Tuesday, February 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

ባቡሩን ጥበቃ በለገሀር

ትኩስ ፅሁፎች

የዘመናዊት ኢትዮጵያ መገለጫ ከሆኑት አንዱ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመን (1881 – 1903) የተጀመረው የምድር ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ነው፡፡ ሲጀመር የኢትዮጵያና የፈረንሳይ ምድር ባቡር ይባል የነበረው የአሁኑ የኢትዮጵያና ጂቡቲ ምድር ባቡር፣ የአዲስ አበባው መነሻ ለገሀር ባቡር ጣቢያ የሚባለው ነበር፡፡ ፎቶው በ1930ዎቹ የነበረውን ገጽታና ከምሥራቅ ኢትዮጵያና ከባሕር ማዶ በጂቡቲ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ዘልቀው የሚገቡትን መንገደኞች ለመቀበል የተሰለፉ የመዲናይቱ ተሽከርካሪዎች ይሆኑ? ፎቶው እንደሚያሳየው የፖሊሶች አለባበስ ቁምጣ ሱሪና ሰንደል ጫማ ነበር፡፡ ከፖስት ካርድ ላይ ያገኘነውን ይህን ምስል በፌስቡክ ገጹ የለጠፈው፣ ከ20 ዓመት በፊት  በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አማርኛ ቋንቋ የተማረው አንድርያስ ወተር ነው፡፡

(ሔኖክ መደብር)

*******************

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መዝሙር

ከግማሽ ምእት ዓመት በላይ ዕድሜ ባስቆጠሩት ሁለቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኢንስቲትዩት እና ባሕር ዳር መምህራን ኮሌጅ (አካዴሚ ፔዳጎጂጥምረት 1992 .የተመሠረተው ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ  ‹‹ከዓባይ ጓዳ ጥበብ ሲቀዳ›› የሚል መሪ ቃልም አለው፡፡ በቅርቡ በአማራ ቴሌቪዥን ‹‹መስኮተ ጥበብ›› የተሰኘ  የቴሌቪዥን ፕሮግራም የጀመረው ዩኒቨርሲቲው  ከመሪ ቃሉና ከግቡ  ጋር ተዘምዶ ያለው መዝሙርም ይፋ አድርጓል፡፡ የመዝሙሩ ግጥም ደራሲ ዶ/ ሙሉቀን አንዱዓለም  ሲሆኑ፣ በዩኒቨርሲቲው የዓባይ የባህልና ልማት ጥናትና ምርምር ማዕከል (ዓባልጥማዳይሬክተር ናቸው፡፡

በራዕይ ጥበብ ነግሣ

ራዕይ አለኝ፣ ራዕይ አለኝ፣

እኔ የማየው፣ የማልመው፣ በገሐድ የሚታየኝ፡፡

ራዕይ አለኝ፣ ራዕይ አለኝ፣ ራዕይ አለኝ፣

እኔ የማየው፣ የማልመው፣ በገሐድ የሚታየኝ፤ ራዕይ አለኝ፣

       የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በራዕይ ጥበብ ነግሣ፣

       ሰማያዊ ጥበብ ለብሳ፣ ጣና ሐይቅን ተንተርሳ፣

       ሊነጋጋ ሲል በማለዳ፣ ከዓባይ እልፍኝ ከዓባይ ጓዳ፣

       ዘወትር አያታለሁ ጥበብን ስትቀዳ፡፡

የወርቅ ዋንጫዋን ከፍ አድርጋ በቀኟ ይዛ ቀድማ ሮጣ፣

ሁሉንም የሚያስደስት የግብዣ ጥሪ ካፏ ወጣ፣ (2)

ከቀዳሁት ከጥበቤ በነፃነት እንዲጠጣ፣

ጥበብን የተጠማ ዛሬም ነገም ወዲህ ይምጣ፡፡

  • በዶ/ር ሙሉቀን አንዱዓለም 

**************

አሁንስ ተስፋዬ ማነው? ዳያስፖራ አይደለምን?

አለች ኢትዮጵያ፤ የውጭ ንግዷ ያስገኘላት ገቢ ዳያስፖራው ከሚልከው ረሚታንስ(ድጎማ) ቢያንስባት። ወደፊት ግን ሃገሬን እመክራታለሁ። በሰው ኪስ ላይ ከመንጠልጠል በንግድ ገቢ ላይ መመካት ይሻላልና ኤክስፖርቱን ጠበቅ፣ ዳያስፖራውን ላላ ማድረግ ሳይሻላት አይቀርም።

ውጭ የኖረ ሰው አንድ የትውልድ ሃገር ብትኖረውም ሌላ መቀመጫ ሃገርም አለችው። እዚህ ቢደብረው እዛ ሄዶ ያኮርፋል። እዚህ አቧራ ቢቦንበት እዚያ ሄዶ ፊቱን ቅባት ይወለውላል። እዚህ ጭቃ ቢነካው እዚያ ሄዶ ይታጠባል። አማራጭማ ግጥም አድርጎ አለው እንጂ!!

እኛን የዚህች ሃገር ዋሊያዎችን ነው አጥብቆ መያዝ ወዳጆቼ!! ………ከፋንም ደስ አለንም እዚችው እየኖርን…ችግሩንም አብረን ተቸግረን፣ ክፉ ቀኑንም አብረን ገፍተን ፣አማራጭ ሃገር የለንም ብለን ሃገራችን ላይ የሙጥኝ ያልነውን እኛን ነው አጥብቆ መያዝ አለሞቼ!!! ወጡን አኛ ሰርተን እፍታውን ለሱ መስጠትማ ደግም አይደል!!

ይልቅስ የያዝነው ዘመን እጅ ይፈልጋልና ቆርጦ መጥቶ አብሮን ጭቃ እንዲያቦካ፣ ሲሚንቶ እንዲመርግ፣መሬት እንዲቆፍር ማሳመን ይሻላል። አለያ እኛ ቤት ሰርተን አንተ ኑር ካልነው፣ እኛ መንገድ ጠርገን አንተ መኪና ንዳበት ካልነው ምኑን የልማት አጋር ሆነው? ሳናስበው ኪራይ ሰብሳቢ አደረግነው ማለትም አይደል? ገንዘብ ብቻ ሃገር አይገነባም ጎበዝ። ሙሉ ጊዜና ያልተቋረጠ ድጋፍም ግድ ነው። ባይሆን የሰው ሃገር ያደገበትን ዘዴ የቀሰመውን ሰው መረጥረጥ አድርገን ፈጣኑን መንገድ እንዲያመላክተን ብናደርግ ብዙ እናተርፋለን። ……ብሳሳትም ልክ ብሆንም እኔ የታየኝ እንዲህ ነው ዘመዶቼ!!!

  • መላኩ ብርሃኑ በገጹ እንደከተበው

********

የኔ ንብረትማ

አንድ ሽማግሌ ባህታዊ የአንድ እጅግ ሀብታም ንጉሡ ቤተ መንግስት እንዲጐበኙ ተጋበዙ፡፡ ‹‹የተቀደሱት ባህታዊ በጥቂት ንብረትዎ ረክተው መኖር መቻልዎ በአያሌው ያስቀንኛል›› በማለት ንጉሡ ተናገሩ፡፡

‹‹ከኔ ባነሰ ንብረትዎ የረኩት እርስዎ ይበልጥ ያስቀኑኛል›› ባህታዊው መለሱ፡፡
ንጉሡም በባህታዊው መልስ ግራ ተጋባ፡፡ የንጉሡ ግራ መጋባት ያስተዋሉት ባህታዊው፡-
‹‹እኔማ ንብረቴ ብዙ ነው፡፡ ….የሰማያት ዝማሬ አለኝ፤ ወንዞችና ተርሮችአሉኝ፤ ጨረቃና ፀሀይም የኔ ናቸው፡፡ የሌለኝ ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም በልቤ ውስጥ አምላክ ነግሧል፡፡
ግርማዊነቶዎ በአንፃሩ ግን ድሃ ኖዎት፡፡ ግዛትዎ ከዚህች የተከለለች ምድር አይሰፋም››

******

‹‹በእውነት የምትሰጡት ከገዛ ራሳችሁ ስትሰጡ ነው፡፡››

የተወደድከው አልሙስጠፋ፡- ‹‹ስለ መስጠት ንገረን››፡፡ እርሱም አለ፡- ‹‹ከሀብቶቻችሁ ስትሰጡ ጥቂት ብቻ ትሰጣላችሁ፡፡ በእውነት የምትሰጡት ከገዛ ራሳችሁ ስትሰጡ ነው፡፡ ነገ ትፈልጓቸው እንደ ሆነ ከመፍራት የተነሳ የምትጠብቋቸውና የምትንከባክቡዋቸው ነገሮች ናቸው እንጂ ሀብቶቻችሁ ምንድን ናቸው?
ካላቸው ብዛት ጥቂት የሚሰጡ አሉ ….. የሚሰጡትም ለመዘከር ነውና ድብቁ ምኞታቸው ስጦታዎቻቸውን ያበላሻል፡፡

ጥቂት ያላቸውና ሁሉንም የሚሰጡ አሉ ….. እነዚህ ሕይወትንና በሕይወት ልግስና የሚያምኑ ናቸው፤ ሳጥናቸው ከቶ ባዶውን አይሆንም፡፡ በደስታ የሚሰጡ አሉ….. ያም ደስታ ሽልማታቸው ነው፡፡

በስስት የሚሰጡ አሉ….. ያም ስስት መፍትሔያቸው ነው፡፡ በመስጠት ስስት የማያውቁ የሚሰጡ አሉ፤ደስታም አይፈልጉም፡፡ ለደግነትም ብለው አይሰጡም፡፡
ከማዶ ሸለቆ ውስጥ የአበባዋ ዛፍ መዓዛዋን ወደ ህዋ እንደምትተነፍስ፣ እነርሱም ይሰጣሉ፡፡
እንደዚህ ባሉት ሰዎች እጆች በሉል እግዚአብሔር ይናገራል፤ ከዓይኖቻቸውም ጀርባ ሆኖ በምድር ላይ ፈገግ ይላል፡፡ ሲጠየቁ መስጠት ደህና ነው ግን በማስታዋል ሳይጠየቁ መስጠት የተሻለ ነው፡፡ ‹‹የመስጠት ወቅት የናንተ እንዲሆን እንጂ የወራሾችችሁ እንዳይሆን አሁን ስጡ፡፡›› ካህሊል ጂብራን

  • ነፀብራቅ በዛብህ በገጹ ያሰፈረው

*********

ምን እንጠጣ?

. . . .በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣው የአልኮል መጠጥ ፍላጎት በተለይም የቢራው ገበያ የዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን ትኩረት እየሳበ ነው፡፡ የኔዘርላንዱ ሀይኒከን ከናይጄሪያና ከደቡብ አፍሪካ ቀጥሎ በኢትዮጵያ ግዙፉን ፋብሪካ በአቃቂ ገንብቶ በመጨረስ ማምረት ጀምሯል፡፡ ከዚህ ቀደም ሁለት የሀገሪቱን ግዙፍ የቢራ ፋብሪካዎችን ማለትም በደሌና ሐረር ቢራን በ200 ሚሊዮን ዶላር ግዢ የራሱ አድርጓል፡፡ የእንግሊዙ ዲያጂዮም እንዲሁ ሜታን ጠቅልሎታል፡፡ ሌሎችም በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣውን የደራ የአልኮል መጠጥ ገበያ የተረዱ የውጭ የቢራ ጠማቂዎች ወደ ምድሪቱ ሊመጡ ተነቃቅተዋል፡፡ በሀገራችንም የቢራ ቢዝነሶችን ለማቋቋም አክስዮኖች በከፍተኛ ሁኔታ እየተሸጡ ወደ ጠመቃው በመገባት ላይ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትራችንም ቀደም ብለው ዝዋይ አካባቢ የሚገኘውን በሀገሪቱ ትልቁን የወይን መጥመቂያ በመቀጠልም አቃቂ ላይ የተገነባውን ግዙፋን የሄይኒከን የቢራ ፋብሪካ አስመርቀው የፊታውራሪነት ድርሻቸውን አበርክተዋል፡፡ ከሰሞኑ በርካታ የኢኮኖሚ መሻሻሎችን እያሳየች እንደሆነ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጭምር እየተነገረላት ያለችው ሀገራችን፣ ‹‹በቤተሰብ ደረጃ በምግብ ራሷን ለመቻል›› ከመዳኽ አልፋ በመጠጥ ‹‹ወፌ ቆመች›› ችግሯን በአልኮል አጥምቃ ለመቅረፍ ላይ ታች እያለች ያለች አስመስሎባታል፡፡ የጠጪ ወጣቱ ትውልድ አባል መበራከት፡ – ያኛው ትውልድ ‹‹ተራሮችን ያንቀጠቀጠ›› ሲሆን ይህ ትውልድ ደግሞ የመጠጥ ቤት ‹‹ባንኮኒዎችን ያንቀጠቀጠ›› ትውልድ የሚል ሥያሜ በአንዳንዶች እንዲሰጠው ሆኖአል፡፡ ይህ ስያሜ ሁሉንም የትውልዱን አባል ባይወክልም ግና ብዙ የትውልዱ አባላት ከ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ በከፍተኛ ጠጪነት ውስጥ እየተዘፈቁ መምጣታቸው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡

ቀደም ባሉት ጊዜያት በአማኞች ዘንድ እንደ ነውር ይቆጠር የነበረው የአልኮል መጠጥን መውሰድ እንደ ቀላልና ተራ ነገር መታየት ከጀመረ ሰነበተ፡፡ ብዙ ወዳጆቼና ወገኖቼ የአስተሳሰብ ‹‹ትራንስፎርሜሽን›› በማምጣት የአልኮል መጠጥ የሚወስዱ በመሆኑ አንዳንዴ ኋላ ቀር እንደሆንኩ ሊሰማኝ ይዳዳዋል፡፡ ቆየት ብዬ በአንዳንድ አጋጣሚ የማገኛቸው አንዳንድ የቀድሞ ጓደኞቼ፣ የሥራ ባልደረቦቼ፣ የአንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያን አባላት የነበርን ወዘተ ምግብ ልንበላ በተቀመጥንበት አስተናጋጁ “የሚጠጣ?” ሲል ወይን ወይም ቢራ ምናምን ሲያዙ መመልከት በመጀመሪያ ቀልድ ሲመስለኝ የምራቸውን እንደሆነ ስረዳ ግን ትንፋሼ ለሰከንዶች የተቋረጠበትን ጊዜ አስታውሳለሁ፡፡ ይህንን ሁናቴ ‹‹የመጠጥ አብዮት›› ልበለው ወይስ ምን? ኢትዮጵያዊ ድህነቱን በቢራና በወይን እንዲረሳ እየተጣረ መሆኑ ነው እንግዲህí

ብዙዎች ባዶ ሆዳቸውን በሚያድሩባት ሀገር በሚያሳዝን ሁኔታ የአንደኛ ደረጃ ህጻናት ተማሪዎች ሳይቀሩ አልኮል መጠጥ የሚጨልጡባት ሀገር እየሆነች ነው ኢትዮጵያ፡፡ ‹‹ዴይ ፓሪ፣ ናይት ፓሪ›› (Day party, Night party) በሚባሉ ከሆሊዉድ ‹‹እስኩል ላይፍ›› (School life) ፊልሞች በተኮረጁ የርኩሰት መለማመጃ ስፍራዎች ልጆች ወላጆቻቸውን ተደብቀው በመጠጥ፣ በአደንዛዥ ዕፅና በዝሙት ይነከራሉ፡፡ ያለአግባብ በአቋራጭ የከበሩና ሕዝቡን በዝብዘው አንቱ የተባሉ የምድራችን ነጋዴ ‹‹ሹገር ዳዲዎች›› እምቦቃቅላ ሴቶቻችንን በእንቡጥነታቸው በመቅጠፋቸው በምድርም በሰማይም ተጠቂዎች ናቸው፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት ሴቶቻችን አልኮል በአደባባይ መጠጣት ቀርቶ ሆቴል ቡና ቤት ለብቻቸው መታየትን  እንደነውር ነበር የሚያዩት፡፡ መሰለኝ፡፡ ዛሬ ላይ ግን ለምግብ ማወራረጃ ቢራና ወይን እንደውሀ ሲጨልጡ በየጥጋጥጉ መመልከት ተራ ነገር ሆኗል፡፡ አልኮል በአደባባይ ከመውሰድ ባለፈ ጭምትነቱ በሁሉም ቦታ መጥፋቱ ለትዳሮች መፈራረስ፣ ለቤተሰብ መበተን፣ ለሞራላዊ እሴቶች መናድ ወዘተ ትልቁን ሚና ይጫወታል፡፡ ከምዕራቡ ዓለም የቀዳነው እርባና ቢስ ዘመናዊነት አቅል አሳጥቶ ወደማንወጣው አዘቅት ውስጥ አንደርድሮ እየዘፈቀን ነው፡፡ ችግሩን ቆም ብሎ ተመልክቶ መፍትሔ ከማፈላለግ ይልቅ ሁሉም በቸልተኝነት ለገዛ ንግዱ ይሮጣል፤ ሀይ ባይ ጠፍቷል፤ ጎበዝ ምን ይበጀናል ትላላችሁ?

  • መሳይ ማቱሳላ በድረ ገጹ እንደጻፈው

 

 

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች