Thursday, March 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊእነ አቶ መላኩ ፈንታ በሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ውሳኔ ላይ ተቃውሞ...

እነ አቶ መላኩ ፈንታ በሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ውሳኔ ላይ ተቃውሞ አቀረቡ

ቀን:

አዲሱ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 የመሸጋገሪያ ድንጋጌ አንቀጽ 182 ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22(2) ጋር እንደሚጋጭ በመግለጽ፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል በማለት ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ተልኮ ጉባዔው “አይጋጭም” ብሎ ውሳኔ መስጠቱን በመቃወም፣ እነ አቶ መላኩ ፈንታ አቤቱታ አቀረቡ፡፡

ጉዳዩን እየመረመረ የሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት እነ አቶ መላኩ የተከሰሱባቸው የወንጀል ድርጊቶች በአዲሱ የጉምሩክ አዋጅ በአስተዳደር የሚያልቁ መሆናቸውን የደነገገ ቢሆንም፣ አንቀጽ 182 ግን ‹‹አዲሱ አዋጅ በሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት የተጀመሩ ጉዳዮች በነባሩ አዋጅ እንዲቀጥሉ፤›› ማለቱ፣ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22(2) ጋር እንደሚቃረን ተከሳሾቹ ገልጸዋል፡፡ አጣሪ ጉባዔው የተጠቀሰው አንቀጽ ትርጉም እንደሚያስፈልገው ወይም እንደማያስፈልገው ከመግለጽ ባለፈ፣ በፍርድ ቤቱ ሥራ ውስጥ በመግባት ከሥልጣኑ ውጪ መሥራቱን በአቤቱታቸው ጠቁመዋል፡፡

ጉባዔው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62(2) መሠረት ሕገ መንግሥት የመተርጎም ሥልጣን የተሰጠው የፌዴሬሽን አካል መሆኑን የገለጹት ተከሳሾቹ፣ ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሠራር ወይም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ፣ ከሕገ መንግሥቱ ጋር እንደሚቃረን የሚገልጽ ጥያቄ ሲቀርብለት ተቀብሎ መተርጎም ወይም ውድቅ ማድረጉን ለአቅራቢው በጽሑፍ ማሳወቅ እንዳለበት፣ በአንቀጽ 84 (1)(3)፣ ጉባዔው በተቋቋመበት አዋጅ ቁጥር 798/2005 አንቀጽ 3(1) እና 12(1) (ሀ) መደንገጉን አብራርተዋል፡፡

እንደ ተከሳሾቹ ገለጻ፣ የጉባዔው ሥልጣን ሕገ መንግሥትን ከመተርጎም ጋር ብቻ የተያያዘ እንጂ፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 78 እና 79 ለመደበኛ ፍርድ ቤቶች የተሰጠውን ሕግ የመተርጎም የዳኝነት ሥልጣን አልተሰጠውም፡፡ ሕገ መንግሥቱን ከመተርጎም አልፎ መደበኛ ሕጎች እንዴት መተርጎም እንዳለባቸው ለፍርድ ቤቶች መመርያ የሚያስተላልፍ ከሆነ፣ ተግባሩ የዳኝነት ነፃነትን የሚጋፋ ኢሕገ መንግሥታዊ ተግባር እንደሚሆንም አክለዋል፡፡

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ጉዳያቸውን እየመረመረው የሚገኘው ፍርድ ቤት የላከለትን “የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል ወይስ አያስፈልገውም?” ጥያቄን በቀጥታ “ትርጉም አያስፈልገውም” ከማለት አልፎ የሰጠው ምላሽ፣ አግባብ አለመሆኑን ተከሳሾቹ በማመልከቻቸው ገልጸዋል፡፡

የገቢዎችና ጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 አንቀጽ 182 መተርጎም ያለበት ሕጉ ከወጣበት አጠቃላይ ዓላማ፣ ከፍትሐዊነትና ከፍትሕ አንፃር እንጂ በቀድሞው ሕግ ለተከሰሱ ወይም ለተቀጡ ሰዎች ይጠቅማል ወይም አይጠቅምም ለሚል ምላሽ መሆን እንደሌለበት ተከሳሾቹ ጠቁመዋል፡፡

እነ አቶ መላኩ በማመልከቻቸው እንደገለጹት፣ በመሸጋገሪያ ድንጋጌው አንቀጽ 182 መግቢያ “በሌሎች ሕጎች የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ…” የሚለው ሐረግ የሚመለከተው ከጉምሩክ ጋር የተያያዙ አዋጆችን፣ ደንቦችንና መመርያዎችን ነው፡፡ በወንጀል ሕግ 5(3) እና በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22(2) የተመለከተውን መርህ እንደማይመለከት ተደርጎ ለመደበኛ ሕጉ የተሰጠው ትርጉም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 84(1) (3)ና በሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አዋጅ ቁጥር 798/2005 አንቀጽ 3(1) እና 12(1ሀ) ከተሰጠው ሥልጣን ውጪ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 78 እና 79 ለፍርድ ቤቶች የሰጠውን መደበኛ ሕግ የመተርጎም የዳኝነት ሥልጣን ውስጥ ለመግባት የሰጠው ትርጉም በመሆኑ፣ ተግባሩ ሕገ መንግሥቱን የሚጥስ መሆኑን ተከሳሾቹ በማመልከቻቸው ገልጸዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱ የአገሪቱ የበላይ ሕግ መሆኑ በአንቀጽ (9) መደንገጉንና ማንኛውም አካል የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት እንዳለበት የሚናገሩት ተከሳሾቹ አጣሪ ጉባዔውም ማክበር እንዳለበት አሳስበው፣ ፍርድ ቤቶችም ሕገ መንግሥቱን የሚጥስ ተግባር መፈጸሙን ሲረዱ፣ እንደ አንድ የሥርዓቱ አካል በአንቀጽ 9(2) በተጣለባቸው ኃላፊነት መሠረት ተግባሩን በማስወገድ ሕገ መንግሥቱን የማስከበር ኃላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ከፍርድ ቤት የተላከለትን የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ በማየት ጉዳዩ “የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል? ወይም አያስፈልገውም?” የሚለውን ብቻ በማየት ለፍርድ ቤቱ ምላሽ መስጠት ሲገባው፣ ጉዳዩ “የሕገ መንግሥት ትርጉም አያስፈልገውም” ከማለት ማለፉን ተከሳሾቹ በአቤቱታቸው ጠቁመዋል፡፡ ጉባዔው በሕግ ከተሰጠው ሥልጣን ውጪ የአዋጅ 859/2006 የመሸጋገሪያ ድንጋጌ አንቀጽ 182 እንዴት መተርጎም እንዳለበት ለፍርድ ቤቱ ያስተላለፈው መመርያ ወይም ውሳኔ፣ በሕገ መንግሥቱ የሰፈረውን የሥልጣን ክፍፍል የሚያፈርስና አንቀጽ 78 እና 79፣ እንዲሁም በአንቀጽ 9(2) መሠረት ሕገ መንግሥቱን የማስከበር ኃላፊነት ከመወጣት አኳያ የጉባዔውን ውሳኔ ውድቅ እንዲያደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡

አንድ ሰው የተከሰሰበትን ድርጊት ከፈጸመ በኋላ ተከሳሹን የሚጠቅም ሕግ ከወጣ፣ የሚጠቅመው ሕግ ሊፈጸምለት እንደሚገባ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 5(3)ና በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22(2) የሰፈረውን መሠረታዊ የወንጀል ሕግ መርህን ተፈጻሚነት ሊያስቀር እንደማይችል እነ አቶ መላኩ አስታውሰዋል፡፡ የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 አንቀጽ 182 እንዴት ሊተረጎም እንደሚችል የሚወስነው ፍርድ ቤቱ እንጂ ጉባዔው አለመሆኑንም አክለዋል፡፡ ጉባዔው መመርያም ሆነ ትዕዛዝ መስጠት እንደማይችልም ገልጸዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ጉባዔው የሰጠውን ትርጉም ወደ ጎን ትቶ፣ ቀደም ሲል ጉዳዩን ወደ ጉባዔው በላከ ጊዜ በያዘው ትርጉም መሠረት ጉዳዩን አይቶ እንዲወስንላቸው ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የሚያልፈው ከሆነ፣ ጉባዔው የሰጠው ትርጉምና ለትርጉም መሠረት ያደረጋቸው ምክንያቶች ሕገ መንግሥቱን መሠረት ያደረጉ ባለመሆናቸው ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 94(3ሀ) እና በፌዴሬሽን ምክር ቤት አዋጅ ቁጥር 251/93 አንቀጽ 5(2) መሠረት ሕገ መንግሥቱንም የሚተርጉም የመጨረሻ ሥልጣን ላለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጉባዔው ሙሉ ውሳኔ ግልባጭ ከነልዩነት ሐሳቡ፣ በአዋጅ ቁጥር 798/205 አንቀጽ 13 መሠረት በትዕዛዝ አስቀርቦ በመመርመር ለምክር ቤቱ እንዲልክላቸው አመልክተዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...