በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው የቀድሞ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ፣ የአረናና የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች የተከሰሱበትን የሽብርተኝነት ወንጀል ክስ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ ተሰናበቱ፡፡
በነፃ የተሰናበቱት አቶ ሀብታሙ አያሌውና አቶ ዳንኤል ሽበሺ ከአንድነት ፓርቲ፣ አቶ አብርሃ ደስታ ከአረና፣ አቶ የሺዋስ አሰፋ ከሰማያዊ ፓርቲ ሲሆኑ፣ አቶ አብርሃም ሰለሞን የተባሉ ተጠርጣሪም በነፃ ተሰናብተዋል፡፡
የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የመሠረተውን ክስ ሲመረምር የከረመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ነሐሴ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በሰጠው ብይን እንዳስረዳው፣ ተጠርጣሪዎቹ የቀረበባቸው ክስ ከጥርጣሬ ያለፈ ተግባር ስለመፈጸማቸው ዓቃቤ ሕግ የሰውም ሆነ የሰነድ ማስረጃ እንዳልቀረበባቸው አስረድቷል፡፡ በመሆኑም መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ብይን ሰጥቷል፡፡ አቶ ሀብታሙና አቶ አብርሃም በሌላ ወንጀል የማይፈለጉ ከሆነ በዕለቱ (ሐሙስ ነሐሴ 14 ቀን) እንዲፈቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ አቶ አብርሃ፣ አቶ የሺዋስና አቶ ዳንኤል ፍርድ ቤት በመድፈር ወንጀል የተጣለባቸውን ቅጣት እንደጨረሱ እንዲፈቱ አዟል፡፡
ከእነሱ ጋር ክስ የተመሠረተባቸው አቶ ዘለዓለም ወርቅአገኘሁ፣ አቶ ዮናታን ወልዴ፣ አቶ ሰለሞን ግርማ፣ አቶ ባህሩ ደጉና አቶ ተስፋዬ ተፈሪ ላይ ዓቃቤ ሕግ እንደ ክሱ በምስክሮችም ስላስረዳባቸው ክሳቸው በወንጀል ሕግ 113 መሠረት ተቀይሮ በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 7 (1) መሠረት እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ በነፃ እንዲሰናበቱ ብይን የሰጠባቸው እነ አቶ ሀብታሙ ባለፈው ዓርብ ሌሊት ኅትመት እስከገባንበት ሰዓት ድረስ ከእስር አለመፈታታቸው ታውቋል፡፡