የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊው የዲአፍሪክ ሆቴል ባለቤት ሐሰተኛ ሰነድ በመገልገል ወንጀል ተጠርጥረው ነሐሴ 18 ቀን 2005 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ውለው ታስረው ካደሩ በኋላ፣ በሐሴ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው በ200 ሺሕ ብር ዋስ እንዲለቀቁ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ፡፡
የሆቴሉ ባለቤት አቶ ብሥራት ሰይፉ በ200 ሺሕ ብር ዋስ እንዲፈቱ ትዕዛዝ የሰጠው የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ተረኛ ችሎት ነው፡፡ አቶ ብሥራት ሊታሰሩ የቻሉት፣ ‹‹ከ17 ዓመታት በፊት አባታቸው ዲአፍሪክ ሆቴልን ለእሳቸው ተናዘዋል›› የተባለበት ሰነድ የሐሰተኛ ሰነድ (ፎርጅድ) ነው ተብሎ ነው፡፡
አቶ ብሥራት በጠበቆቻቸው አማካይነት ለፍርድ ቤቱ ሰነዱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ትክክለኛነቱ የተረጋገጠ መሆኑን፣ እስከ ሰበር ችሎት ድረስም ክርክር ያደረጉበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
መርማሪ ፖሊሶች ሰነዱን ፍርድ ቤቱ እንዲያይላቸው በመጠየቅና ወንጀሉም ከፍተኛ መሆኑን በማስረዳት የምርምራ ጊዜ እንዲሰጣቸው የጠየቁ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ አልተቀበላቸውም፡፡ አቶ ብሥራት በ200 ሺሕ ብር ዋስ እንዲለቀቁና ከአገር እንዳይወጡም ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡