– በሕገወጥ መንገድ ተይዞ የነበረ 500 ካሬ ሜትር ቦታ ለመንግሥት ተመለሰ
የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በ2008 በጀት ዓመት ከሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ነሐሴ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ በሙስና ተጠርጥረው በክስ ሒደት ላይ ከሚገኙ ሰዎች፣ 28 ቤቶችን በፍርድ ቤት ማሳገዱንና ስድስቱ ቤቶች በዱባይና በደቡብ ሱዳን ጁባ ከተማ የሚገኙ መሆናቸውን ገለጸ፡፡
ኮሚሽኑ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንደገለጸው አራት ቤቶችን በዱባይ፣ ሁለት ቤቶችን ደግሞ በደቡብ ሱዳን ጁባ ከተማ ውስጥ አሳግዷል፡፡ ቀሪዎቹ 22 ቤቶች በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የሚገኙ መሆኑንም ኮሚሽኑ አክሏል፡፡
በዱባይና በጁባ ከተማ የታገዱት ቤቶች፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጁባ ቅርንጫፍ ላይ ተፈጽሟል በተባለ የሙስና ወንጀል ከተጠረጠሩ የባንኩ ሠራተኞችና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ “ወርቅ ነው” በማለት ባሌስትራ በማቅረብ በአጭበረበሩ ግለሰቦች የተገዙ መሆናቸውን፣ ቀሪዎቹ ቤቶች ደግሞ በሌላ የሙስና ወንጀል ድርጊት የተጠረጠሩ ግለሰቦች መሆናቸውን ኮሚሽኑ አብራርቷል፡፡
ኮሚሽኑ በአዲሱ በጀት ዓመት አንድ ወር ተኩል ጊዜ ውስጥ ከ3.2 ሚሊዮን ብር የሚበልጥ ገንዘብና በየካ ክፍለ ከተማ በአንድ ግለሰብ በሕገወጥ መንገድ ተይዞ የነበረ 500 ካሬ ሜትር ቦታ ለመንግሥት ማስመለሱን ገልጿል፡፡ በተለያዩ የሙስና ወንጀል ድርጊቶች ጋር በተያያዘ 21 የግንባታና 35 የቤት አውቶሞቢሎች፣ 56 የተለያዩ ዓይነት ተሽከርካሪዎች፣ የአክሲዮን ገንዘብን ጨምሮ ከ53 ሚሊዮን ብር በላይና አንድ የግል ድርጅት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማሳገዱን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
የግንባታ ማሽነሪዎች፣ የተለያዩ ተሽከርካሪዎችና ገንዘብ ያሳገደው በሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ ክስ ከተመሠረተበት የእስራኤሉ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ትድሃር ሲሆን፣ አብዛኛው ገንዘብ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደቡብ ሱዳን ጁባ ቅርንጫፍ ሠራተኞች ከነበሩት ተጠርጣሪዎች መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡