልፋይ አንዳንድ መዝጊያ እንደማበጀት በቁሙ ሜትር ከሃምሳ በር ገጥመን። ኋላማ ያልተሞሸረውን ወፍ ከላይ አስገብተን ጥንዶቹን ከሥር ስናስገባ ያ ከላይ ያስገባነው ከመቼው እንደሚበር እግዜር ይወቀው። በሩ የሚዘጋው አንዴ! ዋ ልጅነት። ኋላ ዘዴ አመጣሁ አለና የሠፈሩን ውሪ ሰበሰበው። እያንዳንዳችን አንዳንድ ወፍ በየርብራቡ ካጎርን በኋላ አንዱ ቶሎ ሊደረግምባቸው ተስማማን። የአስተኳሽና ተኳሽ ጨዋታ በሉት። እህ? አጉጎረን እንዳበቃን ያ ሁሉ ውሪ “ዝጋው!” ብሎ ቢጮህ በርግገው ክንፍ የዘረጉት ወፎች ሄደው ከመዝጊያው ጋር ተላተሙ። የሞተው ሞተ፣ የተጎዳው ተጎዳ። እና እላለሁ . . . እንኳንም የዚያ ወዳጄ ቤት አሠራር እንደ ሞዴል አልተወሰደ እንጂ ምድረ ባለኮንዶሚኒየም አልቆለት ነበር። ኧረ ቀልዴን ነው ብሩና ቤቱ ይገኝ እንጂ ደግሞ በሩ ሊያሳስበን? አይደለም አራት አርባ ፎቅ ቢሆን እንዘላለን። ድፍረቱ በእጃችን ዕድሜ ለኑሯችን!

ይኼን ሁሉ ያወራሁት አሁን ቤት አከራይልኝ ስላለኝ ሰውዬ ላጫውታችሁ ነበር። የእኔ ነገር። “ስንት ይባላሉ?” አልኩት። “ከ4,000 ብር በታች አይከራዩም . . .” ሲለኝ የለሁም። “እኮ ይህቺ ክፍል?” ብዬ ስጮህበት (ሳይታወቀን የምንጮኸው ጩኸት በራሱ በኃይል መቆራረጥ ላይ ድርሻ ሳይኖረው አይቀርም ብዬ እያሰብኩ ነው ሰሞኑን) “ምነው አንተ ግባበት አልኩህ እንዴ? ምን ያስጮሃል?” መልሶ ጮኸብኝ። እንዲያው አንዳንዱ አከራይ ደግሞ የተቀደሰ የእምነት ሥፍራ እንጂ ቤት የሚያከራይ አይመስልም እኮ። “እንኳንም አድባራት የግል ይዞታ አልሆኑ?” ያለኝ ወዳጄ ትዝ አለኝ። በአጭር የመክበር ሩጫ የመተዛዘን አንገት እንዴት ገዝግዞ ጨረሰው እናንተ። የምሬን እኮ ነው። የገንዘብ ፍቅር እኮ አንዳንዱን ጀላቲ በኮንቴይነር አስጭኖ እስከማስመጣት ሁሉ ያሳስበዋል አሉ። አንዴ ከክፍለ አገር ሊጠይቀኝ አንድ ዘመዴ ይመጣል። አዲስ አበባን ሲያይ የመጀመርያ ጊዜው ነበር። እናም መንገድ ላይ ጀላቲ ሲሸጥ ያይና ሳላየው ቀስ ብሎ ሄዶ ሻጯን ስንት ስንት ነው አላት። የብር አሥር ስትለው አንዱን በሁለት ብር ብሸጠው ብሎ ያስብና የሃያ ብር ገዝቶ ሳይነግረኝ ሄዷል። እዚህ ጫንጮ ሳይደርስ ሞሟለታ። አገሩ ገብቶ የሆነውን በስልክ ሲያጫውተኝ ሆዴ እስኪታመም ነበር የሳቅኩት። ጊዜ ያጀገናቸው ብልጥ ነን ባዮች ግን በደካማ ጎናችን እየገቡ ሲበዘብዙን ግን አያንገበግብም? ኧረ ያንገበግባል!

በሉ እንሰነባበት። ውዷ ማንጠግቦሽና እኔ የሆድ የሆዳችንን እያወራን ቴሌቪዥን ስናይ መብራት ድርግም ብሎ ጠፋ። ደርሶ የጨለመባት ማንጠግቦሽ ተናዳ የምትይዝ የምትጨብጠው ስታጣ ሻማ ለመግዛት ወጣሁ። ሱቅ ሳልደርስ የባሻዬ ልጅ ደውሎ የዘወትር መገናኛችን ወደሆነችው ግሮሰሪ ብቅ እንድል ነገረኝ። ጥቂት ሳመነታ ቆይቼ ወደ ግሮሰሪዋ ተጣደፍኩ። ስደርስ ታዳሚው ቴሌቪዥን ላይ አፍጥጦ ሩጫ ያያል። የገንዘቤ ዲባባን ጥንካሬና ውጤት እያነሳ ያወካል። አንዱ፣ “ምነው በወንዱም በሴቱም እሷ ብቻ በሮጠችልን?” ሲል፣ “ተው እንጂ የሌላውም ጥረትና ላብ ይታይህ እንጂ፤” ይላል ወዲያ ያለው። “ሁሉም የራሱን ሩጫ ተግቶ ቢሮጥ ይህቺ የጀግኖች አገር የት በደረሰች?” ሲል ከባሻዬ ልጅ አጠገብ የተቀመጠው፣ “ኤድያ በየት በኩል? በመመሳሰልና በመጠጋጋት ታጥረን መተካካትና መተጋገዝ ከየት ይምጣ?” አለ አፉ መያያዝ የጀመረ ጠጪ። ይኼን ጊዜ እዚህም መብራት ድርግም። “እሰይ! ገላገለን፤” ሲል አዲስ ድምፅ “ከምን?” ብሎ በራፉ አካባቢ የተቀመጠ ሰው አጉረመረመ። “ከመሳቀቅ ነዋ። የነበረው መልሶ እየመጣ፣ የዘለልነው መሰናክል መልሶ እንደ አዲስ ፈተና እየሆንብን ተሳቀን ሞትን እኮ? ነገራችን ሁሉ የሚያምረው ወረቀት ላይ፣ ኑሯችን አፈር፣ ዘለልን ስንል መሰበር፣ ፊት ለፊት ስንናገር ‘ነብር አየኝ በል’ . . .” እያለ ሲቀጥል አንዱ “በቃ በቃ!” ብሎ አቋረጠው፡፡ “ማለት የፈለግከውን ጨለማ ውስጥ ሆነህም ለማለት ትፈራለህ? ‘የምንተካካው በሞትና በውልደት ነው? ወይስ በቁም ነው?’ አትልም? ምን ዳር ዳር ትዞራለህ?” ብሎ በሻማ ብርሃን ሒሳብ ከፍሎ ወጣ። እኛም ነገር ሳይመጣ ብዙ ሳንጠጣ ውልቅ። እውነትም የምን ዳርዳርታ ነው? መተካካት ብርቅ ነው እንዴ? ትውልድ እየተቀባበለ የሚያልፈው እየተተካካ አይደለም እንዴ? ሆሆ? መልካም ሰንበት!     

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት